በፖሊስ ህይወታቸው ያለፈው ሚካኤል እና ሚሊዮን እነማን ነበሩ?

0
909

ረቡዕ ከእኩሌ ሌሊት በኋላ በተለምዶ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቅድስት አርሴማ እና ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ግንባታ ጋር በተያያዘ ለጥር 27/2012 አጥቢያ ላይ ግርግር ተፈጠረ። ችግር የተፈጠረው በቤተክርስትያኒቱ በነበሩ ምዕመናን እና በጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶች መካከል ነበር። በተፈጠረው ግርግር መካከልም ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት የአካባቢው ኹለት ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ። ቁጥራቸው ያልተገለጸ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም፣ ክስተቱ ከተፈጠረ አንድ ቀናት በኋላ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በተፈጠረው ክስተት ሚካኤል ፋኖስ እና ሚሊዮን ድንበሩ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ሕይወታቸው አጥተዋል። ሐሙስ ጥር 28/2012 ሥርዓት ቀብራቸው ገርጂ በሚገኘው ቅዱሰ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል። የፍትኀት ሥነ ስርዓቱ በቦሌ መድኃኒዓለም ቤተክርስትያን የተከናወነ ሲሆን፣ በርካታ የኢትዮጵያ ኦተርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመንና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተለያየ መንፈሳዊ ዝማሬዎችን እያሰሙ ነው የኹለቱን ወጣቶች አስክሬን ወደ ቀብር ስፍራው የሸኙት።
ላዘኑት መጽናናትን የምትመኘው አዲሰ ማለዳም የኹለቱን ወጣቶች የቅርብ ቤተሰቦች አነጋግራለች።

ስለ ሚካኤል ፋኖስ
ሚካኤል ፋኖስ የተወለደው አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ሥሙ 22 ተብሎ በሚጠራው ሰፈር በ1986 ነሐሴ 13 ነበር። አሳዳጊ አጎቱ እሱባለሁ ካሳሁን ስለ ሚካኤል ሲናገሩም ፀባዩ ጥሩ የሚባል፣ ከሰው ተግባቢ፣ ሰው ላይ የማይደርስ እንዲሁም ሰው ተጎድቶ ማየት የማይወድ ነበር ሲሉ ገልጸውታል። እንደውም በዚህ ጸባዩ ነው ‹‹ወንድሜ በፖሊስ እየተደበደበ ነው›› ብሎ እዛው ቤተክርስትያን ውስጥ ግርግር ወደ ነበረበት ቦታ ሲሄድ፣ ከየት እንደመጡ በማያውቃቸው የጸጥታ ኃይሎች በጥይት የተመታው።
ሚካኤል ይህ ከሆነ በኋላ ልክ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከ30 ገደማ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል ሲሉ፣ እምባ በተናነቀው ድምጻቸው ለአዲስ ማለዳ የሆነውን አብራርተዋል።

‹‹ሚካኤል ለእናቱ የመጀመሪያ ልጅ ነው። እራሱንም ቤተሰቡንም የሚያስተዳድረው በሾፌርነት ሙያ ነበር።›› ያሉት አጎቱ፣ በጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ሕይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ፣ ምሽት ከ6 ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት አብረው እንደነበሩም አንስተዋል። ‹‹ከዛ በኋላ ነው የተገደለው።›› በማለትም የነበረውን ሁኔታ አጎቱ በሃዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ያስረዳሉ።
ሚካኤል ሕይወቱ በማለፉ ቤተሰቦቹ በእጅጉ ልባቸው ተሰተብሯል፤ አዝነዋል። ድንገተኛ ያልተጠበቀው የወጣቱ ሞት ዘመዱንና ጓደኞቹንም በእጅጉ ያስደነገጠ ነው። በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪም የተፈጸመው ግድያና የጸጥታ ኃይሎች ድርጊት ትክክል እንዳልነበር ሲያወግዙም ተሰምተዋል።

