በአዲስ አበባ አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች የጤና መድህን አባል ሆኑ

0
1484

በአዲስ አባባ ከተማ በሶስት ወራት ውስጥ በስራቸው ከአምስት ሰው በላይ የያዙ ከ183 ሺሕ በላይ አባ ወራዎች የማህበረሰብ አቀፍ ለጤና መድሕን አባልነት ተመዝግበው ከ 75 ሚሊዮን ብር በላይ ማዋጣታቸውን መሰብሰብ መቻሉን የኢትጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ አስታወቀ።

ምዝገባው ከ ጥቅምት ወር ጀምሮ በአዲስ አባባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከ 115 በላይ ወረዳዎች እሰከ ታህሳስ 30 ሲከናወን የቆየ ሲሆን በአማካኝ በስራቸው እስከ አምስት የቤተሰብ አባላት አቅፈው የያዙ ከ183 ሺሕ ነዋሪዎች በጤና መድህን አባልነት መመዝገብ ተችሏል።

ተመዝጋቢ ቤተሰብም በጋራ የጤና መድህኑ አባል ለመሆን 350 ብር የአባልነት ክፍያ እና የመመዝገቢያ ክፍያ 20 ብር የሚከፍሉ ሲሆን በአንድ ቤተሰብ ውስጥም ባል እና ሚስትን ጨምሮ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች የነፃ ህክምና አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ። ነገር ግን 18 ዓመት የሞላቸው ልጆች እና ሌሎች የቤተሰብ አባላት ሽፋኑን ባገኛ ቤተሰብ ውስጥ ካሉ እያንዳንዳቸው 70 ብር በመክፍል የጤና መድህን አባል መሆን እንደሚችሉ ተገልጿል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን መርሃ ግብር ተመዝጋቢዎች በየዓመቱ በሚያዋጡት 350 ብር ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ እና ድንገተኛ ወጪ በመንግስት የህክምና ተቋማት የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት አማራጭ ሲሆን የህክምና ወጪውም በኤጀንሲው የሚሸፈን ነው።

በዚህ ዙር ምዝገባም በክፍለ ከተማ ጤና ቢሮዎች አማካኝነት ስለ አገልግሎቱ እውቀት እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት በጤና መድን ኤጀንሲ የአዲስ አባባ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ብርሃኑ አይካ የጤና መድህን አላማው የተሻለ ገቢ ያለው የማህበረሰብ ክፍል እና በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደረው የማህበረሰብ ክፍል የሚያዋጡትን ግንዘብ በማስተዳደር ሁሉም ዜጎች የጤና አገልግሎትን ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

በከተማዋ በሚገኙ 13 ሆስፒታሎች እና በሁሉም ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት በመሰጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን የጤና መድህን አባልነት መታወቂያ ያላቸው አባላት የተመላላሽ ህክምና፣ አስተኝቶ ማከም፣ ቀዶ ጥገና ፣ በህክምና ባለሙያዎቸ የታዘዙ ምርመራዎችን እንዲሁም የጽንስ ክትትል እና የወሊድ አገልግሎቶችን ከመድሃኒት አቅርቦት ጋር የሪፈራል ስርሃቱን በጠበቀ መልኩ በሁሉም ከፍተኛ እና ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል።

በአንዳንድ የጤና ተቋማት የመድሃኒት እጥረት እና የላብራቶሪ አለመኖር ቅሬታ እየፈጠረ እደንሚገኝ የገለፁት ሃላፊው አገልግሎቱ ባለባቸው በከተማዋ በሚገኙ መድሀኒት ቤቶች አባላት መድሀኒቶችን በነፃ እንያገኙ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ከሶስት ዓመታት በፊት የጤና መድህን ሽፋኑን በመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከአስር በላይ ሰራተኞችን በሚያስተዳድሩ የግል ድርጅቶች ላይ ለመተግበር ታስቦ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መቅረቱ ይታወሳል። ከሰራተኞች ደመወዝ ላይ በየወሩ ሶስት በመቶ በመውሰድ የጤና መድህኑ አባል እንዲሆኑ ለማድረገ ሃሳ ቀርበው እንደነበር የገለፁት ብርሃኑ ከሰራተኞች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ስምምነት ላይ ባለመደረሱ እንዲዘገይ ተደርጓል ብለዋል።

‹‹በጤና መድህን ውስጥ መታቀፍ ግዴታ መሆን የለበትም፣ ከደሞዝ ላይ የሚቆረጠው ገንዘብ ብዙ ነው፣ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ባል እና ሚስት እንዲመዘገቡ መደረጉ አግባብ አይደለም እንዲሁም ለኩላሊት ስራ ማቆም ለሚደረግ ህክምና የጤና መድህን ሽፋን አለመሰጠቱ አግባብ አይደለም›› በሚል ሰራተኞች ቅሬታ በማቅረባቸው ኤጀንሲው መቸገሩንም ብርሃኑ ጨምረው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በበለፀጉት አገራት የጤና መድህን ሽፋን የተለመደ አሰራር እንደሆነ የገለፁት ብርሃኑ በኢትዮጵያ ገና በጅማሮ ላይ የሚገኝ አሰራር መሆኑን አስታውሰዋል። ዜጎች በረዢም ጊዜ በከፈሉት ክፍያ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት የህክምና ተቋማት አገልግሎት አቅራቢ ኤጀንሲው ደግሞ አገልግሎቱን የሚገዛ የሚሆንበትን አሰራር ለመተግበር በስፋት እደንሚሰራም ተናግረዋል።

የዚህ ዓመት የክልሎች የጤና መድህን አባልነት ምዝገባ በያዝነው ጥር ወር እና የካቲት መካሄድ እንሚጀምር ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here