የህዳሴ ግድቡ ድርድር መጨረሻ ወዴት ያመራ ይሆን?

በዓመት 15 ሺሕ 692 ጊጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የጠየቀው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዛሬውን ሥሙን ከመያዙ በፊት ‹ፕሮጀክት ኤክስ› በሚል ሥያሜ ሊገነባ መታቀዱ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ነበር ዜናው የተሰማው።

በየሳምንቱ እሁድ ጠዋት የሚታተመው ፎርቹን ጋዜጣ በፊት ገፁ ላይ ይዞ የወጣውን ዜና ያነበቡ ብዙዎች ባለማመን እና ሌሎች ስለ ፕሮጀክቱ ለማወቅ በመጓጓት ለሳምንታት መነጋገሪያ አድርገውትም ነበር። ታዲያ የዜናው ጸሐፊ ስለ ፕሮጀክቱ እንዴት እንዳወቁ እና በጊዜው ስለነበረው ስሜት ያስረዳሉ።

በጋዜጣው ቅጽ 11 ቁጥር 562 ጥር 22/ 2003 እለተ እሁድ ታትሞ የወጣው ፎርቹን ጋዜጣ ያኔ በሦስት ብር ብቻ የሚሸጥ ነበር። ተስፋለም ወልደየስ የተሰኘ ጸሐፊ የጻፈው እና ( ) በግርድፉ ሲተረጉም ‹‹የኃይል ሞገድ ቀያሪው›› በሚል ርእስ ነበር ዜናውን ያስነበበው። በወቅቱም ግንባታው ለሳሊኒ ኮንስትራክሽን መሰጠቱን እና ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት ማለትም ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከምታመነጨው ኃይል ሦስት እጥፍ ኃይል የሚያመነጨው ግድብ ግንባታ መጀመሩን የሚያበስር ነበር።

የግድቡ ግንባታ ጉዳይም በወቅቱ የኢትዮጵያ ኤሌክቲክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የቦርድ ዳይሬክተሮች እና የተወሰኑ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ብቻ የሚያውቁት ከፍተኛ ምስጢር እንደነበርም ያትታል። ግድቡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ በእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የያዙት 10 ሺሕ ሜጋ ዋት በዓመት የማመንጨት እቅድን የሚያሳካ ይሆናል ተብሎ አንደሚጠበቅም ዜናው አትቶ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜናው ከመታተሙ ከሦስት ቀናት በፊትም ሰፋፊ የኃይል ማመንጨት ሥራዎች እንደሚሠሩ እና ቢያንስ ቢያንስ ዋናውን እና ትልቁን በዚህ ዓመት እንጀምራለን ማለታቸውንም ያትታል። የጋዜጣው ምንጮችም ስለ ቀድሞው ‹ፕሮጀክት ኤክስ› ስለ አሁኑ ህዳሴ እያወሩ ነበር ብለው ማረጋገጣቸው ተመዝቧል።

ከሳሊኒ ጋርም በወቅቱ የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት ግርማ ብሩ ውል መፈረማቸውን እና የፕሮጀክቱም ሥም ወደ ሚሊኒየም ፕሮጀክት ሊቀየር እንደሚችል የጠቆመው ይህ ዜና፣ ግድቡ በአምስት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ መታመኑን አትቷል። ታዲያ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ህልፈት በኋላ ኹለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተቀያይረው ግድቡም በተባለው ጊዜ ሳይጠናቀቅ አራት ዓመት ዘግይቷል።

በመጪው ኹለት ዓመት ተኩል ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ሕዳሴ ግድቡ፣ ልእለ ኃያሏን አሜሪካን ጨምሮ የዓለማችንን ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋማትን በማሳተፍ ዓለማቀፍ አጀንዳ ከሆነም ወራት ተቆጠሩ።

ግድቡ ዛሬ
ባሳለፍነው ሳምንት ሐሙስ ጥር 28/2012 የስትራቴጂክ ጥናት ማእከል በየወሩ በሚያዘጋጀው ወርክ ሾፕ የጥር ወር ርዕስ ሆኖ የተመረጠው የህዳሴ ግድቡ እና በግድቡ ላይ የሚደረጉ ድርድሮች ነበሩ። በመድረኩ ላይም የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ስለግድቡ አጠቃላይ ይዞታ እና አሁን ስለሚገኝበት ደረጃ በሰፊው አብራርተዋል።
በዚህ መድረክ ላይም ከተለያዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት የተጋበዙ እንዲሁም በግለቸው በግድቡ እና በአባይ ወንዝ ዙሪያ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች ተጋብዘዋል፣ ተሳትፈዋልም። የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሚዲያ ሰዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም ምሁራንም ተሳታፊ ነበሩ።

ታዲያ ለግድቡ መዘግየት የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒሰትሩ ስለሺ ካስቀመጧቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን ገና ብቁ ሳይሆን ለሜካኔካል ሥራ መታጨቱ መሆኑን ይናገራሉ። ‹‹የአገራችን የሜታል ኮርፖሬሽን እንደ አሜሪካው ኮርፕስ ኦፍ ኢንጂነርስ ትልቅ ተቋም አድርጎ ለመገንባት መታሰቡ ጥፋት የለውም፤ ጥሩ ሐሳብ ነበር። ነገር ግን ኢንጂነሪንግ በፍላጎት ሳይሆን በልምድ እና በብቅቃት የሚሠራ ነው። ሜቴክ ግን ያ ልምድ አልነበረውም›› ሲሉ ወቅሰዋል።

ሜቴክን ለዚህ ሥራ መምረጥ ዋጋ አስከፍሏል ብለው የሚያምኑት ስለሺ፣ የግድቡ መዘግየት ያመጣውን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳለ ሆኖ በተጨማሪም ‹‹አሁን ያለንበት ጭቅጭቅ ውስጥም አንገባም ነበር›› ብለዋል። ያለፈውን ለማሻሻል አሁን በከፍተኛ ፍጥነት ግንባታው እየተከናወነ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ አሁንም ግድቡን በቶሎ ወደ ሥራ ማስገባት አማራጭ የለውም ብለዋል።
ስለሺ አክለውም ግድቡ የሦስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የጋራ ጥረት ውጤት ነው ብለዋል። ‹‹ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል የማመንጨት ታላቅ የሚባል ርዕይ ነበር። አቶ መለስ ጀምረውታል፣ በአቶ ኃይለማርያም ቀጥሏል፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይቀጥላል›› ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫነት ዋነኛ ሚናው ሲሆን፣ በተጓዳኝም ለቱሪዝም አገልግሎት የሚያገለግል በመሆኑ በተለያየ ጊዜ በዓለም ትልቁ ግድብ እየተባለ መነሳቱ ትክክል ያለመሆኑን ያስረዳሉ።
‹‹ከኻያ አንድ በመቶ በላይ የሚሆነው ዜጋ ከድህነት በታች የሚኖርባት ኢትዮጵያ እንደ አባይ ያሉ ተፋሰሶችን ይዛ አታልማ ማለት አግባብ ያልሆነ ነው›› ይላሉ። በየዓመቱ ኹለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን አዲስ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፈላጊ የሚፈጠርባት ኢትዮጵያ፣ የውሃ ፍላጎቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚጨምር ይጠቅሳሉ። አክለውም ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት አገር እንደመሆኗ የውሃ ፍላጎቷን የምታሟላው ከዝናብ በምታገኘው ውሃ ነው ይላሉ።

‹‹በዓለም ላይ የንፁህ ውሃ እጥረት ወደ ፊት ለተለያዩ ግጭቶች ይዳርጋል የሚባለውን እኔ አልስማማበትም። ምክንያቱም በርካሽ ቴክኖሎጂ የባህር ውሃን በማጣራት ለመጠጥም ሆነ ለእርሻ ማዋል ተችሏል›› ያሉት ስለሺ ‹‹ለዚህም እስራኤል እና ራሷም ግብፅ አሌክሳንድሪያን ጨምሮ አዳዲስ ለምታቋቁማቸው ከተሞቿ ውሃ እያቀረበች ነው። የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያ ደግሞ ተፋሰሶቿ ብቻ ናቸው ያሏት›› ብለዋል።

