ሰኞ ጳጉሜ 04 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት (ፓርኪንግ) በማዘመን የቁጥጥር እና የተሽከርካሪ ማቆሚያ አሰራር መፈጠሩን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ከዚህ በኋላ ደረሰኝ በተቋማት ማሳተም፣ በሲስተሙ ወይም በቦታው ከተተመነው ታሪፍ ውጪ እንደፈለጉ ማስከፈል፣ ሰአት አራዝሞ ወይንም አሳንሶ ማስከፈል እንደማይቻል ተጠቁሟል፡፡
በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ለመጀመር መታቀዱን የተናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የመንገድ ደህንነት እና ኢንጂነሪንግ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ኤልያስ ዘርጋ አሰራሩ ይህን ያህል ቆጠረ ይህን ያህል ክፈል የሚለውን ጭቅጭቅ እንደሚያስቀር አመላክቷል፡፡
እንዲሁም ተሽከርካሪው ሲቆም ሲስተሙ ላይ ታርጋውን በማስገባት የክፍያ ተመኑን ይወስናል የተባለ ሲሆን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችም ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው መጠናቀቃቸውም ተገልጻል፡፡
የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት ከመስጠት ጋር ተያይዞ እስካሁን ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት ደረሰኝ በማሳተም እና አንጸባራቂ እንዲለብሱ በማድረግ የተሸከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል።



