ማክሰኞ ነሐሴ 21 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የሞንኪፖክስ ወረርሽኝ ወደ ኢትየጵያ አለመግባቱን ገልጸው በኦክስፋምና በአንዳንድ አለም አቀፍ ድርጅቶች የተሰራጨው መረጃም ሃሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
“የእኛም ሰዎች እዛው ድረስ በመሄድ አረጋግጠዋል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ምንም እንኳን ምልክታቸው አንድ ቢመስልም ያጋጠመው ግን ሞንኪፖክስ አይደለም ብለዋል፡፡
ቺክንፖክስ የሚባል ቀለል ያለ በሽታ ነው ያጋጠመው ያሉት ዶ/ር ደረጄ ይህ ብዙ ቦታዎች አለ፤ ሰሞኑን ይሄኛው ስለተነገረ፣ ስለሆነ ከጥርጣሬ የተነሳ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎች ትክክለኛ አለመሆናቸውን አንስተው ስለበሽታው በጤና ሚኒስቴር በኩል ብቻ የሚወጡ መረጃዎችን መከታተል እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ ተረጋግቶ የእለት ተእለት ተግባሩን እንዲያከናውን ያሳሰቡት ደ/ር ደረጄ አሁን ላይ የሚያሰጋ ምንም ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
በአየርመንገድና በመሰል የከተማዋ መውጫና መግቢያ አካባቢዎች ተከታታይነት ያለው ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡



