መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየተዘነጋው የሕጻናት ዓለም - በጉዲፈቻ መነጽር

የተዘነጋው የሕጻናት ዓለም – በጉዲፈቻ መነጽር

ምርጫ ካርድ ወስደው ለፓርቲዎች ድምጽ የመስጠት እድሜ ላይ አልደረሱም። እንደ ብሔር ‹ተጨቁነናል› ብሎ የሚሟገትላቸው፣ እንደ ጾታ ‹መብታችን ይከበር› ብሎ የሚጮኽላቸው አክቲቪስት ነን ባይ ተወካይ የላቸውም። የጣሏቸው አዋቂዎች ሆነው ድምጽ እንዲያሰሙላቸው የሚጠበቁትም እነዛው አዋቂ የተባሉ ሰዎች ናቸው። መንግሥትም፣ ማኅበረሰብና አገርም የሕጻናትን ነገር ከስሩ መፍትሔ ሳይሰጡ በወጣት ላይ ጩኸታቸውን ተያይዘውታል።
የተተዉ፣ የተረሱ፣ የተዘነጉና የእኔ ናችሁ ባይ ያጡ ሕጻናት ደግሞ ከቆሻሻ ገንዳ፣ ከየሜዳውና በየሆስፒታሉ ዛሬም ይገኛሉ። የሚከፋው ደግሞ የአካል ጉድለትና የጤና መታወቅ ሲኖርባቸው፣ ዓለም ጭራሹን ትጨክነባቸውና ትገፋቸዋለች። ከዚህ ሁሉ የሚብሰው ደግሞ የሚመለከታቸው የተባሉ የመንግሥት አካላት ሳይቀር ጠያቂ በሌለበት ቸልታ ዋሻቸው መሆኑ ነው።
ይህ ሁሉ እውነት በኢትዮጵያ ምድር ተወልደው በሚጣሉና በተለያየ ምክንያት ያለ ወላጅና አሳዳጊ የሚቀሩ ልጆች ሕይወት ነው። ይህን በሚመለከት፤ የውጪ አገር ጉዲፈቻ መቅረትና በአገር ውስጥ ያለው የጉዲፈቻ አሰጣጥ ያለበትን ደረጃ፣ የባለሙያዎችን አስተያየት እንዲሁም ተያያዥ ነጥቦችን በማንሳት፣ የሕጻናት ክብካቤ ባለሞያዎችን፣ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት፣ ባለታሪኮችና በጎ አድራጎዎችን በማነጋገር የአዲስ ማለዳዋ ሊደያ ተስፋዬ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

ወይንሸት ከበደ (ሥማቸው የተቀየረ) ይሞቅልኛል ይደምቅልኛል ብለው የመሠረቱት ትዳር ሳይቆይ በልጅ ማጣት ምክንያት ፈርሶባቸዋል። የተሰማቸውን ሐዘን እንዲከርምባቸው፣ በትዳር አጋራቸው መተዋቸው ልባቸውን ሰብሮ ለኑሮአቸው ሸክም እንዲሆንባቸው አልፈቀዱም። ከወዳጅ ቤተሰብ ተመካክረው ወደ አዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ አቀኑ።

አዲስ ማለዳ እኚህን እናት ያገኘቻቸው በጉዲፈቻ ዙሪያ ምን እየተሠራ ነው ብላ ባለሞያዎችን ለማናገር ወደ ቢሮው ባቀናች ወቅት ነው። ወይንሸትም ‹‹ልጅ ለመውሰድ ምን ማድረግ አለብኝ፤ አማክሩኝ›› ሲሉ በመጠየቅ፣ አስፈላጊውን ነገር ከተረዱ በኋላ ማመልከቻቸውን አስገቡ። ‹‹ልጄ ብዬ የማሳድጋት፣ ነፍስ ያላወቀች ሴት ልጅ ይሰጠኝ›› ሲሉም መጠይቁን ሞሉ።
‹‹ልጅ መውለድ እንደማልችል የተረዳሁ ጊዜ ብዙ አዝኜ ነበር። ግን ደግሞ እግዚአብሔር በዚህ መልክ እንዳሳድግ ፈቅዶና ፈልጎ ቢሆንስ አልኩኝ። የቅርብ ጓደኛዬም ተመሳሳይ ነገር ገጥሟት ልጅ ወስዳለች። ከእርሷ ጋር ስንመካከርም በሰጠችኝ ሐሳብ ነው ወዲህ የመጣሁት›› ሲሉ አስረድተዋል።

እንደ ወይንሸት ያለ የሕይወት አጋጣሚ የደረሰባቸው የአባትና የእናት ወግ ለማየት የሚናፍቁ ጥንዶች አሉ። ቀዳዳና ክፍተቴን ይሞላል ያሉት የልጅ ጣዕም በየቤትና በየልባቸው እንዲገባ አልታደልንም ያሉ ሰዎች፣ በአንጻሩ የልጅን ጻጋ ታድለው ለማሳደግ የተቸገሩ ወይም በሌላ ምክንያት ስጦታቸውን ለመተው በተገደዱ ሰዎች ይደፈናል። ውሉና ቅብብሉም በእነዚህ ወገኖች መካከል ይደረጋል።
አንድ ባለታሪክ እንጨምር። የምሥራች [ሥማቸው የተቀየረ] የሦስት ሴት ልጆች እናት ናቸው። ከሦስቱ ሴት ልጆቻቸው በኋላ መጨረሻ ላይ አንድ ወንድ ልጅ ወልደው ነበር። ነገር ግን በሕይወት አልቆየላቸውም። ልጅ አለማግኘትም ሆነ የወለዱትን ማጣት ያላቸውን ሕመም የደረሰበት ያውቃልና፣ በእርሳቸውና በትዳር አጋራቸው ሕይወት ተመሳሳይ ከባድ ሕመም አለፈ።

ከሐዘኑ ሳይወጡ ሕይወቱ ላለፈው ልጃቸው የአርባ ቀን መታሰቢያን ሲያስቡ ሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ እንዲሆን ፈለጉ። ባለቤታቸውም በዚህ ሐሳብ ስለተስማሙ ወደ ስለእናት በጎ አድራት ማኅበር አቀኑ። የልጃቸው የአርባ ቀን መታሰቢያ በዛ ሲያደርጉ፣ ልጅ ሊወስዱና ሊያሳድጉ እንደሚችሉ ተረዱ። ወንድ ልጃቸውንም ከድርጅቱ ተረከቡ።

‹‹ልጄ ነው። አብዝቼ በእጅጉ ነው የምወደው። እኔንም ባለቤቴንም በእጅጉ ደስ አሰኝቶናል። አሁን ስላጣነው ልጅ አናነሳም።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እንዲህ ያሉ ጥቂት የማይባሉ ታሪኮችን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሁሉ ግን ልጅን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ከሚፈልጉና ሊወስዱ ፈቃደኛ ከሆኑ ሰዎች አንጻር የሚታይ ነው። ሕጻናቱስ?

ስለ ሕጻናት
በስለእናት በጎ አድራት ድርጅት የፕሮግራም ክፍል ኃላፊ ናቸው፤ ሙሉጌታ በቀለ። 12 ዓመታት ገደማ ቀጥታ ልጆችን በሚመለከት የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል። ስለ ሕጻናት ሲናገሩ ትኩረት የሚሻና መዘናጋት የሚታይበት ጉዳይ እንደሆነ አጥብቀው ገልጸዋል።

ምክንያቱም በኢትዮጵያ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕጻናት የሚንከባከብና የሚያሳድግ ወላጅ የላቸውም። ዋና ዋና በሚባሉ ከተሞች ጎዳና ተዳዳሪ ሆነው የሚኖሩ ሕጻናት ቁጥርም ከፍተኛ ነው። የጉልበት ብዝበዛን ጨምሮ የተለያየ ጉዳትና ችግር የሚደርስባቸው ልጆች ጥቂት አይደሉም። ሙሉጌታ የስታትስቲክ ኤጀንሲን ዘገባ ጠቅሰው እንደገለጹት፣ በ2007 በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ኹለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት ከእናቶቻቸው ጋር ብቻ ሲኖሩ የአባት ፍቅር አያገኙም። 600 ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ ከአባቶቻቸው ጋር ብቻ የሚኖሩ ናቸው።

የኢፌዴሪ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የ2011 በጀት አፈጻጸም የ11 ወራት ክንውኖችን ይፋ ባደረገበት ሰነድ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ከተባሉ ሕጻናት ውስጥ ለ1 ሚሊዮን 97 ሺሕ 279 ለሚሆኑት ድጋፍና ክብካቤ በመስጠት ቁጥሩን ለመቀነስ እቅድ ይዞ እንደነበር ሰፍሯል። እነዚህ በእቅድ ውስጥ የተካተቱ ልጆች የተወሰኑ የሚባሉ ከሆነ፣ በችግር ውስጥ ያሉ ልጆች በጠቅላላው ምን ያህል ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም።

ሙሉጌታ አያይዘው ባነሱት ነጥብ፣ መንግሥት ብዙውን እንቅስቃሴውን ከፖለቲከ ትርፍ ጋር ያሰላዋል። ስለዚህም ትኩረት የሚሰጠው ከ18 ዓመት በላይ ላሉ ዜጎች ነው። የሕጻናትን መብት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጀምሮ በእኔነት ስሜት ተከታትለው የሚሠሩት በጣት የሚቆጠሩ ተቋማትና ሰዎች ናቸው። ‹‹የሕጻናትን ጉዳይ በሚመለከት ግፊት የሚፈጥር ካለ ለራሱ ጥቅም ነው ተብሎ ይታሰባል። እናም ከእኛ በላይ ለልጆች የሚያስብላቸው የለም በሚል መታበይ ምክንያት ለሕጻናት መብት የሚታገሉትን ወደታች ያደርጋሉ [በመንግሥት ተቋማት የሚሠሩት]›› ሲሉ ለዓመታት በቆዩበት የልጆች ጉዳይ ያለውን ፈተና ያስረዳሉ።

ጉዲፈቻ በኢትዮጵያ
ረሂላ አባስ ‹‹የጉዲፈቻ አሠራር በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሑፍ፤ በኢትዮጵያ ስለጉዲፈቻ አጀማመር መረጃዎችን አካፍለዋል። በዚህም መሠረት ‹ጉዲፈቻ› የሚለው ቃል ከኦሮምኛ ቋንቋ በቀጥታ ወደ አማርኛ የተወሰደ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ፍቺውም ‹‹ጉዲፈቻ ከሌላ አብራክ የተገኘን ልጅ ከሌላ ሰው የተወለደ መሆኑን አምኖና ተቀብሎ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቱን ጠብቆ እንደ ገዛ ልጅ አድርጎ ማሳደግ ነው።›› ሲሉ አስቀምጠዋል። ታድያ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላትም እንደ ‹ጡት ልጅ› ያለ ተመሳሳይ ስርዓት የሚገኝ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለጉዳዩ እንግዳ እንዳልሆነች ያሳያል።

ረሂላ ለዚህ ስርዓት ሃይማኖታዊ መሠረቶችን በጽሑፋቸው ጠቅሰዋል። አንደኛው በአይሁድና በክርስትና ሃይማኖቶች ታሪክ ውስጥ የሚጠቀሰው የነቢዩ ሙሴ ታሪክ ነው። ሙሴ በተወለደበት ጊዜ ወንድ ልጆች እንዲገደሉ የታወጀበት ነበርና፣ እናቱ በውሃ ላይ ትታው እንዲተርፍ ከማድረጓ በተጨማሪ በንጉሡ ቤት እንዲያድግ ሆኗል።

ሌላው በጽሑፉ የተጠቀሰው በህንድ፣ ግብፅና በሮማውያን የዘር ግንድን ማስቀጠል ባልተቻለበት ሁኔታ የቤተሰብ ሥም እንዲቀጥል ጉዲፈቻን መጠቀማቸው ነው። በእስልምና ሕግ በሚተዳደሩ አገሮች ደግሞ ‹‹ካፍላህ›› በመባል የሚታወቅ የጉዲፈቻ ሥርዓት ይተገበራል።

ታድያ እነዚህ ስርዓቶች በተመሠረቱበትና በተዋወቁበት ዘመን ጉዲፈቻ ከልጆች ይልቅ የጉዲፈቻ አድራጊዎችን ጥቅም መሰረት ያደረገ ነበር። ረሂላ እንደጠቀሱት፣ ‹‹ጉዲፈቻ የዘር ሀረግን በቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ በወንድ ጉዲፈቻ ተደራጊ ልጅ አማካይነት ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ እንዲሁም በገበሬዎች አካባቢ ተጨማሪ አጋዥ ኃይል ለማግኘት ጭምር ሲተገበር ቆይቷል። የጉዲፈቻ ተደራጊዎች የእድሜ ክልልም በአብዛኛው ከ10 ዓመት በላይ ነበር።››

በዓለም አገራት ጉዲፈቻን በሚመለከት ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ ሕጎች እየወጡ፣ እየተሻሻሉና እየበለጸጉ ሄደው፣ የጉዲፈቻ ውል በፍርድ ቤት እንዲጸድቅ የተደነገገበት ደረጃ ላይ ተደረሰ። ይህም ከጉዲፈቻ አድራጊዎች ጎን ለጎን የልጅን ደኅንነት የሚያስጠብቅ መሆኑ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ አስችሏል። ሕጉ በፍርድ ቤት በኩል በጉዲፈቻ የሚወስዱ ቤተሰቦች ለሕጻኑ ተስማሚ መሆናቸውን በቅድሚያ ማረጋገጥ እንዳለበትም ያስቀመጠ ነበር።

እንደውም ቀስ በቀስ ልጅን ለማሳደግ ከሚወስዱት በላይ የልጆች የደኅንነት ጉዳይ ቀዳሚውን ትኩረት አገኘ። ረሂላ ጉዳዩን እንደሚከተለው ያስቀምጡታል፤ ‹‹ጉዲፈቻ መንግሥታት የተጣሉ፣ ቤተሰብ የሌላቸው/የማይንከባከባቸው ወይም ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ልጆችን የሚንከባከቡበትና ደኅንነታቸውን የሚያስጠብቁበት ተቋም ለመሆንም በቃ።››

- ይከተሉን -Social Media

ሙሉጌታም በጉዲፈቻ አጀማመር ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በየባህሉ ሲከወን የኖረ ቢሆንም ጉድለት ነበረው ሲሉ ያነሳሉ። አንደኛው ለወንድና ለሴት የሚካሄደው ጉዲፈቻ እኩል የማይታይ ወይም ለወንዶች ያደላ መሆኑ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ብቻ የተወሰነ እና እንደ አጠቃላይ ችግሩን የሚፈታ አለመሆኑ ደግሞ ሌላ ችግር ሆኖ ይነሳል።

ይህ ሁሉ ታድያ፣ እንደ ሙሉጌታ ገለጻ፣ በዚህ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው ልጆች የተሳካ ሕይወት እንዲኖሩ፣ ለአገርም ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ ለማስቻል ነው። ለዚህም በማኅበረሰቡና በቤተሰብ ፍቅር ማደጋቸው ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ተብሎ ይታመናል። ይህን በሚመለከት ጉዳዩ በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ፣ በተለያዩ መዋቅር በሚወርዱና መመሪያና ደንቦች በጽሑፍ ይስፈር እንጂ በአካል ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መስጠት ላይ ግን አልተሠራም።

የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ
ልጆችን/ሕጻናትን በጉዲፈቻ ወደ ውጪ አገር መላክን የሚፈቅደው አንቀጽ ከኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ከተሰረዘ በኋላ በአገር ውስጥ ባለው እንቅስቃሴ ላይ ጫና ፈጥሯል።
መንግሥት ይህን ጫና ምን ያህል ተወጥቶታል የሚለው ይቆየንና፣ ነገር ግን ይህን ለመሸከም ትከሻውን ሰፋ ለማድረግ ያለወላጅ ለሚቀሩ ልጆች ቤተሰብ ከመፈለግ በተጓዳኝ ተጨማሪ አራት አማራጮችን ይዞ መሥራት ላይ ማተኮሩ በግልጽ ይታያል።

እነዚህም የማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍና ክብካቤ፣ ወደ ቤተሰቡ የመመለስና የማገናኘት እንቅስቃሴዎች፣ በአደራ ቤተሰብ ውስጥ ልጆች እንዲያድጉ ማድረግና የመጨረሻው አማራጭ ደግሞ በማሳደጊያ ማእከላት እንዲቆዩ በዛው እየደገፉ ማቆየት ነው።

በዚህ መሠረት በአዲስ አበባ ብቻ በመንግሥት የሚተዳደሩ ሦስት የሕፃናት ማሳደጊያና አንድ የማገገሚያ (ሪሀብሊቴሽን) ማእከላት ያሉ ሲሆን፣ 30 የሚሆኑ የግል የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ይገኛሉ።

