ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ( አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ መንገድ ዳር ሽንታቸውን ሲሸኑ የተገኙ 22 ግለሰቦች 44 ሺህ ብር ተቀጡ
በተለይም በመዲናዋ ህገወጥ የመሬት ወረራ ያከናወኑና ሽንታቸውን ሲሸኑ በተገኙ ግለሰቦች ላይ ቅጣት አስተላልፊያለሁ ያለው የአዲስ አበባ ደምብ ማስከበር ባለስልጣን ነው፡፡
ባለስልጣኑ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረደ 11 ባልተፈቃደ ቦታ ሽንታቸውን በመሽናት አካባቢ ያቆሸሹ 22 ግለሰቦች በባለስልጣኑ በተሻሻለዉ የቅጣት ሰንጠረዥ 2 ደንብ ቁጥር 167/2016 መሰረት እያንዳንዳቸው 2 ሺህ ብር አጠቃላይ 44 ሺህ ብር በመቅጣት ለመንግስት ገቢ ማደረጉን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 የህዝብና የመንግስት የሆነ መሬት በህገወጥ መንገድ በመውረር ታጥሮ የነበረ 5 ቦታዎች በአጠቃላይ 2,200 ካሬ ሜትር መሬት በአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን እርምጃ ስለመወሰዱ ባለስልጣኑ አሳውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በህገ ወጦች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፀ ሲሆን ሆን ብለዉ ደንብ የሚተላለፉ አንዳንድ ግድ የሌሽና ስግብግብ ግለሠቦች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ሲልም አስጠንቅቋል፡፡