የሐዘኑን ጥልቀትና ክብደት ለማስረዳት ቃላት ያጠራቸው እሱባለው፣ ያም ሆኖ በቤተክርስትያን በኩል የተደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው የአዲስ አበባ ነዋሪም ቀብሩ ላይ በመገኘቱ፣ በጥቅሉም የነበረው ሁኔታ ያፅናና እንደነበር ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ሁኔታው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ፣ ለማስረዳትም እንደሚቸግራቸው በሐዘን በተሰበረ አንደበት ተናግረው፣ ‹‹እኔ በበኩሌ ሚኪያስ በሕይወት አለ ብዬ ነው የማምነው›› ብለዋል።

በእለቱ ስለተፈጠረው ክስተት የሚያብራሩት እሱባለው፣ እየታነጸ ያለው የቅድስት አርሴማ እና የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን አዲስ ስለነበር እሱን በማስመልከት ምሽት ላይ መርሐ ግብር ነበረ ሲሉ ያስታውሳሉ።

‹‹በዚህም ካህናትን ራት እያበላን፣ ምሽቱን በዝማሬ እያሳለፍን በነበርንበት ወቅት ድንገት ከየት መጡ ያላልናቸው የጸጥታ ኃይሎች እንደ አልሸባብ አስለቃሽ ጭስ ተኮሱብን። አስለቃሽ ጭሱ አይደለም የራሴ በሚባል ወገን ይቅርና በሌላ ጠላት ላይ እንኳ ሊፈጸም የማይገባ ነው›› ሲሉ በቁጭት በማስታወስ በቦታውም የነበሩ እናቶች እንዲሁም ሕጻናት በማንሳት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
ከጸጥታ አስከባሪም ሆነ እንደ ኢትዮጵያዊ ከዜጋ የማይጠበቅ ድርጊት ነው የተከናወነው የሚሉት የሚካኤል አጎት፣ ‹‹እንዲህ ዓይነት ነገር ይፈጠራል ብለን በፍጹም አላሰብንም ነበር። የትኛውም መንግሥት ቤተክርስትያንን ደፍሮ አያውቅም። ቤተክርስትያንን የናቀ መንግሥት ሕዝብን ሊያከብር ይችላል እንዴ?›› ሲሉ በሐዘንና ቁጭት ስሜት ውስጥ ሆነው ጠይቀዋል። ቀጠል አድርገውም ‹‹ይህንንማ ብናውቅ እኛም ራሳችንን እንከላከል ነበር።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹እኛ ለእውነተኛ ሥራ ለፅድቅ ሥራ ነበር የቆምነው። ፖሊሶቹ ሲመጡም በሕግ አምላክ ስንላቸው ‹ሌባ ሁላ! ያልተፈቀደ ቦታ ላይ ሆነህ! ውጣ!› እያሉን ነበር። አንድ ፖሊስ ያለ መንግሥት ትዕዛዝ ምንም አያደርግም፣ ሊያደርግም አይችልም። በመሆኑንም ያዘዛቸው አካል እንዳለ እናስባለን ሲሉም ተናግረዋል። ድርጊቱም ኢ ሰብአዊ ድርጊት ነው። በቦታው ላይ ሕፃናት፣ አባቶች፣ እናቶች እና አረጋውያንም ነበሩ። ታዲያ ሰው ወገኑ ላይ እንዴት አስለቃሽ ጭስ እና መሣሪያ ይተኩሳል? ይላሉ የሚካኤል አሳዳጊ።

ስለ ቤተሰቡ እጣ ፈንታ በተመለከተም፣ ከዚህ በኋላ ቤተሰቡ ሊቸገር ይችላል ያሉ ሲሆን የዚህ ምክንያቱም እናቱ ሥራ የሌላቸው መሆናቸው፣ ኹለት ታናናሽ ወንድሞች እና አንድ እህቱ ደግሞ ገና ተማሪዎች ናቸው በማለት ሚካኤል በቤተሰብ ውስጥ የነበረበትን ኃላፊነት ጠቅሰዋል። ‹‹የጸጥታ ኃይሎቹ የገደሉት የአንድን ሰው ሕይወት ብቻ አይደለም። የአራት ሰዎችን እንጂ›› በማለት አክለዋል።

ሚካኤል ቤተሰቡን የሚረዳ፣ እናቱን ‹አይዞሽ!› እያለ የሚደግፋቸውና ለነገው ብዙ ርዕይ የነበረው እንደሆነም አጎቱ እሱባለው ያስረዳሉ።

ሚሊዮን ድንበሩ
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሟች ሚሊዮን ድንበሩ አብሮ አደግ ስለ ሚሊዮን እና በእለቱ ስለተፈጠረው ክስተት ለአዲስ ማለዳ እንዲህ ነግረዋታል።
ሚሊዮን የ42 ዓመት ጎልማሳ ነበር። ቤተሰቡን፣ አቅመ ደካማ እናቱን የሚጦር፣ በጸባዩም ቢሆን ጥሩ ጸባይ ያለው የቤተሰብ ኃላፊ ነበር፤ ለዚህም ብዙዎች ምስክር ናቸው ይላሉ።
ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ሚሊዮን፣ በታላቅነት ቤተሰቡን ለመርዳት በሹፍርና ሙያ የእራሱን እንዲሁም የቤተሰቡን ሕይወት ለመምራት ሲል የሚተጋ ሰው ነበርም ብለዋል።
የጸጥታ ኃይሎች ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት በኋላ በተለምዶ 24 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የመጡ መሆኑን በማስረዳት፣ በተፈጠረው ግርግርና ግጭት ከጸጥታ ኃይል በተተኮሰ ጥይት የሟች ሚሊዮን ድንበሩ ሕይወት ሊጠፋ እንደቻለ ይገልጻሉ። ይህ ድርጊት ከመፈጸሙ ኹለት ቀናት በፊት የጸጥታ ኃይሎች ቤተክርስቲያኑ በሚገነባበት ቦታ ላይ መምጣቸውን የሚናገሩት የሟች ሚሊዮን አብሮ አደግ፣ በድጋሚ መጥተው ይህን ያደርጋሉ ብለው እንዳልጠበቁ ነው ያስረዱት።

ይሁን እንጂ የጸጥታ ኃይሎቹ በሌሊት በመምጣት እየተሠራ የነበረውን ቤተክርስቲያን አፍርሰዋል፣ የነበሩት ሰዎችንም ደብድበዋል፣ የአስለቃሽ ጭስ በአካባቢው ላይ ተኩሰዋል ሲሉ ነገሩን ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስረዳሉ። በዚህም ሳቢያ ብዙ ሰዎች በአካባቢው ወደ ነበረው ወንዝ ውስጥ በመግባት ጉዳት ሲገጥማቸው ኹለት ሰዎች ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ሕይወታቸው አልፏል። ‹‹ከሞቱት ውስጥ ደግሞ ወንድማችን ሚሊዮን ይገኝበታል›› ሲሉም የሟች ሚሊዮን አብሮ አደግ ስለ ነበረው ነገር በተሰበረ ስሜት ያስታውሳሉ።

ወደ አካባቢው ስለመጡት የጸጥታ ኃይሎች ሲናገሩም፣ ቁጥራቸው ብዙ የሚባል ነበር ብለዋል። በየመንደሩ ውስጥ በመግባት በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋልም ይላሉ፣ የሚሊዮን ድንበሩ አብሮ አደግ።

የተፈጠረው ነገር በመነጋገር ሊፈታ የሚችል ነበር የሚሉት እኚህ ግለሰብ፣ ‹‹ይህ ድርጊት ይፈጸማል የሚል ሐሳብ በማንም ዘንድ አልነበረም። ከዛ በተጨማሪም ወንድማችን ሚሊዮን ይሞታል ብለን አልገመትንም። ይህ ለእኛ ዱቡ እዳ ነው።›› በማለትም የተፈጠረውን ነገር አስታውሰዋል።

እሳቸውም የሚካኤልን አጎት ሐሰብ ይጋራሉ። ሐዘኑ ከባድ መሆኑንም አንስተው ‹‹በቤተክርስትያን የነበረው ሥርዓት፣ ሕዝቡ እኛን ለማፅናናት ከጎናችን በመቆሙ ሃዘኑን ለመቋቋም ብርታት ይሆኖናል እንጂ፣ በቤት ውስጥ ያለው ሐዘን በቃላት የሚገለፅ አይደለም›› ሲሉ የሐዘኑን ጥልቀት ለማስረዳት ሞክረዋል።

ቤተክርስትያኑ ይሠራበታል የተባለው ቦታ ከ20 ዓመት በላይ ዝም ብሎ ታጥሮ የተቀመጠ እንደነበር የሚያነሱት ግለሰቡ፤ ‹‹እኛም ቦታው እንዲፈቀድለን የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በተደጋጋሚ ሄደናል። የመሬት ጉዳይ በቀላሉ እንዲህ ቶሎ ምላሽ የሚገኝለት ባለመሆኑ እንጂ እየተንቀሳቀስን ባለንበት ወቅት ይህ ድርጊት መፈፀሙ አሳዝኖናል›› ሲሉ የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል።
አክለውም እንዲህ ሲሉ ይቀጥላሉ፤ ‹‹የተፈጸመው ድርጊት አንባገነንነት ነው። አገሪቱ ብዙ አዛዥ እንዳላት ነው የሚያሳየው። ይህ ውንድብና እና ኢ ሰብኣዊ ተግባር ነው።›› ሲሉም ስለ ደረሰባቸው ነገር ለአዲሰ ማለዳ አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ
የአዲሰ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በተለምዶ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከቤተክርስትያን ግንባታ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ስለ ማዋላቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል። በመግለጫው ላይ አያይዘውም የሃይማኖት ተቋሙ የተገነባበት ቦታ ተገቢ አለመሆኑን አስታውቀዋል።
ምክትል ከንቲባው የጸጥታ ኃይሎች በሌሊት ቤተክርስትያኑን ለማፍረስ መኬዱ ተገቢ ባለመሆኑ ትእዛዝ የሰጠው አካል ላይ ማጣራት እየተደረገ እንደሆነና ተገቢው እርምጃም እንደሚወሰድ አስታውቀዋል። አያይዘውም አስተዳደሩ ጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሆነና ከጥፋቱ ጋር በተያያዘ የተደራጁ መረጃዎች እየተገኙ ነው ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ያለው የጠበቀ ግኑኝነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመናገርም፣ ለተጎጂ ቤተሰቦችን የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
በዚህም የሟቾች ቤተሰቦችን ለማጽናናት ወደ አካባቢው ሄደዋል። ምክትል ከንቲባው ወደ ሚካኤል ቤተሰቦች በማቅናት ለማፅናናት ቢሞክሩም፣ ከአካባቢው ተቃውሞ እንደገጠማቸውና ቤተሰቦቹንም ምንም ሳያናግሩ ገብተው ብቻ እንደወጡ በአካባቢ ነበርኩ ያሉ የዐይን እማኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በበኩላቸው በተለምዶ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ሳቢያ በጠፋው የኹለት ሰዎች ሕይወት የተሰማቸውን ሐዘን ገልፀዋል።

ጉዳዮችን በውይይትና በሰከነ መንፈስ መፍታት ይቻል ነበር ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የተፈጠረው ችግር ተገቢ ያልሆነ እና መፈጠር የሌለበት እንደሆነም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መናገራቸውም አይዘነጋም።

ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጉዳዩን አጣርተው እንዲያሳውቁና ወንጀለኞችንም ለሕግ እንዲያቀርቡ በመጠየቅ የወንጀል ምርመራ የማጣራት ሂደቱን በተመለከተም ዝርዝር ሪፖርት ለሕዝቡ ይፋ እንዲሆን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ቅዱስ ፓትርያሪኩ ጨምረውም እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በሚፈጠርበት ጊዜ የግራ ቀኝ ወገኖች በሰከነና በሠለጠነ መንገድ ችግሩን በውይይት መፍታት ይገባቸዋል። ወደ ኃይል እርምጃ መገባቱና የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ቤተክርስትያኒቱን በእጅጉ እንድታዝን አድርጓታል ሲሉም ነው የገለፁት።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here