ሐሙስ ነሐሴ 30 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በቅርቡ በተደረገው አወዛጋቢ ጉባኤ የህወሃት ምክትል ሊቀ-መንበር ሆነው የተሾሙት አቶ አማኑኤል አሰፋ የድርጅቱ ልሳን ከሆነው ወይን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
አቶ አማኑኤል በቆይታቸው በፕሪቶሪያው ስምምነት ውስጥ ህወሃትን የሚያፈርሱ፣የፓርቲውን አወቃቀር የሚያናጉና በድርድር ውስጥ የድርጅቱን ሚና የሚያሳንሱ ነጥቦች በአደራዳሪዎች ግፊት ተካተዋል ሲሉ ከሰዋል፡፡
አክለውም በድርድር ወቅት ህወሃትን ለማፍረስ የተለያዩ ስልቶችን ሲጠቀሙ የነበሩት አደራዳሪዎች በተለይም ለፌድራል መንግስቱ ውግንና ያላቸውን ነጥቦች አካተው ህልውናችንን ሊያሳጡን ሞክረዋል ብለዋል፡፡
ምክትል ሊቀመንበሩ ታዲያ ጎጂ የስምምነት ነጥቦች ባሉበት ሁኔታ እንዴት ለድርድር አልፎም ለስምምነት ድርጅታቸው እንደ ተቀመጠ ባያብራሩም በአጠቃላይ ስምምነቱ የህወሃትን አመራሮች ለመነጣጠል ሆን ተብሎ የተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ በስምምነት የተቋጨው የሰሜኑ ጦርነት አፈጻጸሙን በሚመለከት በአፍሪካ ህብረትና በሌሎች የማደራደር ሚና በነበራቸው አካላት ተደጋጋሚ ግምገማ እየተደረገበት እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡



