ገንዘቡ የት ገባ?

0
1487

የምጣኔ ሀብት እስትንፋስ የሆነው የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ፍጥነትና መጠን ለገንዘብ ባለሞያዎች መነጽር ነው፤ የአንድ አገርን ኢኮኖሚ የሚያዩበት። ከቅርብ ወራቶች ወዲህ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት በግልጽ እየተስተዋለ ይገኛል። ሁኔታውን ከገንዘብ ባለሙያዎች አልፎ ‹‹ከኹለት ሺሕ ብር በላይ ከሒሳባችሁ አታወጡም›› ወደሚሉ ባንኮች ያቀኑ ዜጎችን እንደዚሁም ገበያው ከምንጊዜውም በላይ ጭር ያለበት የመርካቶ ነጋዴዎች ተረድተውታል። ባንኮችም ካዝናቸው እየተራቆተ በመሆኑ መፍትሔ ያሉትን ማስተካከያ እየወሰዱ ይገኛሉ።
ለመሆኑ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በገንዘብ ተጥለቅልቀው የነበሩት ባንኮች ዘንድሮ ምን ቢከሰት ነው የገንዘብ ድርቅ የመታቸው? የአዲስ ማለዳው በለጠ ሙሉጌታ፣ ነጋዴዎችን፣ የባንክ ባለሞያዎችንና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በማነጋገር የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

ታላቁ የኢትዮጵያውያን ገበያ መርካቶ ውስጥ እንኳንስ ለእጅ ለማሽንም የሚከብዱ ብሮችን በሰከንዶች ውስጥ የሚቆጥሩ እረፍት የሌላቸው ነጋዴዎች መመልከት ለአገሪቷ ዜጎች አዲስ ነገር አይደለም። ምናልባት ለከተማዋ አዲስ ለሆኑ የውጭ ዜጎች ካልሆነ በስተቀር፣ በመርካቶ ዲታ ከሚባሉ ነጋዴዎች እስከ ጉሊት ቸርቻሪዎች የሚያንቀሳቅሱትን ከፍተኛ የብር መጠኖች ማየትም ሆነ መስማት ምንም አይገርምም። ምን ይሄ ብቻ፤ አንድ ነጋዴ በእቁብ በሚሊዮኖች እንደሚያገኝ መስማት አዲስ ነገር አይደለም።

መርካቶ በገንዘብ እጥረት ስትታመስ ማየት ግን አዲስ ከመሆኑም አልፎ ለብዙዎች አስደንጋጭ ነው። መቼም ይህ ዓይነቱ ያልተጠበቀ ክስተት የገበያ መቀዛቀዝን ተከትሎ የመጣ ሊመስል ይችላል። እውነታው ግን ለየቅል ነው። ለዚህም እንደ ማሳያ በመርካቶ በጫማ ንግድ ላይ ከስምንት ዓመታት በላይ የተሰማራውን ሰለሞን አስራት (ሥሙ የተቀየረ) ባለፉት 20 ቀናት ያጋጠመውን ማንሳት ይቻላል።

በመርካቶም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ለሚሠሩ ነጋዴዎች ወቅቱን የጠበቀ የገንዘብ አቅርቦት ማግኘት ከምንም በላይ አስፈላጊ መሆኑን የሚያነሳው ሰለሞን፣ ባለፉት 20 ቀናት ግን ይህንን ማከናወን አለመቻሉን ያነሳል። ባንኮች ለሚቀርብላቸው የገንዘብ ጥያቄ ‹ገንዘብ የለም!› በማለት የሚሰጡት ምላሽ፣ ሥራውን በእጅጉ እንደጎዳው ሰለሞን በምሬት ይናገራል።
‹‹ከዚህ ቀደም፤ የፈለግነውን ያህል ገንዘብ ማውጣት እንችል የነበረ ቢሆንም በአሁን ሰዓት መርካቶ ውስጥ የሚገኙት የባንክ ቅርንጫፎች ይህንን ማድረግ አልቻሉም። ስለዚህም ገንዘብ ለማግኘት ከተማውን ማካለል የግድ ሆኖብናል›› ይላል ሰለሞን፤ የችግሩን ክብደት ሲያስረዳ። ‹‹ጊዜያችንንም አባክነን የምንፈልገውን ያህል የራሳችን ብር ማውጣት የማይቻልበት ደረጃ ደርሰናል።›› ሲል ሰለሞን ምሬቱን ይገልፃል።

በተፈጠረው የገንዘብ እጥረት ምክንያት እቃ ጭነው ከሚመጡ አስመጪዎች ከፍለን ምርት መረከብ አልቻልንም የሚለው ሰለሞን፣ ብር ፈልጎ አውጥቶ እስኪመጣ ድረስ በእጃቸው ቀድመው ብዙ ገንዘብ በያዙ ነጋዴዎች የሚፈልገው ምርቶች እንደሚወሰዱበት ያነሳል። እቁብ እንኳን አሸንፎ እቃ ከፍሎ ለመውሰድ ቢፈልግም፣ ጥሬ ገንዘብ ከእቁብ ሰብሳቢ ከባንክ ለማውጣት ቢሞክርም፣ እንዳልቻለ ሰለሞን ይናገራል።

‹‹ጥሬ ገንዘብ የምናገኝበት አጋጣሚ እየጠበበ ከመምጣት በላይ በአሁኑ ወቅት ባንኮች ገንዘብ ያላቸው ወቅት እንኳን 30 ሺሕ ብር ማውጣት አልተቻለም›› የሚለው ሰሎሞን፣ ይህ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሸቀጦች እንደልብ እንዳይራገፉ በማድርግ መርካቶ ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲቀዛቀዝ ምክንያት እንደሆነ ገልጿል።
ችግሩ በዚህ አላበቃም።

ለመርካቶ ንግድ አንድ ምሰሶ የሆኑት የክልል ከተሞች ነጋዴዎችም የገንዘብ እጥረቱን ተከትሎ የሚገዙትን የሸቀጥ መጠን እንደቀነሱ ሰለሞን ያነሳል። ከእጥረቱ በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ሌሎች ከተሞች የሚላከውን ሸቀጥ እንደ ሰለሞን ያሉ ነጋዴዎች በራሳቸው ገንዘብ ገዝተው በእምነት ለክልል ነጋዴዎች በመስጠት ምርቱ ቀስ በቀስ ሲሸጥ እንዲከፍሉ ይደረግ ነበር። ቢሆንም ከተከሰተው የብር እጥረት በኋላ ግን ይህንን ማድረግ አልተቻለም።

መፍትሄ ያላገኘው የገንዘብ እጥረት መሬት ላይ ያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ አሁንም በዚህ አላበቃም።
ከችግሩ መከሰት በፊት እጃቸው ላይ ገንዘብ የያዙ ሰዎች ከባንክ እንዲሸሹ እንዲሁም ነጋዴዎችን እንደዚህ ቀደሙ የሚያገኙትን ገቢ በአቅራቢያቸው ባለው ቅርንጫፍ ከማስገባት ይልቅ ካዝናቸው ውስጥ ደብቀው እንዲያስቀምጡ ምክንያት ሆኗል። ‹‹ወደ 20 ሺሕ ወይንም 30 ሺሕ ብር ገደማ ከባንክ ለማውጣት ሰዓታት ወይም አንድ ሙሉ ቀን እያባከንኩ በምንም ተዓምር የማገኘውን ገንዘብ ባንክ ላስቀምጥ አልችልም። እንደውም በተቻለኝ አቅም ያለኝን አውጥቼ በእጄ መያዝ እፈልጋለው።›› ሲል አንድ በመርካቶ የሚገኝ የውጭ ሱሪዎችን አከፋፋይ ችግሩን ለአዲስ ማለዳ አጋርቷል።
ታዲያ ይህ አይነቱ ችግር ያቺ ‹ምንም ነገር የሚታጣባት የለም!› እንዲሁም በውስጧ ‹የዕለት ጉርሱን ለማግኘት የቀረባትን ፆሙን አታሳድርም› የምትባለውን መርካቶ የቀድሞ ገፅታዋን እንድታጣ ከማድረጉም በላይ ከንግድ ወደ ድብርት መናኽሪያነት እንድትቀየር ምክንያት ሆኗል። የእቃ ያለ የሚሉ የተራቆቱ ሱቆቿ፣ እንቅልፍ ሊወስዳቸው ጫፍ የደረሱ ወዛደሮቿ፣ ያለሥራ ተቀምጠው ‹ኪሳራ ውስጥ እወድቅ ይሆን› በሚል እሳቤ ሞባይላቸውን በንዴት በየጥቂት ደቂቃዎች የሚደቁሱ ነጋዴዎቿ፣ እንዲሁም እቃዎችን አጥተው ደፋ ቀና የሚሉ ደንበኞቿ እና ተገበያዮቿ ምንም እንኳን ቢዥጎሮጎሩም የመርካቶ አዲስ መልክ ናቸው።

‹‹የለም›› የሚለው ቃል ላለፉት 20 እና 30 ቀናት የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ፣ ተገበያዮች ከቀልጣፋ የመርካቶ ነጋዴዎች አንደበት የሚያገኙት መልስ ነው። ደፋ ቀና ብለው የቆጠቡትን ብር በጥሬ ገንዘብ ማግኘት ልክ ድንጋይን ቀጥቅጦ ደም የማውጣትን ያህል ከባድ የሆነባቸው ነጋዴዎች፣ ይህ አይነቱ ምላሽ መስጠታቸው ተመሳሳይ መልስ ከባንኮች እንደማግኘታቸው መጠን ላይገርም ይችላል።
ታዲያ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት የተከሰተው የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ማሳያ ተደርጋ በምትወሰደው መርካቶ ብቻ አይደለም። ችግሩ ከዳር እስከ ዳር በመላው ኢትዮጵያ ያጋጠመ ሲሆን፣ ከሸማች እስከ ፋብሪካ ባለቤቶች እና አስመጪዎች፣ ሁሉም የእጥረቱ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።

ይባስ ብሎ፤ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ባለባት መቀሌ ከተማ ዜጎች ደሞዛቸውን እንኳን ማውጣት ተስኗቸው የነበረ ሲሆን፣ ከኹለት ሺሕ ብር በላይ ማውጣት በኹሉም ባንኮች ተከልክሎ ነበር። ምንም እንኳን ይህ አይነቱ ችግር በሌሎች ንግድ እንቅስቃሴ ባለባቸው ከተሞች አጋጥሞ የነበረ ቢሆንም፣ ያገኘው የሚዲያ ሽፋን አነስተኛ በመሆኑ መነጋገሪያ ሊሆን አልቻለም።
ከዚህ በላይ አሳሳቢው የሆነው ጉዳይ ግን ችግሩ እንዴት ተከሰት እንዴት ይፈታል የሚለው ሲሆን፣ ለመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆነ ለፖሊሲ አውጪዎችም ቢሆን እጥረቱን ማቆም ዋነኛ አጀንዳ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የገንዘብ ዕጥረቱ ምን ያህል የከፋ ነው?
የገንዘብ ፍሰት የኢኮኖሚን ወቅታዊ እንቅስቃሴ መሰረት ባዳረገ መልኩ የሚከናወን እና የሚመራ ነው። ፍሰቱን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ባለፉት ዓመታት አብዛኛው የመንግሥት ወጪ ዕድገትን በሚያፋጥኑ እና ድህነትን በሚቀንሱ ዘርፎች ላይ የዋሉ ሲሆን፣ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጡ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይም እንዲውሉ ተደርጓል። ይህም በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን በባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በ13 እጥፍ አድጎ ወደ 900 ቢሊዮን ብር እንዲጠጋ ምክንያት ሆኗል።

በአንድ በኩል ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መሰራጨቱ አገሪቷ ይበል የሚያሰኝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንድታስመዘግብ ምክንያት ሲሆን፣ ብዙ ገንዘብ እንዲታተም እንዲሁም የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ እንዳደረገም በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይነሳል። ከዚያ ባሻገር፤ የዋለበት መንገድም ትክክለኛ ባለመሆኑ፣ ሙስና እና የሀብት ብክነት እንዲስፋፋ ምክንያት እንደሆነ በባለሙያዎች ይነሳል።

ታዲያ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ መንግሥት በንፅፅር ጥብቅ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ መተግበሩን ተከትሎ፣ የመንግሥት ፕሮጀክቶች እንዲቋረጡ እንዲሁም የተጀመሩት ሳያልቁ አዳዲስ ግንባታዎች እንዳይጀመሩ ማዘዛቸው መንግሥት-መር የሆነው የአገሪቷ ምጣኔ ሀብት እንዲዳከም ምክንያት ሆኗል። ይህንንም ተከትሎ ዐቢይ ሥልጣን ከተቆናጠጡ አንስቶ፣ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ዕድገት እንዲቀንስ እና ባንኮችም ያላቸው የጥሬ ገንዘብ መጠን እንዲቀነስ ምክንያት ሆኗል።

ቁጥሩን በግልፅ ለማስቀመጥ፣ በግል እና በመንግስት ባንኮች እጅ የነበረው የጥሬ ገንዘብ መጠን በባለፈው በጀት ዓመት በ21 ነጥብ 3 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት (2011) ሰኔ ወር መጨረሻ 143 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ደርሶ እንደነበር የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል። መጠኑ በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም መቀነሱን የቀጠለ ሲሆን፣ መጠኑ ከባለፈው በጀት ዓመት የመጨረሻ ሦስት ወራት ውስጥ ከተመዘገበው ጋር ሲነፃፀር በ72 ነጥብ 7 በመቶ መውረዱን ብሔራዊ ባንክ ከወር በፊት ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያመላክታል።

ምንም እንኳን ከዚያ በኋላ ያለው መጠን በብሔራዊ ባንክ ይፋ ባይደረግም፣ የግል እና የመንግሥት ባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት የገጠማቸው ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ መሆኑ መጠኑ ወርዶ እንደ ነበር ግልፅ አድርጎታል።

በሌላ በኩል፤ ባንኮች ከፍተኛ የቁጠባ መቀነስ እያጋጠማቸው መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። ለምሳሌ፤ በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ወደ ባንኮች የገባው የቁጠባ መጠን ባለፈው በጀት ዓመት የመጨረሻው ሩብ ዓመት ጋር ሲነፀፀር በ45 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር (በ72 በመቶ) ወርዷል። ይህም ገንዘባቸውን ባንክ የሚቆጥቡ ሰዎች እየቀነሱ መምጣታቸው የሚያሳይ ሲሆን፣ ባንኮች በእጃቸው ሊኖራቸው የሚችለውን የጥሬ ገንዘብ መጠን ሊቀንሰው እንደሚችል እና ብድር የመስጠት አቅማቸውንም እንደሚያዳክመው ግልፅ ነው።

ከእነዚህ ቁጥሮች ባሻገር፤ ዋናው ጉዳይ ግን ከባለፈው በጀት ዓመት አንስቶ እየቀነሰ የነበረው፡- ከዚያም ቀውስ በሚባል ደረጃ ባለፉት ኹለት ወራት ውስጥ የደረሰው የገንዘብ እጥረት፣ ለምን ተከሰተ የሚለው ጉዳይ እንደሆነ ብዙም አያከራክርም። በተለይም አሁን እጥረቱ አስከፊ ደረጃ የደረሰበት ወቅት ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የገንዘብ ፍሰት የሚመዘገብባቸው ወራቶች (ታኅሳስ እና ጥር) መሆናቸው በባንኮችም ዘንድ ሆነ በመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ዘንድ ከግርምትም በላይ ድንጋጤን ፈጥሯል። ከኹለት ወራት በፊት፤ ለእጥረቱም ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት መጀመሪያ አምስት ቢሊዮን ብር ከዚያም ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ብሔራዊ ባንክ ጨረታ ላሸነፉ ባንኮች የሰጠ ቢሆንም፣ ይህም ውጤት ባለማስገኘቱ በየሳምንቱ አዳዲስ ችግሮች እንዲከሰቱ በር ከፍቷል።

ለአብነትም፤ ከወር በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሠራተኞች ለጊዜው ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት ብድር ማቆሙን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ይህም በብዙዎቹ የግል ባንኮች በተመሳሳይ ምክንያት ተግባራዊ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ፤ ብዙዎቹ ባንኮች አዳዲስ ብድር መስጠት አቁመዋል የሚባልበት ደረጃ ደርሰዋል። እጥረቱ አስከፊ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ብድር ለፈቀዱላቸው ደንበኞችም ገንዘብ መልቀቅ ባለመቻላቸው ቃላቸው መጠበቅ አልቻሉም።

ሌላኛው የቆመ አገልግሎት ደግሞ ከተቀማጭ በላይ ገንዘብ ማውጣት (ኦቨር ድራፍቲንግ) ሲሆን፣ ብዙዎቹ ባንኮች ደንበኞቻቸው ይህንን አገልግሎት እንዳያገኙ ለጊዜው እገዳ ጥለዋል። ታዲያ እነዚህ እጥረቱን ተከትሎ የተከሰቱ ችግሮች የግሉን ዘርፍም ሆነ መንግሥትን አደጋ ላይ ጥሏል። ከዛም አልፎ ንግድ እንዲቀዛቀዝ፣ የተጀመሩ የመንግሥትም ሆነ የግል ግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲቋረጡ፣ ድርጅቶች ምርት መስጠት እንዲያቆሙ አልያም ከአቅማቸው በጣም በወረደ ሁኔታ እንዲሠሩ እና ከፍተኛ ገንዘብ የሚያካትቱ ስምምነቶች እንዲቋረጡ ምክንያት ሆነዋል።

በዚህ መሃል ነበር ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጨማሪ 27 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ያፀደቀው። ወደ 18 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆነው ግልፅ ባይደረግም፣ ማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚውል ይፋ ተደርጓል። እንዲሁም የጥሬ ገንዘብ እጥረቱን ይፈታል የሚለው ለብዙዎች አጠራጣሪ ነው።

እጥረቱ ለምን ተከሰተ?
ከባንክ ኃላፊዎች አንደበት
ላለፉት አምስት ዓመታት የዳሽን ባንክ ፕሬዝደንት ለነበሩት አስፋው ዓለሙ እጥረቱ ግርምት ከመፍጠሩ ባሻገር፣ ምክንያቱን በግልፅ ለማሰቀመጥ አስቸጋሪ ይመስላል። በእርግጥ ከዛሬ ኹለት ወራት በፊት እጥረቱ ዳሽን ባንክን ጨምሮ የግል ባንኮች ላይ እየጠነከረ መምጣት ሲጀምር የግብር መሰብሰቢያ ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ነጋዴዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚያወጡበት ወቅት ስለነበር በአጭር ጊዜ ይፈታል ብለው አስበው እንደነበር ያስታውሳሉ።

በወቅቱም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከባንካቸው ወደ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የወጣ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በነበሩ የግብር ጊዜያት ተመሳሳይ ችግሮች ይከሰቱ ስለነበር በአጭሩ ይፈታል ብለው አስበው ነበር።

ምንም እንኳን ዳሽን ባንክን ጨምሮ ባንኮች በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ ከፍተኛ ብድር መስጠታቸው እጥረቱን ቢያባብሰውም፣ ችግሩ እየከፋ መሄዱን የተገነዘቡት አስፋው ለክስተቱ ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ለመለየት እንደተቸገሩ ያወሳሉ። በግብር የተሰበሰበው ገንዘብም ይሁን ባንኮች የሰጡት ብድር በኢኮኖሚው ውስጥ ገብቶ መታየት ነበረበት ያሉት አስፋው፣ የተፈጠረውን ክፍተት ለመለየት እና ገንዘቡ የት ገባ የሚለውን ማወቅ እንዳልተቻለ ያነሳሉ።

ከሰኔ እስከ መስከረም አጋማሽ ባሉት ወራት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸውን ተከትሎ የገንዘብ ፍላጎት ሲቀንስ ይስተዋላል። ከጥቅምት ወር ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ወራት አብዛኛዎቹ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መነቃቃት የሚያሳዩበት ወቅት ነው። ይህንንም ተከትሎ የገንዘብ ፍላጎቱ ከፍ እንደሚል ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመትም ከባንኮች በመውጣት የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን በ16 ነጥብ 4 ከመቶ ከፍ ብሎ ተስተውሏል። የመጀመሪያ እና ሦስተኛ ሩብ በጀት ዓመት ወቅቶች ላይ፣ ይህ ለውጥ ከፍ ብሎ የሚስተዋል ሲሆን፣ የደረሱ ሰብሎች መሰብሰብ እና ታክስ የሚሰበሰብበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ባንኮች የተንቀሳቃሽ ገንዘብ እጥረት እንዲገጥማቸው ያደርጋል። አሁን ላይ ግን ከፍተኛ እጥረት ያጋጠመው ኹለተኛው ሩብ ዓመት ላይ መሆኑ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎቷል።

ለአንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ግን እጥረቱ የሚጠበቅ ነው። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንድ የንብ ባንክ ከፍተኛ አመራር እንደገለፁት፣ እጥረቱ በዋነኝነት የተከሰተው ባንኮች ከአቅማቸው በላይ ማበደራቸው፣ የሰጧቸው ብድሮች ከባለፈው በጀት ዓመት አንስቶ በሚገባ አለመሰብሰባቸው እንዲሁም ከ20 በመቶ በላይ የደርሰው የዋጋ ግሽበት ዜጎች እንዳይቆጥቡ ማድረጉ ሲሆን፣ እጥረቱ ከታየበት ጊዜ አንስቶ የሰበሰቡትን ገንዘብ ባንክ ማስቀመጥ ማቆማቸው ችግሩን እንዳባባሰው አንስተዋል።

በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ከ30 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱት ክብሩ ፎንጃ በበኩላቸው፣ አሁን ለተከሰተው የገንዘብ እጥረት ሦስት ዐበይት ምክንያቶችን አስቀምጠዋል። ወቅቱ የሰብል ምርቶች የሚሰበሰቡበት እና ገበሬ ምርቶቻቸውን ለገበያ በማቅረብ ገንዘብ የሚሰበስብበት ነው የሚሉት ባለሙያው፣ ምናልባት አሁን ባለው አለመረጋጋት ምክንያት የተሰበሰበውን ገንዘብ መልሰው ጥቅም ላይ ሳያውሉት ቀርተው ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

በኹለተኛነት የባንኮች የተበላሸ ብድር መጨመር እና የብድር አሰባሰብ መዳከም ከተቀማጭ መቀነስ ጋር ተዳምሮ ለእጥረቱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል። ክብሩ በሦስተኛነት ያነሱት የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትን ሲሆን፣ ይህም ገንዘብ በጥቂት ባለሀብቶች ወይም ተቋማት እጅ እንዲቆይ ሊያደርግ እንደሚችል እና ይህም ገበያ ውስጥ ያለው የገንዘብ ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር እንዳይመጣጠን ሊያደርገው እንደሚችል አስረድተዋል።

