‹‹ ሕጉ ተፈፃሚ እንዲሆን አያስገድድም››
የኤክሳይስ ታክሱ አዋጅ የካቲት 5/2012 በተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን ተከትሎ ታክሱ በተጣለባቸው እንደ ቢራ ያሉ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ የሕግ አተገባበር ጊዜውን የጠበቀ አይደለም ተባለ።
የታክስ ጉዳዮች እና የሕግ ባለሙያ የሆኑት ዮሐንስ ወልደገብርኤል እንዳሉት፣ አዋጁ ከፀደቀበት ጊዜ አንፃር ጭማሪው መደረግ የነበረበት ሦስት ወር ቆይቶ በነጋሪት ጋዜጣ ከታወጀ በኋላ ነበር። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ጭማሪው ሕጉን ያልጠበቀ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሃጂ ኢብሳ በበኩላቸው፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት አዋጁን ማዘጋጀት እንደነበር እና ይህም ተከናውኖ አዋጁ መጽደቁ ኃላፊነታቸውን ሙሉ በሙሉ እንደተወጡ የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልፀዋል። ነገር ግን መቼ ተግባራዊ ይደረግ የሚለውን መወሰን እና መቆጣጠር የንግድ እና ኢንዱስትሪ ኃላፊነት ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዲኤታ እሸቴ አሰፋ በአንጻሩ፣ አዋጁ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል ብለዋል።
በነጋሪት ጋዜጣ ካልታወጀ በስተቀር የአዋጁ ተፈፃሚነት አስገዳጅ ሊሆን እንደማይችል ዮሐንስ ያብራሩ ሲሆን፣ ድርጅቶችም ይህንን ዓይነቱን ጭማሪ ጊዜው እስኪደርስ ያለመቀበል መብት እንዳላቸው አስረድተዋል።
የኤክሳይስ ታክሱ አዋጅ መፅደቁን ተከትሎ ታክሱ በተጣለባቸው እቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።
ታክሱ በአገር ውስጥ በሚመረቱና ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ በአንዳንድ የተመረጡ ዕቃዎች ላይ ብቻ የሚጣል ሲሆን፣ የአልኮል መጠጦች ላይ አርባ በመቶ ከአልኮል ነፃ የሆኑ መጠጦች ላይ ደግሞ ሃያ አምስት በመቶ ጭማሪ ተደርጓል።
ይህንን ተከትሎ የቢራ አምራች ድርጅቶች የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል። በዚህም መሠረት በተለያዩ ፋብሪካዎች በድራፍት በርሜል ከ300 እስከ 550 ብር ጭማሪ ተደርጓል። ባለ ሦስት መቶ ሚሊ ሊትር ቢራዎች በሳጥን 140 ብር ጭማሪ አሳይተዋል።
የሄኒከን ቢራ ሠራተኛ የሆኑ እና ሥማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ አሁን ካለው የዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ተገቢውን ያህል የምርት ዝውውር ይኖራል ብለው እንደማይገምቱ ገልጸዋል። ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በምርቶቹ ላይ የተደረገው ጭማሪ በኤክሳይስ ታክሱ መሰረት የተደረገ እና ተገቢውን ያህል መሆኑን ለማጣራት ኮሚቴ አዋቅሮ እየሠራ ነው ሲሉ ሚኒስትር ዲኤታው እሸቴ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የኤክሳይስ ታክስ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች ተብለው ከሚታወቁ በዕቃ እና አገልግሎት ላይ ከሚጣሉ ታክሶች ምድብ ውስጥ የሚገኝ ታክስ ነው። የኤክሳይስ ታክስ ዋና ዓላማዎች ለመንግሥት ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት፣ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች ፍጆታ መቀነስ፣ ከፍተኛ ሀብት ያላቸው ሰዎች ከሚጠቀሙባቸው የቅንጦት ዕቃዎች ላይ ገቢ በመሰብሰብ በአካባቢ ደኅንነት ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች አጠቃቀም መቀነስ ነው።
ኤክሳይስ ታክስ የቅንጦት ዕቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም፤ አልጨመረም መሠረታዊ ባለመሆናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ፣ እንዲሁም የኅብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱና ማኅበራዊ ችግር የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የሚጣል ታክስ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012