ልጆች በተለያየ ምክንያት መንገድ ላይ፣ ሕክምና ማእከል ውስጥ፣ ቆሻሻ መጣያ አካባቢ፣ ወላጆችን በሞት አጥተው ያለአሳዳጊ ሲቀሩና መሰል ክስተቶች ሲፈጠሩ፣ ፖሊስ ልጆቹን የሚያስረክበው ክበበ ፀሐይ ለተሰኘው የሕጻናት ማሳደጊያ ነው። በዚህም ከዜሮ እስከ ስምንት ዓመት መካከል የሚገኙ ሕፃናት እንዲቆዩ ይደረጋል። ስምንት ዓመት ሲሞላቸውና እስከዛ ድረስ በጉዲፈቻ የሚወስዳቸው ካላገኙ፣ ወንዶች ወደ ኮልፌ የወንዶች ሕፃናት ማሳደጊያ፣ ሴቶቹ ደግሞ ወደ ቀጨኔ ሴት ሕፃናት ማሳደጊያ ይዛወራሉ።

ታድያ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛው እንቅስቃሴ ከማኅበረሰቡ ተሳትፎ ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚገናኝ ነው። ስለዚህም ነው ዋናው ሥራ የግንዛቤ ማስጨበጥና ሰዎች ልጆችን እንዲንከባከቡ፣ እንዲጠብቁና ኃላፊነት እንዳለባቸው እንዲውቁ የማድረጉ ነገር ትኩረት የሚሻው። በዚህ ላይ ግን እምብዛም እንዳልተሠራ ባለሞያዎቹ ይናገራሉ።

አናንያ ያዕቆብ በአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ የሕጻናት ድጋፍና ክብካቤ ባለሞያ ናቸው። ግንዘቤ መፍጠር ላይ የተሠራው ሥራ ካለው ሁኔታ አንጻር እጅግ አነስተኛ የሚባል እንደሆነ ይስማማሉ። ጉዳዩን እንደ ችግርም በቅሬታ የሚያነሱት ነው።

- ይከተሉን -Social Media

‹‹የግንዛቤ ሥራ ላይ አሠራራችን ደካማ ነው። ማኅበረሰቡ ንቁ እንዲሆን አልተደረገም። የግማሽ ቀን ወይም የአንድና የኹለት ቀን ግንዛቤ እንሰጣለን። የሰማ ሰው ስሜታዊ ሆኖ ይቆይና ከዛ ሲወጣ ይረሳዋል።›› ሲሉ የሚሆነውንና የሆነውን ያስታውሳሉ። አሁንም ቢሆን በዚህ መልክ መቀዛቀዙ እንዳለ ነው፣ ለአዲስ ማለዳ የጠቀሱት።

‹‹የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ላይ በደንብ መሠራት አለበት። የተለያየ ዘዴ መጠቀምም አለብን። እኛ ባለመሥራታችን ተቀዛቀዘ እንጂ ልጅ የሚፈልጉ ብዙ ቤተሰቦች አሉ።›› ሲሉ አክለዋል።
ታድያ በሰው በሰው እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች የጉዲፈቻ ልጅ ማግኘት እንደሚቻል የተረዱ ሰዎች ወደ ቢሮው ሲያቀኑ፣ በተለያዩ መስፈርቶች ተነጥረውና ታይተው ልጆችን እንዲወስዱ ይደረጋል። እንደ አናንያ ገለጻም ያልተጠበቀ ክትትል በየወቅቱ በእነዚህ ቤተሰቦች ላይ ይደረጋል።

ይህ በአዲስ አበባ ይሁን እንጂ ሕጻናቱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ይገኛሉ። እነዚህም እንደተባለው ተጥለው የሚገኙና ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ልጆች ናቸው። ተጥለው ለተገኙት ልጆችም በሥጋ የወለዳቸውን ወላጅ ማፈላለግ የሚቀድም ተግባር ሆኖ፣ ተፈልገው ከታጡ ግን ለአደራ ቤተሰብ እንዲሁም እንደ ልጅ በጉዲፈቻ ተቀብለው ለሚያሳድጉ ይሰጣሉ።

በዚህ መካከል የሚያጋጥም ነው ሲሉ አናንያ ተከታዩን ጠቅሰዋል። ‹‹በቅርቡ አንድ ሕጻን ልጅ ወደ ማሳደጊያ መጥቶ ነበር። ወላጆቹ ሊገኙ ስላቻሉ ወደ መመደብ ሥራ ገብተን ሊያሳድጉ ከሚችሉ ቤተሰቦች ጋር አገናኘን። በኋላ ግን ወላጅ እናት መጥታ መልሱልኝ ብላ ተቀብላለች።›› በማለት ያስታውሳሉ። እነዚህም ጉዳዮች በሕግ አግባብና በፖሊስ ትብብር ተጣርተው የሚከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ አናንያ ገለጻ፣ ምንም እንኳን ቢሮው በተቀናጀ መልኩ ወደ ማሳደጊያው የሚገቡና በጉዲፈቻ የሚሰጡ ልጆችን አጠናቅሮ ባይመዘግብም፣ በሳምንት ቢያንስ ከ4 እስከ 5 የሚሆኑ ሕጻናት ወደ ክበበ ፀሐይ እንደሚገቡ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይህ ግምታዊና ነባራዊ ነው ብለው የሰጡት ይሁን እንጂ፣ በአንጻሩ ቁጥሩ በየሳምንቱ ሳይሆን በየቀኑ የሚመዘገብ ነው የሚሉ ዘገባዎች በተለያየ ጊዜ ወጥተዋል።

አናንያ ቀጥለው ‹‹የሚገቡትም እኛ ጋር ብቻ ነው። ለግል ሕጻናት ማሳደጊያ የምንመድባቸው ልጆችም አሉ።›› ሲሉም ከመንግሥት በተጨማሪ የግል ተቋማት በሥራው ድርሻ እንዳላቸው አውስተዋል።

ልጅ ለመውሰድ ወደ ስፍራው የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ግን በወቅትና በሁኔታ የሚፈራረቅ ነው ያሉ ሲሆን፣ ጉዳዩ በመገናኛ ብዙኀን አጀንዳ የሆነ ሰሞን፣ ሥልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ የሚሰጡ ጊዜያት አካባቢ ቁጥሩ እንደሚጨምር ጠቅሰዋል።

በሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሕጻናት የድጋፍ አገልግሎትና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ በለጠ ባዬ በጉዳዩ ላይ የተወሰነ አስተያየት ሰጥተዋል። በዚህም የአገር ውስጥ ጉደፈቻ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ሲያስሩዱ፣ ‹‹ምን ያህል ፍላጎት እንደተፈጠረ ከቢሮው [አዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ] ማየት ይቻላል። ሕጻናት በተቀመጡ አማራጮች የተለያየ ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት ይደረጋል። ግንዛቤ ላይም እንሠራለን።›› ሲሉ አጠቃለዋል። በዚህም ብዙ ልጆች ጋር ተደራሽ መሆን እንደተቻለና ተጥለው የሚገኙ ልጆች ቁጥርም መቀነሱን ጠቅሰዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ሆኖም ምን ያህል ተደራሽ ሆነ? ምን ያህል ልጆች ተጥለው ተገኙ? ምን ያህሎቹ በሞት ወላጆቻቸውን አጥተው ፖሊስ ወደ ማእከላቱ አስገባቸው? ምን ያህል ወላጆች ልጆችን ወሰዱ? የሚለው የጠራ ሪፖርት የሚገኝለት ጥያቄ አይደለም። በተመሳሳይ ማስተባበርና መከታል እንዲሁም ጥናቶችን ማድረግ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ‹‹ልጆች የሚጣሉበት ምክንያት ግልጽ ስለሆነ ያደረግናቸው ጥናቶች የሉም። የተወሳሰበ ጥናት የሚፈልግ አይመስለኝም። ጎዳና ላይ ከሚገኙ ልጆችና ጥቃት በሚፈጸምባቸው ልጆች ላይ የተሠሩ ጥናቶች ግን አሉ።›› ሲሉ ነው በለጠ አስተያየታቸውን የሰጡት።

የውጪ ጉዲፈቻ ለምን ተዘጋ?
በስለ እናት በጎ አድራጎት የምትገኝ እስራኤል የምትባል ተጥላ የተገኘች ትንሽዬ ልጅ አለች። ሰውነቷ ልጅ መሆኗን አይቶ ይመስል አይታዘዛትም። የምትበላው፣ የምትጠጣው በአስታዋሽና በሞግዚት ነው። ተነስቼ ልጫወት ልቦርቅ፣ ምግቤን ስጡኝና ራሴ ልጉረስ፣ ልብሴን እኔው ልልበስ ብላ እንደ ልጅ ልታስቸግር አትችልም። የአካል ጉዳቷ ከዚህ ሁሉ ገድቧታል።

ይህቺን ሕጻን በአገር ውስጥ ሕክምና ማዳን አይቻልም። ቀሪ ሕይወቷ ሁሉ አሁን ልጅነቷ እንደ ዋዛ በሚያልፍበት መንገድ ሊያልፍ እንደሚችል የዛሬ መስታወት የሚያሳየው መራራ እውነት ነው። ነገር ግን ለዚህች ሕጻን የውጪ ጉዲፈቻ ተገኝቶ ልትላክ ነበር። ሊወስዷት ፈቃዳቸው የሆነ ከባህር ማዶ የመጡ ሰዎችም ነበሩ። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕግ ነገሩን አልፈቀደምና ሳይሆን ቀረ።

ይህን ክስተት እንደ አንድ አጋጣሚ ሙሉጌታ ያንሱት እንጂ፣ አናንያም ተመሳሳይ ጉዳይ ጠቅሰዋል። ‹‹የውጪ ጉዲፈቻ መኖሩ ትልቅ ዋስትና ሆኗቸው የነበረው የአካል ጉዳት ያለባቸው ልጆች ያንን የማግኘት እድላቸው ሰፊ ነበር። መንቀሳቀስ የማይችሉና የተለያዩ ጉድለት ያለባቸው ልጆች አሉ። እነሱን በሚገርም ሁኔታ ነጮቹ ይወስዷቸው ነበር። ፎቶዎች እናያለን።›› ብለዋል።

ያ በመቅረቱም እነዚህ ልጆች መገፋታቸውንና መጎዳታቸውን ነው ያነሱት። ‹‹እኛ አገር ማንም [በጉዲፈቻ ልጅ ለመውሰድ የሚሄድ] አንዳች እንከን ያለበትን ልጅ አይፈልጉም። እንደ እቃ አገለብጠው ነው የሚወስዱት። በማህጸን ፈጣሪ ልጅን ሲሠራ ምን ዓይነት እንደሚሰጥ አናውቅም። በዚህ ግን እድሉ ሰፊ ነው። እናም አስመርምረው የሆነች እንከን ካለች ይመልሳሉ።›› በማለት በሐዘን ይናገራሉ።

ኤች አይ ቪ ያለባቸው ሕጻናትም ከአንድ ዓመት በታች ሳሉ ቀድሞ ከታወቀ በሕክምና ሊድኑ የሚችሉ መሆኑ እየታወቀ፣ እነዚህ ሕጻናት በወላጆቻቸው የተገፉት አንሶ በማኅበረሰቡም ይተዋሉ፤ ይገፋሉ።

በአንድ ጊዜ 70 ሕጻናትን ማስተናገድ የሚችለው በአዲስ አበባ የሚገኘው ስለእናት በጎ አድራጎት ድርጅት ከክበበ ፀሐይ የሚቀበላቸውን ሕጻናት በጉዲፈቻ ማሳደግ ለሚሹ ይሰጣል። ‹‹እስከ አሁን ሕመምተኛ የሆኑትን ልጆች ለመወሰድ የመጣ የለም፤ ሐሳብ ያለውም የለም። ጤነኛውን ነው የሚወስዱት።›› በማለት ሙሉጌታ ትዝብታቸውን ያካፍላሉ።