በክቡር ገለጻ ሌላኛው በፋይናንስ ኃላፊዎች ዘንድ ያለው ፍራቻ ደግሞ መንግሥት ምናልባትም እጥረቱን የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር እየተጠቀመበት ሊሆን ይችላል የሚለው ነው። ይህም ብዙውን ጊዜ የምግብም ሆነ ምግብ-ነክ ያልሆኑ ጭማሪዎች በኢትዮጵያ የሚታዩት ከአቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ በመሆኑ፣ የገንዘብ ፖሊሲው ግሽበትን ከመቀነስ አኳያ የሚኖረው ሚና አነስተኛ እንደሚሆን ብዙዎች ያነሳሉ።

ሌላኛው የባንክ ባለሙያዎች ስጋት ደግሞ ምርጫው እየቀረበ መምጣቱን ተከትሎ አንዳንድ አካላት ጥሬ ገንዘብ አሰባስበው በራሳቸው ካዝና ውስጥ ማስቀመጥ ጀምረው ከሆነ የሚለው ሲሆን፣ ይህ ግን ለብዙዎች ሚዛን የማይደፋ መከራከሪያ ነው።

ከፋይናንስ እና ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አንደበት
ለፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን ሙሐመድ፣ ለገንዘብ እጥረቱ ዋነኛ ምክንያት በግል ባንኮች ከሚጠበቀው በላይ የተስተዋለው የብድር ፍላጎት ተከትሎ የወለድ መጠን እንዲቀንስ መደረጉ እና ባንኮች እነዚህን ጥያቄዎች ያላቸውን የተንቀሳቃሽ ገንዘብ መጠን ባላገናዘበ መልኩ ለማስተናገድ መሞከራቸው እንደሆነ አብራርተዋል። ይህም የቅርንጫፍ ባንኮችን አማካኝ የጥሬ ገንዘብ አቅም ማዳከሙን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል፤ ኢንቨስትመንቶች የማደጋቸውን ያህል የገንዘብ አቅርቦት ወደ ገበያ አለመግባቱ ለእጥረቱ ምክንያት ነው የሚሉት ከኹለት አስርት ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው የፋይናንስ ባለሙያ እና የግሎባል ኢንሹራንስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሰግድ ገብረመድኀን ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ፣ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን እጃቸው ላይ እንዲያቆዩ ምክንያት እንደሆነ የሚያነሱት አሰግድ፣ አለመረጋጋቱ ቁጠባ እንዳያድግ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል ባይ ናቸው። ይህም ባንኮች አዲስ የተፈጠሩ የገንዘብ ፍላጎቶችን ማሟላት ካለመቻላቸው ጋር ተዳምሮ እጥረቱን አባብሶቷል።

በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥናቶችን በማድረግ የሚታወቁት ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በብሔራዊ ባንክ የባንኮችን የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው ዘርፍ ደካማነቱን በማንሳት፣ በቦታው ላይ ያሉት ባለሙያዎች ከአይ ኤም ኤፍ እና ከዓለም ባንክ የመጡ መሆናቸውን የገንዘብ ዝውውር እንደፈለጉት እንዲዘውሩት ምክንያት ሆኗል ይላሉ።

እነዚህ ባለሙያዎችም የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገነዘቡ አይደሉም። እጥረቱንም ጨምሮ ሌሎች ችግር ለመፍታት ብቁ አይደሉም ሲሉም ወቀሳ ሰንዝረዋል። ይህም ድርጊት አገሪቱን የፋይናንስ ሉዓላዊነት የሚጋፋ በመሆኑ እንደዋዛ ሊታይ አይገባም ሲሉ አክለዋል።

በተመሳሳይ፤ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ እና ባለሙያ የሆኑት አየለ ገላን፣ እጥረቱ የዓለም ገንዘብ ድርጅትን (አይ ኤም ኤፍ) እና የዓለም ባንክን ለማስደሰት በመንግሥት እየተደረገ እንዳይሆን ስጋታቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አያይዘውም በተለይ ቀውሱ የተከሰተው አይ ኤም ኤፍ ሦስት ቢሊየን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን በመጠቀም ዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር እንደ ቅድመ ሁኔታ ካስቀመጠ በኋላ መሆኑ፣ መንግሥት እጁ እየተጠመዘዘ እንዳይሆን የሚል ፍርሃት ያጭራል ብለዋል።

