የጠቅላይ ሚኒስትሩ የትዊተር ገፅ 20 በመቶ ተከታዮች በማሽን የተፈበረኩ ሐሰተኛ አካውንት መሆናቸው ተገለፀ

0
389

የመብቶችና ዴሞክራሲ ብልጽግና ማእከል (ካርድ) ከትዊተር ኦዲት አገኘሁት ባለው ጥናት መሰረት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የግል የትዊተር አካውንትን ከሚከተሉ ከ100 ሺሕ ተከታዮች መካከል 80 በመቶው ትክክለኛ ተከታዮች ሲሆኑ 20 በመቶው ግን ትዊተር ቦት ወይም በማሽን የሚፈበረኩ ሐሰተኛ አካውንቶች መሆናቸውን አስተወቀ።

ይኸው ድርጅት ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የኦፌኮ አባል የሆኑት ጃዋር መሐመድ ካሏቸው 95 ሺሕ በላይ ተከታዮች ውስጥ 66 በመቶው ትክክለኛ የትዊተር አካውንቶች ሲሆኑ ቀሪ 34 በመቶ የሚሆኑት ግን እነዚህ ሐሰተኛ አካውንት ወይም ቦቶች መሆናቸውን ካርድ አስታውቋል።

በታኅሳስ ወር የተሠራው ይህ ጥናት አምስት ሺሕ የተከታይ ናሙናን በመውስድ የተሠራ ሲሆን፣ እነዚህ በገንዘብ የሚገዙት የሐሰት አካውምቶች የሚከተሉትን ግለሰብ ትዊቶች በመጋራት እና በማደናነቅ በእውነተኛ ተከታዮች ላይ ጫና እንደሚያሳድሩም የኒው ዮርክ ታይም የምርመራ ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በተመሳሳይም ሪፖርቱ ይፋ እንዳደረገው፣ መንግሥት መረጃን በጊዜ ባለመስጠቱ ሐሰተኛ መረጃ ለሚያሰራጩ አካላት በር እየከፈተ ነው። ካርድ ለስድሰት ወራት ባካሄደው ጥናትም የተዛቡ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች በተለይም ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መዛባት ጋር ተያይዞ እያመጣው ያለው ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም ገልጿል።

እነዚህን የተዛቡ መረጃዎች የሚያሰራጩ አካላት ምንም እንኳን አንዱ ምክንያታቸው በተመልካች ብዛት የሚገኝ ገቢ ቢሆንም፣ በዋነኛነት ግን ለፖለቲካዊ አላማ፣ ለተራ ዝና እና ለግላዊ ብሽሽቅ እንዲሁም ባለማወቅም ጭምር መሆኑ በጥናቱ የተገኙ ውጤቶች ናቸው።

የተዛቡ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ከመደበኛው ጊዜ በበለጠ የሚበራከቱበት ወቅት አለ ያለው ካርድ፣ በተለይም የተቃውሞ ሰልፍ፣ ግጭቶች፣ ሃይማኖታዊ በአላት እና ፌስቲቫሎች በሚኖሩባቸው ጊዜያት የሐሰት መረጃው የሚጠናከርበት ጊዜ ነው። በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ሲኖር፣ የፖለቲካ መሪዎች የገቢ ማሰባሰቢያ ሲያደርጉ እና የሕዝብ ውሳኔዎች ሲካሄዱ እንደሆነም የካርድ ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት እንዲበዛ እና ዋጋ እንዲኖራቸው ካደረጉት ምክንያቶች መካከል፣ መንግሥት ግልፅ ባለመሆኑ እና መረጃዎች ክፍት አለመደረጋቸው ተጠቃሽ ናቸው። በተያያዘም መረጃ ክፍት የማያደርጉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተጠያቂ ባለመሆናቸው፤ የሲቪክ ማኅበራት የሚዲያ ግንዛቤ በመጨመር ዜጎች እራሳቸውን ከተዛቡ መረጃዎች እና ከጥላቻ ንግግሮች እንዲጠብቁ የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራት ባለመቻላቸውም ነው ተብሏል።

እንዲሁም የሚዲያ ተቋማት እና ጋዜጠኞች በተለያየ መልኩ የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት ለመከላከል በቂ ትኩረት ያለመስጠታቸው እና ሀቅ የማረጋገጥ ሥራ ላይ ደካማ መሆናቸው ለችግሩ እንደ ዋነኛ መንስኤነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከዛ በተጨማሪም የማኅበራዊ ሚዲያ ቅኝቶች እና አካሄዶች የዜጎችን በቂ እና ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት እና ፍላጎት እንዲስተጓጎል ያደርጋል ብለዋል።

በተጨማሪም ከወዲሁ የተደራጁ ስለመሆናቸው ምልክት የተገኘባቸው ሲሆን፣ ሐሰተኛ የሥም ማጥፋት እና የማጥላላት ዘመቻዎች እየተካሄዱ በመሆናቸው እነዚህ አሳሳቢ አካሄዶች በሁሉም ኃላፊነት በሚሰማቸው አካላት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው ይገባል። ካልሆነ ግን በምርጫው ወቅት ዜጎች በተሳሳተ መረጃ መምረጥ ለማይፈልጉት አካል ድምጻቸውን እንዲሰጡ ከማሳሰቱም በላይ በተለያዩ አካላት ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ ሊያደርጉ ይችላሉ ሲሉ በፍቃዱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here