የኢንዱስትሪ ፓርኮች የወጪ ንግድ በ42 ሚሊዮን ዶላር አደገ

0
813

አብዛኛዎቹ ባለሀብቶች በጨርቃ ጨርቅ እና ቆዳ ውጤቶች ላይ የተሰማሩ ናቸው።

የኢንዱስትሪያል ፓርኮች የስድስት ወራት የወጪ ንግድ ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የ42 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አስመዘገበ።
ፓርኮቹ በሳለፍነው 2011 ግማሽ ዓመት 48 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ወደ ውጪ አገራት መላክ ችለው የነበረ ሲሆን፣ በ2012 ስድስት ወራት ቁጥሩ ወደ 86 ነጥብ 5 ሚሊዮን ከፍ ሊል ችሏል። በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ 75 የውጭ አገራት ባለሀብቶች እና 12 የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በድምሩ 87 ባለሀብቶች ወደ ሥራ ገብተው እየሠሩ ይገኛሉ።

ለገቢው መጨመርም የባለሀብቶች የማምረት አቅም ማደጉን ተከትሎ የመጣ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደርቤ ደበሌ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በያዝነው ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ በተለያዩ ፓርኮች ውስጥ አዳዲስ 14 ሼዶች በኪራይ መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
አብዛኛዎቹ ባለሀብቶች በጨርቃ ጨርቅ እና ቆዳ ውጤቶች ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን የገለፀው ኮርፖሬሽኑ፣ ከእነዚህ መካከልም ከቻይና እና ከሕንድ የመጡ ባለሀብቶች ቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

አምራቾቹ ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለውጪ ገበያ የሚያቀርቡ ሲሆኑ፣ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ትዕዛዝ በቀጥታ ለውጪ ገበያ የሚያቀርቡ መሆናቸው ለአምራቾቹ የተሻለ የገበያ እድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ደርቤ ገልፀዋል።

ወደ ሥራ ከገቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በ2011 ግማሽ ዓመት 7 ሺሕ 434 የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፣ በ2012 ግማሽ ዓመት ቁጥሩ በእጥፍ ማደጉን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።

በ2012 አዳዲስ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጐች ቁጥር 14 ሺሕ 761 መሆኑ ተገልጿል። በያዝነው ዓመት ስድስት ወራትም በፓርኮች ውስጥ 65 ሺሕ 463 ሠራተኞች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማልማት መቻሉን ያስታወቀ ሲሆን፣ በእነዚህ ፓርኮች ውስጥም ስምንት የሚሆኑት አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው ተብሏል።

የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ መንግሥታዊ ተቋማት እና ድርጅቶች የሚገለገሉባቸው የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫዎችን ኮርፖሬሽኑ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

በአንድ መስኮት አገልግሎትም ባለሀብቶቹ የባንክ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮም እና ከገቢዎች እና ጉምሩክ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን የሚያገኙበት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ኮረፖሬሽኑ እና የኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚገኝበት ከተማ፣ በፓርኮቹ ውስጥ ተወካዮች ለባለሀብቶች ቅርበት እንዲያገኙ ለማድረግ መቻሉ ተጠቅሷል።
የኤሌክትሪክ አቅርቦት ዕጥረት እና መቆራረጥ ፓርኮቹ የሚጠበቀውን ያህል እንዳያመርቱ ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ የሚገለፅ ነው። ይህም ባለሀብቶቹን ለማሽኖች ብልሽት እየዳረጋቸው እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ይገለፃል።

ፓርኮቹ የተሻለ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሠራ ነው ያሉት ደርቤ፣ ከፀሐይ ኤሌክትሪክ እንዲያመነጩ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ከሌሎች አካላት ጋር እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እና በቦሌ ለሚ ኹለት ኢንዱስትሪያል ፓርክ ላይ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ወደ ፓርኮቹ የሚመጡ ባለሀብቶች ሼዶችን በሚፈልጉት መንገድ ገንብተው ወደ ሥራ የሚገቡበትን አማራጭ ለማመቻቸት በትኩረት እያሠራ መሆኑ ተገልጿል።

ሸንቴክስ የተሰኘ ግዙፉ የቻይና የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት አምራች ድርጅት በቦሌ ለሚ ኹለት ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለማምረት የሚያስችለውን የኪራይ ውል መፈራረሙ የሚታወስ ነው። በቻይና ኹለተኛው ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት አምራች የሆነው ድርጅቱ፣ በኢትዮጵያ ከ65 ሚሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ መስማማቱን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል።

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በ10 ሄክታር መሬት ላይ ሼዶችን በራሱ ወጪ በመገንባት በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መገባደጃ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here