ይህ ዓይነቱም ድርጊት ተገቢ እንዳልሆነ ያነሱት አየለ፣ የውጭ አበዳሪዎች በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት የተከሰተው ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ኢኮኖሚ ውስጥ በመግባቱ ነው የሚለው እሳቤ የተሳሳተ ነው ይላሉ። ይህም ተቋማቱ የአገሪቷን ሁኔታ እንደማይረዱት እንዲሁም የኢትዮጵያውያንን ችግር ከግምት ውስጥ ከማስገባት ይልቅ የፋይናንስ አድራጊዎቻቸውን ፍላጎት ለማሳካት እንደሚጥሩ ማሳያ ነው ሲሉ ሞግተዋል።

ከ12 በላይ የሚሆኑ አዳዲስ ባንኮች ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል በመንገድ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ባለሀብቶች ከእነዚህ ባንኮች የአክሲዮን ድርሻ ለመግዛት ከከፍተኛ ገንዘብ አሁን በገበያ ላይ ካሉት ባንኮች በመውሰዳቸው የገንዘብ አጥረቱ ሊከሰት ችሏል የሚሉ ሙግቶችም ይነሳሉ። በተቃራኒው፤ በምስረታ ላይ ያሉት ባንኮች ብር የሚሰበስቡት በግል እና የመንግሥት ባንኮች ውስጥ በከፈቱት አካውንቶች ውስጥ በመሆኑ እና ሥራ ባለመጀመራቸው የተነሳ፣ ገንዘባቸውን እስከ አሁን ማውጣት ስላልጀመሩ እጥረቱ ላይ ድርሻ ሊኖራቸው እንደማይችል የሚያነሱ ባለሙያዎች አሉ።

የተንቀሳቃሽ ገንዘብ ዕጥረት በኢኮኖሚው ላይ ምን ተፅዕኖ ያሳድራል
ገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ በሚፈለገው ደረጃ መንቀሳቀስ ካልቻለ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ሊያስከትል እንደሚችል በተደጋጋሚ ሲነገር ይስተዋላል። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑትም የኢንቨስትመንቶች መቀዛቀዝ፣ የንግድ እንቅስቀሴዎች መቆም እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ፍላጎት እና የኑሮ ውድነት ተጠቃሽ ናቸው። እንደ ዳሽን ባንክ ፕሬዝደንት አስፋው ገለፃም፣ ችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ የማይሰጠው ከሆነ ባንኮች ገንዘብ ማበደር ያቅታቸዋል። ይህንንም ተከትሎ ኢንቨስትመንት ይበልጥ ይቀዛቀዛል። ይህም የአገሪቷን ኢኮኖሚ አደጋ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ያሳያል ሲሉ አስፋው ስጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል።

በሌላ በኩል፣ እንደ ክብሩ ገለጻ ደግሞ ባንኮች ደንበኞች የሚጠይቁትን ገንዘብ መክፍል የማይችሉ ከሆነ ኅብረተሰቡ በእጁ ያለውን ገንዘብ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ማንቀሳቀስ ይጀምራል። ይህም ቁጠባን በመቀነስ ባንኮቹን የባሰ አዘቅት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ተናግረዋል። ባንኮች ለብቻቸው ይህንን ችግር የመቅረፍ አቅም የላቸውም የሚሉት ክብሩ፣ ያልተከፈሉ ብድሮችን ለመሰብሰብም ሆነ ያላቸውን ንብረት ይሽጡ ቢባል እንኳን የሚገዛ ሰው ማግኘት አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ይገልፃሉ።

ዓለማየሁ በበኩላቸው ደግሞ እንደዚህ ዓይነት የገንዘብ እጥረቶች ኢኮኖሚውን እና መንግሥትን ሊያሽመደምዱት እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ። ባለሀብቶች በኢኮኖሚው ላይ እምነት እንዳይኖራቸው በማድረግ በአገር ውስጥ መገበያያ ገንዘብ እምነት እንዲያጡ ሊያደርግ ይችላል የሚሉት ዓለማየሁ፣ ይህ መሆኑ ደግሞ የብር ዋጋ እንዲዳከም በማድረግ አደጋ ሊፈጥር የሚችል እንደሆነም ጠቁመዋል።
አገር ውስጥ ያሉ ባንኮች እንደዚህ ዓይነት ቀውስ ሲፈጠር ለመቋቋም የሚያስችል አቅም እንደሌለቸው የሚያነሱት ዓለማየሁ፣ ባንኮች በራሳቸው ከሚያመነጩት ገንዘብ በላይ የተቀማጭ ገንዘብ ስለሚበልጥ የሚጠቀሙትም ይሄንኑ ገንዘብ ስለሆነ፣ አደጋ ላይ የሚወድቁበት አጋጣሚ ሰፊ ነው ብለዋል። ይህም የበለጠ ቀውስ ኢኮኖሚ ላይ ይዞ ሊመጣ ይችላል ሲሉ አለማየሁ ተናግረዋል።
አየለ ግን በበኩላቸው ባንኮች ስጋት ላይ ናቸው ብለው አያምኑም። ምንም እንኳን ችግሩ አሳሳቢ ቢሆን እጥረቱ በቀላሉ ጊዜያዊ እና በቀላሉ ሊፈታ እንደሚችል ተስፋቸውን ገልፀዋል። ከዚህ ቀደም የበለጠ ቀውስ ውስጥ ገብታ የነበረችው ግሪክን ያነሱት አየለ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ባንኮችን ከማንገዳገድ አኳያ በአንፃራዊነት ቀላል የሚባል እንደሆነ ጠቁመዋል።