ከዚሁ ሳንርቅ፣ አናንያ የነበረውን ችግር ሳይጠቅሱ አላለፉም። እንደ እርሳቸው ገለጻ ክትትል አለመኖሩ ትልቅ ክፍተት ነበር። ‹‹ያንን ማድረግ ባለመቻል ብዙ ልጆች አጥተናል። አንድ ቤተሰብ ልጅን ወደ ውጪ አገር ከወሰደ በኋላ ክትትል የሚያደርግ አካል ስለሌለ ልጆቹን እንደፈለገ ያደርጋል። ይህም ማንነት ላይ ትልቅ ጉዳት አምጥቷል።›› ሲሉ አክለዋል።

በዚህ የክትትል ማነስና አለመኖር ምክንያትም የውጪ ጉዲፈቻ እንዲቀር አንድ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል። ‹‹ግንዛቤ መስጠት ላይ በደንብ ብንሠራ ግን አገር ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ በቂ ነው። ልጆችን ይፈልጋሉ ግን የሚያገኙበት መንገድ ጠብባ ነው፤ መረጃ የላቸውም።›› ሲሉ አናንያ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሙሉጌታ የውጪ ጉዲፈቻን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባቀረበው ጥያቄ ሊያስቀር እንደቻለ ያስታውሳሉ። ይህም በጊዜው ውዝግብ አስነስቶ እንደነበርና፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዋናነት ያነሳው ‹ልጆች ማንነታቸውን እያጡ ነው› የሚለው ነጥብ በጥናት ያልታየ ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ።

የማንነት ጉዳይ ምክንያት ሆኖ ይጠቀስ እንጂ፣ ሙሉጌታ በአንጻሩ መከራከሪያ ነጥብ አላቸው። ይህም ጥናት ካለመደረጉ ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን፣ ውጪ አድገው የመኖር መብታቸው የተረጋገጠላቸው ልጆች ከመኖራቸው ጋር የሚገናኝ አሉ። ‹‹ከ2 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ዓለም ይኖራሉ። በጉዲፈቻ ሲኬድ ብቻ አይደለም የማንነት ጥያቄ የሚነሳው።›› ሲሉም ነጥባቸውን ያስቀምጣሉ።

የውጪ ጉዲፈቻ መከልከሉ እንዳለ ሆኖ፣ የአገር ውስጡ ላይ በሚገባ እንደሚሠራ ቢጠበቅም፣ በተለይም የአካል ጉዳት ያለባቸውና የተጎዱ ልጆች የበለጠ እንደተገፉም ጠቅሰዋል። ‹‹በመንግሥት አካላት በኩል የውጪ ጉዲፈቻ ቢዘጋም የአገር ውስጥ እየተበረታታ አይደለም። ለቢሮክራሲ ቅድሚያ ይሰጣል። አሠራሩም ቢሮክራሲ ይበዛዋል። ቅድሚያ የመስጠት ኃላፊነትን አይወጡም።›› ሲሉ ይወቅሳሉ።

በለጠ ከእነዚህ ኹለት ባለሞያዎች አንጻር ሆነው፣ ይህን የመሰለ ቅሬታ የሚያነሱት በልጆች ያልተገባ ገቢ የሚያገኙ ናቸው ብለዋል። ‹‹የውጪ አገር ጉዲፈቻን ፓርላማ የዘጋው ጉዳይ ስለሆነ አስተያየት የምሰጥበት ሂደት የለም።›› ያሉት በለጠ፣ የአካል ጉዳት ያለባቸውንና ወላጅ የተዋቸውን ልጆች የውጪዎቹ ሙሉ ለሙሉ ይወስዳሉ ማለት አይደለም ብለዋል። እርሳቸውም ቀድመው በነበሩበት የቢሮ ኃላፊነት ጤነኛ የተባሉ ልጆች ተወስደው ጉዳት ያለባቸውን ‹ተረከቡን› ብለው የመለሱ ስለመኖራቸው ጠቅሰዋል።
ይህን ያደረገው የልጆች ማሳደጊያ ድርጅት የትኛው እንደሆነ በውል ለመጥቀስ ፈቃደኛ ባይሆኑም።

ከዚህም በተጓዳኝ የውጪ ጉዲፈቻ ሥራ በነበረ ጊዜ ሕጻናትን ተረክበው ከቤተሰብ በማገናኘትና ለጉዲፈቻ በመስጠት የሚሠሩ ተቋማት፣ የነቃ ተሳትፎ ቢኖራቸውም አሁን ላይ ተቀዛቅዟል። ይህም የሆነው ጥቅማቸው ስለጎደለባቸው ነው ሲሉም ይከሳሉ።

በለጠ ደጋግመው የሚወቅሱት እነዚህ በገንዘብ የካበቱ የሚሏቸውንና የመንግሥትን እጅ ለመጠምዘዝ የመንግሥት ሠራተኞችን ጭምር በመያዝ ቢሮክራሲ እንዲበዛና ቅሬታ እንዲቀርብ ያደርጋሉ የሚሏቸውን ‹አካላት› ነው። ለዚህም በአሁኑ ጊዜ ከ100 እስከ 200 የሚደርሱ ቤተሰቦች ልጅ እየጠየቁና እየጠበቁ መሆኑንና በአሠራር ድክመት ግን እንዳልተስተናገዱ ነው ያነሱት። ‹‹እናንተንም እንዳያሳስቱ እፈራለሁ።›› ሲሉ አዲስ ማለዳን ጨምሮ ለመገናኛ ብዙኀን ስጋት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
ያም ሆነ ይህ፤ በ2011 የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ እንደተቀመጠው፣ 1 ሺሕ 551 ሕጻናት በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ አማራጭ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ችግሩ ምንድን ነው?
ቢቢሲ አማርኛ ‹‹ከ125 በላይ የተጠፋፉ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችን ያገናኘችው አሜሪካዊት›› ሲል ያነሳቸው አሜሪካዊቷ አንድሪያ ኬሊ ኹለት ኢትዮጵያውያን ልጆችን እንደ እናት ለማሳደግ ከወሰዱ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። እኚህን ሴት አዲስ ማለዳ በኢሜይል አድራሻቸው አግኝታ የተጠፋፉ ቤተሰብ ስለሚያገናኙበት የኢትዮጵያ (ማደጎ) ወይም ጉዲፈቻ ትስስር ድርጅት (ቤተሰብ ፍለጋ/ Ethiopian Adoption Connection (EAC)) ዙሪያ እንዲሁም በኢትዮጵያ የጉዲፈቻ አሠራር ላይ ስላላቸው ምልከታ ጠይቃቸዋለች።

