ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) አሁን የተፈጠረው የፖለቲካ ውጥረት እና ልዩነት ወደ ትግራይ የጸጥታ ሃይሎች እንዳይዛመት እየሰራን ነው ሲሉ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ ተናግረዋል።
የጊዚያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ይህንን የተናገሩት በትግራይ ክልል ለሚገኙ መገናኛ ብዙሃን በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
በትግራይ ተፈጥሮ የሚገኘው ፖለቲካዊ ውጥረት ወደ ሃይል ሽኩቻ እንዳይሸጋገር የጸጥታ ሃይሎች ከማንኛውም አይነት ፖለቲካዊ ውግንና ነጻ በመሆን እየሰራን ነው የሚሉት ጄኔራሉ፣ በዚህ ዓውድ ብዙ የሚያስጨንቅ ሁኔታ እንደሌለ ገልጸዋል።
አያይዘውም በትግራይ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ ውጥረቶች የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነቶች እስከሆኑ ድረስ ‘‘ለምን አጋጠሙ?’’ ሳይሆን መባል ያለበት፣ ‘‘እንዴት በሰለጠነ መንገድ መፍታት ይቻላል?’’ የሚለው ነገር አስፈላጊ ጉዳይ ነው ያሉ ሲሆን አሁን የሚያጋጥሙ ፖለቲካዊ ውጥረት እና ልዩነቶች በትግራይ የጸጥታ ሃይሎች ዘንድ እንዳይስተዋል ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል።
እስካሁን ድረስ በዚህ አኳኋን እየተጓዝን ነው። በጥሩ ሁኔታ ላይ ነን ሲሉ ያብራሩት ጄኔራል ታደሰ በትግራይ አጋጥሞ ያለው ፖለቲካዊ ውጥረት በመጨረሻ በሰለጠነ መንገድ ዕልባት ያገኛል የሚል ዕምነት አለን በማለት አስረድተዋል።


