ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ መታወቂያ የሌላቸው አሽከርካሪዎች ከዚህ በኋላ የባጃጅ አገልግሎት መስጠት እንደማችሉ የሚደነግግ አዲስ መመሪያ መውጣቱ ተሰምቷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የባለሶስት እና አራት እግር ተሽከርካሪ ወይም ባጃጅ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የአሰራር ፣ የአጀረጃጀት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና የዲሲፒሊን ቁጥጥር አፈጻጸም መመሪያ ላይ ያተኮረ ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው ይህ ጉዳይ የተነሳው።
በአፈፃፀም መመሪያው የባለ ሶስትና አራት እግር ተሽከርካሪ ወይም ባጃጅ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ካሁን ቀደም ሲያጋጥሙ የነበሩ የሕግ ጥሰቶችንና የደንብ መተላለፎችን ለመከላከል ሲባል አገልግሎት ሰጪዎች የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ፣የአዲስ አበባ የሠሌዳ ቁጥር እና በማህበር መደራጀት እንደሚኖርባቸው ተገልጿል።
በአዲስ አበባ፣ የከተማ አስተዳደሩን ታርጋ ለጥፈውና የአዲስ አበባ መታወቂያ ይዘው ከሚሰሩት ይልቅ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ አሽከርካሪዎች መበራከት የፀጥታ ችግር ሆነው ቆይተዋል ” ተብ።
ይህ ደግሞ በተለይ በወንጀል ድርጊት ላይ ተሳትፈው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ አዳጋች እንደነበር ተገልጿል።
ከዛ ባለፈ የባጃጅ ትራንስፖርት የከተማዋን ዘመናዊ እሳቤ የሚመጥን ስላልሆነ በሂደት ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱ የሚቋረጥ ይሆናል ተብሏል።
እስከዚያ ጊዜ ድረስ የባለሶስት እግር አሽከርካሪዎች የአዲስ አበባ መታወቂያ፣ ታርጋ እና በማህበር መደራጀት ይኖርባቸዋል ተብሏል።
አሁን ላይ በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ሰፊ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎት በመኖሩ በነዚህ አካባቢ ያለው ፍላጎት በሌላ አማራጮች እስኪተካ ድረስ አገልግሎቱ እንደሚቀጥል ተመላክቷል።
በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባሉባቸው እንዲሁም በውስጥ ለውስጥ ሰፈሮች ዜጎች ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎችን / ባጃጅ ለትራንስፖርት ይጠቀማሉ።
እጅግ በርካታ ዜጎችም በተለይ ወጣቶች በዚሁ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ገቢ ያገኛሉ ቤተሰባቸውንም ያስተዳድራሉ።
ከዚህ ቀደም ባጃጆች በተለይ በከተማው ዳር ከዋና አውራ ጎዳናዎች በመውጣት እንዲሰሩ መደረጉ የሚዘነጋ አይደለም።