የሱዳን ሮዛሪየስ ስናር እና መሮዌ ግድቦች በየዓመቱ የሚያመነጩትን ኃይል በ2 ሺሕ 657 ጊጋ ዋት ያሳድጋል ተበሎ የሚጠበቀው ይህን ግድብ፣ የሱዳን መንግሥት ከመገደብ ባሻገር ገንዘብ አውጥተው ሊደግፉት የሚገባ ነፃ ስጦታ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ሱዳን በየዓመቱ የሚደርስባትን የጎርፍ አደጋም ያስቀርላታል። ይህም በተደጋጋሚ ሲገለፅ የቆየ ጥቅም ነው። ‹‹ሱዳን ኹለት ሦስት ግድብ የመጨመር እቅድ ነበራት። ነገር ግን ህዳሴው ከተገነባ በኋላ ሌላ ግድብ መገንባት አያስፈልጋትም።››

የሱዳኑ ሮዛሪይስ ግድብ በአምስት ዓመት ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ 1958 ነበር ሥራ የጀመረው። ግድቡ ቢበዛ እስከ 68 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ያለው ሲሆን፣ 29 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ ተንጣሎ ኃይል ለማመንጨት ይውላል። መሮዌ ሃይ ግድብም የኃይል ማመንጨትን ጨምሮ የተለያዩ አገልገሎቶችን የሚሰጥ እና ቢባዛ 67 ሜትር ከፍታ ድረስ የሚሞላ እና በ 2001 ተመርቆ ሥራ የጀመረ ግድብ ነው። ሌላው የመስኖ ግድብ የሆነው ስናር ግድብም እንዲሁ በአባይ ወንዝ ላይ የተሠራ እና ቢበዛ 40 ሜትር የሚረዝም እንዲሁም ሦስት ነጥብ 25 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ግድብ ነው።

ስለሺ እንደሚሉትም የህዳሴው ግድብ መገንባት ሱዳን በአባይ ወንዝ ላይ የገነባቻቸው እነዚህ ግድቦች በየዓመቱ ለማፅዳት የምታወጣውን 60 ሚሊዮን ዶላር ከማዳን ባሻገር፣ የተስተካከለ የውሃ ፍሰት የሚሰጥ እና በድርቅ ወቅትም ከህዳሴ የሚለቀቀው ውሃ ፍሰቱን ያስተካክላል ሲሉ አስረድተዋል።

ስለ ሙሌቱ ሲያብራሩም፣ ለአባይ ወንዝ ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 23 ያለው ወቅት የቅድመ ጎርፍ ወቅት ሲሆን፤ ከሐምሌ 24 እስከ ነሐሴ 19 ያለው አንድ ወር ደግሞ የጎርፍ ወቅት ነው። ድኅረ ጎርፍ የሚባለው ወቅት ከነሐሴ 20 እስከ መስከረም 19 ያለው ሲሆን፣ የግድቡ ዋና የሙሌት ሰዓታትም እነዚህ ሦስት ወራት መሆናቸውን ኢንጂነር ስለሺ ይናገራሉ።

ግብጽ ያቀረበችው ፍትሐዊ ያልሆነ ጥያቄ ተብሎ በኢትዮጵያዊያን በኩል የተገለፀው፣ ግድቡ በሚሞላበት ወቅት ኢትዮጵያ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ለመልቀቅ ማስተማመኛ እንድትሰጥ መጠየቋን ነው። ኢንጂነር ስለሺ እንደሚሉት የ104 ዓመት የአባይ ታሪክ እንደሚያስረዳው፣ የወንዙ ፍሰት ከፍተኛ የሆነ የመጠን ልዩነት ያመጣል። በ1913 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር፣ 21 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ብቻ የተመዘገበ ሲሆን፣ በ 1984ም 29.4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በመሆን ዝቅተኛ ሆኖ ተመዝግቧል። እንዲሁም እ.ኤ.አ 1929 ትልቁ ፍሰት የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም 69.1 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሆኖ የተመዘገበበት ነበር።

ግብፅ ያቀረበቸውን 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ዓመታዊ ፍሰት ፍትሐዊ አይደለም ያሉት ስለሺ፣ ቢያንስ 15 በመቶ ያክል የአባይ ወንዝ ውሃ ከ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በታች የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩን ይገልፃሉ። ግበጽ ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት 40 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ እየለቀቀች ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት በአማካኝ ከዘጠኝ እስከ 14 ዓመት የሚፈጅበት ሲሆን፣ አንዳንድ ዓመቶች ላይ 40 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ለመልቀቅ የማይቻልበት ወቅት ይኖራል። ይህም ኃይል የማመንጨት እድልን የሚያሳጣ እና ኪሳራም የሚስከትል ነው።

‹‹ቋሚ ልቀትን መጠየቃቸው ከዚህ ቀደም ድርድሩ ከሚደረግባቸው መርሆዎች ያፈነገጠ እንዲሁም የወንዙን ተቀያያሪ ጠባይ ከግምት ውስጥ ያልከተተ ነው›› ሲሉ ስለሺ ተናግረዋል። ሌላው የግብፅ ፍትሐዊ ያልሆነ ጥያቄ አስዋን ሃይ ዳም ከ165 ሜትር በታች እንዳይጎድል ማስተማማኛ እንድትሰጥ መጠየቋ ነው። ይህም ኢትዮጵያ የናስር ሰው ሠራሽ ሀይቅ በፊት ሱዳን የምትጠቀመውን ውሃ እና አስዋን ሃይቅ ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎች በማትቆጣጣርበት ሁኔታ፣ ይህን መጠየቋ ጥያቄውን ኢ ፍትሐዊ ያደርገዋል ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በዘህ መሰረት በስድስት ነጥቦች ላይ ያተኮሩ ድርድሮች ተካሂደዋል። ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ፣ የሕግ ማእፎች ላይ፣ የትብብር እና የመረጃ ልውውጥ ላይ እንዲሁም የግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ አትኩሮት ይደረጋል።

ሌሎች ኹለት ነጥቦች ላይ ማለትም የግድቡ ደኅንነት እና የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ቀጣይ ውይይቶች እንደሚደረጉም ታውቋል።
ድርድሮቹም በተለይ የድርቅ ጊዜ እንዴት ማቻቻል፣ የተራዘመ የድረው ጊዜ እና የተራዘመ ደረቅ ዓመታት ላይ አተኩሯል። ይህም የግድቡ ሙሌት፣ ዓመታዊ እንዲሁም የእለት ተእለት እንቅስቃሴውን በረጅም ጊዜ ከግምት ውስጥ የከተተ ነው።

አራት ክፍሎች ያሉትን የተሟላውን የስምምነት ሰነድ ማዘጋጀት፣ በመጪው ረቡዕ ወይም ሐሙስ ውይይቶችን በማድረግ ስምምነቶችን መፈረም እንዲሁም የቴክኒካል ኮሚቴ ማቋቋም ላይ ስምምነቶች ተደርሰዋል።

በሦስቱ አገራት መካከል ያለው ስምምነት ሳይጠናቀቅ ዝርዝሩን ላለመዘገብ መገናኛ ብዙኀን ቃል በገቡበት የኹለተኛው ክፈለ ጊዜ፣ በድርድር ሂደት እና በመጨረሻ የስምምነት ነጥቦች ላይ ሰፊ እና የሰላ ውይይት ተደርጓል። አዲስ ማለዳም ይህንን ክፍለ ጊዜ በቻተም ሃውስ ሕጎች መሰረት ከስምምነቱ በኋላ ለማስነበብ ቃል ትገባለች።

ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት፣ በቴክኒካል ቡድን አባላቱ መካከል እንኳን ያለመግባባቶች ያሉ ሲሆን ይህም የድርድሩ መሪዎች የቴክኒክ አስተያየቶችን በተደጋጋሚ ወደ ጎን በማለታቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። የድርቅ ትርጉም 37 ቢሲኤም ላይ መውደቁ ኢትዮጵያ በቀደመው ጊዜ ይዛው የቆየቸው 30 ቢሲኤምን ወደ ግብፅ 40 ቢሲኤም የሚያቀርብ ወደ ፊትም በአባይ ላይ ለሚሠሩ ልማቶች እንቅፋት የሚፈጥር ነው ይላሉ።

ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ደመቀ አጭሶ፣ ድርድሩ እስከ አሁን የሄደበት መንገድ መጥፎ አይደለም ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

‹‹ግብፆች እያሸነፉ ነው፣ ህዳሴ ግድብ ተሸጧል፣ የሚሉት ውዥንብር መፍጠሪያ አጀንዳ እስካልሆነ ድረስ የህዳሴ ግድብ አልቆ ለማየት እና በናይል ተፋሰስ ላይ ረጅም ዓመታት የቆየን የግብፅ የበላይነት ቀልብሶ የኢትዮጵያን ሐሳብ ቶሎ እውን የሚያደርግ ነው›› ብለዋል።

በቀጣይ ሳምንት የሦስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች በዋሽንግትን ተገናኝተው እንደሚመክሩ እና ስምምነት ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉም ስለሺ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here