ጃዋር መሐመድ የኢትዮጵያ ዜግነት ማግኘታቸውን አስታወቁ

0
474

በታኅሳስ ወር ውስጥ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስን መቀላቀላቸውን ያስታወቁት ጃዋር መሐመድ፣ ረቡዕ ጥር 13/2012 ለኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዜግነታቸው እንዲመለስላቸው ጠይቀዋል።

ለአዲስ ማለዳ የደረሰው ባለ ኹለት ገፅ ማመልከቻ እንደሚያስረዳው፣ ጃዋር በአሜሪካ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ በአሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጰያ ኤምባሲ ፓስፖርታቸውን ለማደስ ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ የአሜሪካ ዜግነት ማግኘታቸውን ያስረዳል። ‹‹በነበረኝ የፖለቲካ አቋም ምክንያት በጊዜው የነበረው መንግሥት ፓስፖርቴን ለማደስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ያለፈቃዴ ዜግነቴን ትቼ የአሜሪካ ዜጋ ሆኜ ነበር›› ሲል ማመልከቻው ያስረዳል።

አሁን ግን በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ ምክንያት ከሐምሌ 29/ 2010 ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የገለፁት ጃዋር፣ የሥራ ቦታቸውንም ኢትዮጵያ ውስጥ ማስደረገቻውን ተናግረዋል።
የአሜሪካን ዜግነታቸውንም ታኅሳስ 27/2012 መተዋቸውን የሚገለፅ የማረጋገጫ ደብዳቤ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ማግኘታቸውን በማመልከቻቸው ገልፀዋል። ጃዋር ሲራጅ መሐመድ በድምሩ ዘጠኝ ገፅ ማስረጃ ጋር የተያያዘ ባለ ኹለት ገጽ ማመልከቻቸውን ለዜግነት ጉዳዮች አስገብተዋል።

የጃዋር መሐመድ ጠበቃ የሆኑት ገመቹ ጉተማ፤ ጃዋር በዜግነት አዋጁ የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላታቸውን እና በዚህም መሰረት ለሚመለከተው አካል ማስገባታቸውን ገልፀዋል። ‹‹ከሕጉ አንፃር ካየነው ከኢሚግሬሽን የምንጠብቀው ምንም ነገር የለም፤ ምክንያቱም ቀድሞ ኢትዮጵያዊ የነበረ ሰው ቀጥሎ የውጪ አገር ዜጋ ሆኖ ዳግም የኢትዮጵያ ዜግነትን ለማግኘት ማሟላት ያለበትን ነገሮች አሟልተናል›› ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹አንደኛው ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሪያን ማድረግ ነው። እንዲሁም ይዞት የነበረውን የውጪ አገር ዜግነት መተው እና ዜግነቱ እንዲመለስለት ለባለሥልጣኑ ማማልከት። ስለዚህ ሥልጣን ላለው ኤጀንሲ አመልክተናል›› የሚሉት ገመቹ፣ ደንበኛቸው እነዚህን ነገሮች በሙሉ ስላሟላ እና ሕጉም የሚሰጥ ማረጋጋጫ ወይም መልስ አለ ስለማይል፣ በሕጉ ተፈፃሚነት ጃዋር ኢትዮጵያዊ ናቸው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የተጠቀሰው አዋጅ ዜግነትን መለወጥ መብት እንደሆነ የሚገልፅ ሲሆን፣ በአንቀፅ 22 ላይ ዜግነትን መልሶ ስለማግኘት ያብራራል። በአንቀፅ 23 ስር በተቀመጡት ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ስርም የዜግነት ጉዳይ ኮሚቴ የሚባል እና የባለሥልጣኑ የውጪ ጉዳይ፣ የፍትህ ሚኒስቴር፣ የፌደራል ፖሊስ እና የባለሥልጣኑ ሌላ ተወከይን የያዘ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ እንደሚቋቋም ይደነግጋል። በንዑስ አንቀፅ ኹለት (ሐ) ስርም ለዚሀ ኮሚቴ ከሚሰጡት ሥልጣኖች መካከል አንዱ ዜግነትን መልሶ ለማግኘት የሚቀርብ ማመልከቻ በአንቀጽ 22 ስር የተደነገጉትን ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላቱን ያረጋግጣል ይላል።

የኮሚቴው ሰብሳቢ እና የጃዋር መሐመድንም ማመልከቻ ለተቀበለው ለኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሙጂብ ጀማል እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አዲስ ማለዳ ኮሚቴው ውሳኔ አሳልፎ እንደሆነ ለማወቅ ለኹለት ቀናት ያደረገቸው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጃዋር መሃመድ ኦፌኮን መቀላቀላቸውን ተከትሎ የውጪ አገር ዜጋን የፖለቲካ ፓርቲ አባል ማድረግ እንደማይቻል በመግለፅ የግለሰቡን ዜግነት የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለቦርዱ እንዲያቀርብ መጠየቁ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here