አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ አረፈ 

0
602

ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ( አዲስ ማለዳ) አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ በትናትናው እለት ባጋጠመው ህመም ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል፡፡

በ1957 ዓ.ም በሐረር ከተማ የተወለደው አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ በትወና በመድረክ ቴአትሮች ላይ ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ መሳተፍ የጀመረ ሲሆን በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ‘የዝናቧ እመቤት ‘ እና ‘የገንፎ ተራራ’ ቴአትሮች ፤ በሀገር ፍቅር ቴአትር ‘የጨረቃ ቤት’ ፣ ‘ዓይነ ሞራ’ ፣ ‘ንጉሥ ሊር’ ፣ ‘ፍሬህይወት’ ፣ ‘ጥሎሽ’ ፣ ‘አሉ’ ፣ ‘ጣውንቶቹ’ ፣ ‘ከራስ በላይ ራስ’ እና ‘የሸክላ ጌጥ’ ቴአትሮች ፤ በቴአትርና ባህል አዳራሽ ‘የጫጉላ ሽርሽር’ ቴአትር ፤ በራስ ቴአትር ‘ቅርጫው’ ቴአትር ይገኙበታል።

ከዚህ ባለፈም ከአመት በፊት በአርትስ ቴሌቪዥን በተላለፈው ‹‹እረኛዬ›› በተባለው ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ላይ በመሳተፍ ድንቅ የትወና ብቃቱን አሳይቷል፡፡

በዳይሬክቲንግ ሥራዎች ካዘጋጃቸው የመድረክ ቴአትሮች መካከል በሀገር ፍቅር ቴአትር ‘ስጦታ’፣’ጥሎሽ’ እና ‘መዳኛ’ ቴአትሮች ፤ በቴአትርና ባህል አዳራሽ ‘ሶስና’፣’አንድ ክረምት’፣ጥቁሩ መናኝ’ እና የጫጉላ ሽርሽርና ሌሎች በርካታ ቲያትሮች ይገኙበታል፡፡

አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ በ1979 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በቲያትር ትምህርት አግኝቷል፡፡

የሦስት ልጆች አባት የነበረው ኩራባቸው ደነቀ ነገ ከ5:00 – 6:00 በቀጨኔ መድኃኒዓለም ስርዓተ ቀብሩ ይፈጸማል ።

አዲስ ማለዳ ለአርቲስት ኩራባቸው ደነቀ ቤተሰቦች እና ወዳጆች መጽናናትን ትመኛለች!

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here