መፍትሄዎቹስ ምንድን ናቸው?
ለአብዱልመናን ለንግድ ባንኮች ብድር መስጠት ወይንም ኢኮኖሚ ላይ ገንዘብ መጨመር ለእጥረቱ ጊዜያዊ መፍትሄ ነው። እንደ ፋይናንስ ባለሙያው ገለፃ፣ ችግሩን ለመፍታት መንግሥት ባንኮች በእጃቸው ሊኖራቸው የሚገባው የጥሬ ገንዘብ መጠን ሊጨምር ይገባል። ከዚያም የተቀመጠውንም ገደብ የጣሱ ባንኮች ላይ ከፍተኛ ወለድ መጠን ቅጣት መጣል ያስፈልጋል ሲሉ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንደ መፍትሄ ሐሳብ ያነሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪ፤ በርከት ያለ ገንዘብ ወደ ባንኪንግ ኢንዱስትሪው መግባቱ ችግሩን ለመቅረፍ አቅም መፍጠር ቢችልም፣ ቶሎ መሰብሰብ ካልተቻለ የዋጋ ግሽበትን በማስከተል አደጋ ሊያስከትል የሚችል መሆኑን የጠቁሙት አብዱልመናን፣ ባንኮች ቀጣይነት ያለው እና የተስተካከለ የገንዘብ ስርዓት እንዲኖራቸው የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያከናውኑባቸውን ፖሊሲዎች መለስ ብለው ሊቃኙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ብሔራዊ ባንክ ገበያን እና ወቅትን ተከትለው የሚመጡ የገንዘብ እጥረቶችን በምን ዓይነት መልኩ ባንኮች መከላከል እንደሚችሉ ቀድመው ሊያስቡ እንደሚገባቸው የሚጠቁሙት ደግሞ አስፋው ናቸው። አያይዘውም የግል ባንኮችም ቢሆኑ በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በማጠናከር እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲከሰቱ የሚተጋገዙበትን መንገድ መመልከት አለባቸው ብለዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያዊ ዓለማየሁ የባንኮችን የገንዘብ እንቅስቃሴ የማስተካከሉ ሥራ የብሔራዊ ባንኩ እንደሆነ ይስማማሉ። ተቆጣጣሪው ባንክ የባንኮችን የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲሁም ወጪ እና ገቢ ሳይቀር በዘመናዊ መንገድ በየሰከንዱ ሊከታተል እና የተለዩ ነገሮች ሲስተዋሉ ጣልቃ ሊገባ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚህ በተጨማሪም በባንኮቹ ላይ ድንገተኛ የፋይናንስ ቅኝት እና ቁጥጥር ማድረግ ይገባዋል ያሉት ዓለማየሁ፣ እንዲሁም የባንኮችን የብድር እና ተንቀሳቃሽ የገንዘብ መጠን መወሰን የሚያስችሉ ወጥ የሆኑ መመዘኛዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባው ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ ላይ በቂ እውቀት ያላቸው፣ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ የሆኑ እና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መገንዘብ የሚችሉ ባለሙያዎች ብሔራዊ ባንክ በተገቢው የሥራ ኃላፊነት ላይ እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚገባም ገልፀዋል።

የፋይናንስ ባለሙያው ክብሩ በበኩላቸው፣ እንደዚህ ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ማክሮ ኢኮኖሚው በአጠቃላይ ሊስተካከል እንደሚገባው ጠቁመዋል። በዚህ ላይ አክለውም ቀጣዩን ምርጫ የተረጋጋ ማድረግ እና ባለሀብቶች ያለስጋት ገንዘባቸውን ማፍሰስ የሚችሉበትን አሳማኝ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቁጠባ ሊበረታታ ይገባዋል ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ ሥራዎች ግን በርካታ ጥናቶችን የሚጠይቁ እና አዳዲስ ፖሊሲዎች የሚያስፈልጋቸው እንደሆኑ አብራረተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here