ሐሙስ ነሐሴ 30 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ከሁለቱ የህወሓት ቡድኖች መካከል አንዱ ከኤርትራ ሐይሎች ጋር ግንኙነት እንዳለው እንደሚገነዘብ አረና ትግራይ ፓርቲ አስታውቋል።
ከህወሓት፣ ከሻዕብያ እንዲሁም ከብልፅግና ወገን ወንጀል የፈጸሙ ተጠያቂ ባለመደረጋቸው አሁንም የጦርነት ፍላጎት አለ ያለው ፓርቲው ይህ ደግሞ ክልሉን ለዳግም ውድመት የሚጋብዝ ነው ብሏል፡፡
በትግራይ አሁንም ወደ ጦርነት የሚወስዱ መንገዶች እየታዩ ያሉት እና የጦርነት ነጋሪት የሚጎሰመው ባለፈው ሁለት ዓመት ለነበረው ጦርነት ከሁሉም ወገን ተጠያቂነት ባለመረጋገጡ ነው ያሉት የዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ አሁንም ሌላ ጦርነት ለማድረግ ነጋሪት እየተጎሰመ ነው ሲሉ ስጋቸውን ገልጸዋል።
ከህወሓት ይሁን ከሻዕብያ እንዲሁም የብልፅግና ወገን የጦርነቱ ተጠያቂዎች ስላልቀረቡ አሁንም የጦርነት ፍላጎት እየታየ ነው ሲሉም አክለዋል።
ሁለቱ ህወሓት ውስጥ ያሉ ቡድኖች አንዱ ሌላውን ከአስመራ እና አዲስ አበባ ጋር ካሉ ሐይሎች በመመሳጠር እርስ በርስ ይካሰሳሉ ያሉት ሊቀመንበሩ ከሁለቱ የህወሓት ቡድኖች መካከል አንዱ ከኤርትራ ሐይሎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ፓርቲያቸው እንደሚገነዘብ ጨምረው ገልፀዋል።