የሆነው እንዲህ ነበር። አንድሪያ ከኢትዮጵያ ኹለት ልጆችን በጉዲፈቻ ለማሳደግ ይወስዳሉ። ቆይተው ልጆቹን ከቤተሰባቸው የማገናኘት ሐሳብ ይመጣላቸውና ፍለጋ ያደርጋሉ። የሴት ልጃቸውን ወላጅ እናት ያገኙ ሲሆን የወንዱ ልጃቸውን ግን ማግኘት አልቻሉም። ይህንን አሁንም ከ18 ዓመት በኋላ ተስፋ ሳይቆርጡ እያደረጉት ያለ ፍለጋ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ሳይጠቅሱ አላለፉም። ይህ ሐሳብ ነው ከግላቸው አልፈው ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም እንዲያገናኙ መነሻ ምክንያት የሆናቸው።

በዚህ እንቅስቃሴም ከ150 በላይ ልጆችን ከቤተሰቦቻቸው ማገናኘት መቻሉን ይጠቅሳሉ። አሁንም ከ800 በላይ ተመሳሳይ ጉዳዮች መኖራቸውንም አያይዘው አንስተዋል። በኢትዮጵያ ዙሪያ አዲግራት፣ ጋሞ ጎፋ፣ ቤንች ማጂ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ከምባታ ጠንባሮ፣ ድሬዳዋ፣ ጎንደር ፣ ባህርዳር፣ ወሊሶ፣ ጂማ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ በርካታ ቤተሰብ የማገናኘት ሥራ እንደሠሩና፤ ከ20 እና 30/40 ዓመት በፊት የተለያዩ ቤተሰቦችም በዚህ መገናኘታቸውን አንስተዋል።

አንድሪያ ጉዲፈቻን በመረዳት በኩል በኢትዮጵያውን ዘንድ ያሉ ችግሮችና ፈተናዎችን ሳያነሱ አላለፉም። በዚህም በይበልይ በሕግ አሠራሩ ላይ ያለውን ሁኔታ በክፍተት ተመልክተውታል። ይህም በአውሮፓ አገራት ሰዎች ልጆችን በጉዲፈቻ ከወሰዱ በኋላ ለልጁ ሙሊ ለሙሉ እንደራሳቸው ልጅ ሕጋዊ ተጠያቂ ይሆናሉ። በአንጻሩ በኢትዮጵያ ያሉ ልጆቻቸውን በፍላጎትም ይሁን በተለያየ ሁኔታ እንዲተዉና እንዲሰጡ የሆኑ ቤተሰቦች በልጆቻቸው ላይ ያላቸውን መብት እንደሚያጡ አያውቁም።

ይህ የአንድሪያ እይታ ነው። አሁን ባለው የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ብቻ ብንመለከት ታድያ ተደጋግሞ እንደተጠቀስ የግንዛቤ እጥረት አለ። ይህ የግንዛቤ እጥረት ባለ ብዙ ስለት ሆኖ ጥቂት የማይባል ጥፋትን ያስከትላል። ለምሳሌ አንዱ የማንነት ጉዳይ ነው። ሕጻናት ወደ ውጪ እንዳይሄዱ የሚሆነው አንድም የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዳይገቡ ታስቦ ነው ቢባልም፣ በአገር ውስጥም ቤተሰብ የልጅን ማንነት ደብቆ በማቆየት ነገሩ በድንገት ይፋ ሲሆን የማንነት ቀውስ እንደሚከሰት ነው ባለሞያዎቹ የሚናገሩት።

አንድ በልጆች ጉዳይ ላይ የሚሠሩና የት እንደሚሠሩም ሆነ ሥማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉ ሰው ችግሩን ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል። ‹‹ሁሌም ቅር የሚለኝ በዋናነት በኃላፊነት ላይ የሚቀመጡ ሰዎች በፖለቲካ ሹመኝነት ነው። ሁሌም ሥራቸው ከታይታ ጋር ነው። ለምሳሌ አንድ ክዋኔ ወይም ድግስ ሲኖር ጉዲፈቻ የሚወስዱ ቤተሰብ ፈልጉ ይባላል። ካገኘን እንደ ዕቃ አደባባይ ላይ ልጅ ይረካከባሉ። ይህ ሁሌ ያመኛል›› ሲሉ አንስተዋል።

ይህ በጉዳዩ ግንዛቤ የመፍጠርና የማነሳሳት ዓላማ አለው ቢባል እንኳ ሄድ መለስ የሚሉ ባለሥልጣናት አያያዝ እንደ ችግር ሊታይ የሚገባ ነው ብለዋል። ያም ብቻ ሳይሆን በማሳደጊያ ያሉ ልጆችን መገልገያ ተብለው የተቀመጡ ተሸከርካሪዎችን መውሰድ ሌላው ነው ብለዋል። ይህም በእጅጉ የሚያሳዝናቸው እንደሆነና ከማዘን ውጪ ምንም እቅም እንደሌላቸው በማስተዛዘን ገልጸዋል።

ነገረ ማንነት – ከውጪ እስከ አገር ቤት
የማንነት ነገር በውጪ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥም የሚነሳ ጉዳይ ነው። በውጪም ሆነ በአገር ውስጥ ለጉዲፈቻ የተሰጡ ልጆች ጋር ‹ከየት መጣሁ› የሚል ጥያቄ ይነሳል። ከሐተታችን መግቢያ ያነሳናቸው የምሥራች ከአዲስ ማለዳ ከቀረበላቸው ጥያቄ መካከል አንዱ ፍርሃት ይሰማቸው እንደሆነ ነው። ‹‹አዎን ይሰማኛል›› ሲሉ ነበር እርሳቸውም ምላሽ የሰጡት።

ልጃቸው በጉዲፈቻ የተወሰደ መሆኑን ሲያውቅ የሚሰማውን ስሜትና ሊያሳይ የሚችለውን ግበረ መልስ ማሰቡ ያስፈራቸዋል። ለዚህም ነው ከአሁን ጀምረው በሚኖሩበት አካባቢም በልጆቻቸው ዙሪያ ሲነሳ በሞት በተነጠቁት ልጃቸው ፋንታ አዲሱን ልጃቸውን የማያነሱት። ልጃቸው እንዳይደበቅና የአካባቢው ማኅበረሰብም እንደ አዲስ ግኝት ተናግሮ ልጃቸውን እንዳያስጨንቅ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

አናንያም ይህ ነገር አሳሳቢና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው መሆኑን ጠቅሰዋል። ለልጆች መቼ መነገር አለበት የሚለውንም ከስር ከስር በተረትና በጨዋታ የጉዲፈቻን ጉዳይ በቀላሉ በመንገር ልጆች ሲያድጉ እንግዳ እንዳይሆንባቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ እድሜያቸው 13 እና 14 የሆኑ ልጆች፣ በድንገት ከአካባቢ ማኅበረሰብና በተለያየ አጋጣሚ ያሳደጓቸው ቤተሰቦቻቸው ወላጆቻቸው እንዳልሆኑ ሲረዱ ጠፍተው ወደባሰ ችግር የገቡ መኖራቸውን ያነሳሉ።

አዲስ ማለዳ ቀደም ብሎ በጉዳዩ ላይ የተሠሩ ዘገባዎችን ለማገላበጥ ሙከራ አድርጋለች። በዚህም ቢቢሲ አማርኛ ከውጪ ጉዲፈቻ መቅረት ጋር በተያያዘ በሠራው አንድ ዘገባ ‹‹የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ባለፉት ዓመታት እየጨመረ ነው ወይ?›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው በወቅቱ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ግለሰብ፣ መረጃው ከክልሎች ያልተሰበሰበ በመሆኑ ምላሻቸው በዚህ አልፎ ነበር። አሁንም የተሰጠው መልስ ከዛ የተለየ አልነበረም።

ምን ላይ ይተኮር?
የኢፌዴሪ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ነው። መከታተልና መቆጣጠር እንዲሁም ማስተባበር የተሰኙ ኃላፊነቶች አሉበት። በቀደመው ጊዜ በሕግ ክፍተት ምክንያት ክትትሉ ሊጠናከር እንዳልቻለ ነው በለጠ የሚያነሱት። በጉዲፈቻ ልጅ የወሰዱ በውጪ ያሉ ሰዎችን ለመከታተል የሕግ አስገዳጅነት እንዳልነበረ በመጥቀስ።
ሙሉጌታ ደግሞ በበኩላቸው ልጆችን ለአሳፋጊ በመስጠት ሂደት ውስጥ ትልቅ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ነው ያነሱት። ልጅን ለጉዲፈቻ አሳዳጊ በሚሰጡ ጊዜም የአሳዳገዎችን የኑሮ ሁኔታ እና አቅም ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦና እና ሕይወት መቃኘት፣ ልጅ የፈለጉበትን ምክንያትም መፈተን ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

ማሳደጊያ ውስጥ ሕጻናትን ማቆየት የመጨረሻው አማራጭ እንደመሆኑ፣ ሕጻናቱን በፍጥነት ከዛ ቦታ እንዲወጡ በማሰብ ብቻ ጉዲፈቻ ሊሰጥ አይገባም ሲሉም ይሞግታሉ። ይልቁንም የልጆች ጥቅምና ደኅንነት ነው ቅድሚያ መሰጠት ያለበት። ካልሆነ እንደ ሙሉጌታ ገለጻ፣ ልጅን ሊቀለበስ የማይችል ችግር ውስጥ ይከታል።

እንደ ወይንሸት እና የምሥራች ባይልዱትም በጉጉት የሚናፍቁት፣ ተቀብለው በእንክብካቤና በማይነጥፍ ፍቅር የሚይዙትን ሕጻን ልጅን በጉዲፈቻ መውሰድ፣ ወልዶ እንደመሳም የሚጠጋ ክብር አለው። ይህንንም እነዚህ እናቶች በንግግራቸው ያሳበቁት እውነት ነው።

ታድያ፣ የራስን ገዱለት ለመሙላት ብቻ ሳይሆን፣ ለሕጻናቱም የልጅነት ዘመን እንዳይጎድልባቸው፣ ነገ የአገር ተረካቢ መሆናቸውን በማሰብና የዜግነት ኃላፊነት እንደሆነ በማመን፣ በየአቅማቸው ሕጻናትን በጉዲፈቻ ወስደው እንዲሳድጉ ግን ሁሉም ባለሞያዎችና አስተያየት ሰጪዎች ያቀረቡት ምክረ ሐሳብ ነው። ትኩረቱም ወደ እነዚህ የነገ ሰው ወደሚሆኑ ሕጻናት ሊሆን ይገባል በሚለው ሐሳብ ሁሉም ይስማማሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች