ዋልያ የካፒታል ንግድ ሥራ ማምረቻ ማሽኖችን በዱቤ አቀረበ

0
1862

ዋልያ የካፒታል ንግድ ሥራ አክስዮን ማኅበር ለ84 የተለያዩ ዘርፎች የማምረቻ ማሸኖችን ለደንበኞቹ በዱቤ ሽያጭ ማቅረብ መጀመሩን አስታወቀ።
የዱቤ ግዥዉ የሚከናወነው አከራይና ተከራይ በሚያደርጉት ስምምነት መሠረት፣ አከራይ በተወሰነ ጊዜ የሚፈጽመው ክፍያ እየተከፈለ የካፒታል ዕቃ ተከራይ እንዲጠቀምበት የሚፈቅድ አሰራር ነው። ኢንተርፕራይዙ ተመላሹን በከፈለ ቁጥር ተመጣጣኝ የባለቤትነት መብት እያገኘ እንደሚሄድ እና መጨረሻም ክፍያውንና ተያያዥ ወጪዎችን ከፍሎ ካጠናቀቀ በኋላ የባለቤትነት መብቱን ያገኛል።

ማሽኖችን በዱቤ የሚገዙ ኢንተርፕራይዞች አገልግሎቱን ለማግኘት ስለሚጠይቁት ማሽን በቂ የአጠቃቀም ክህሎት ያላቸዉ፣ የሚገዙት ማሽን ገንዘብ መጠን ከ25 ሺሕ ብር እስከ 10 ሚሊዮን ብር ብቻ ከሆነ፣ ከሚገዙት ዕቃ ዋጋ ከ15 እስከ 30 በመቶ ቅድመ ቁጠባ መቆጠብ እንዳለባቸው እንዲሁም ለሚገዙት ማሽን ዝርዝር ማግለጫ ማቅረብ እንደሚያስፈልጋቸዉ ይጠበቅባቸዋል።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆንም በግል፣ በሽርክና፣ በአክሲዮን ማኅበር እና መሰል የንግድ አደረጃጀቶች የተመሰረቱ ጥቃቅን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መሆናቸውን የአክሲዮን ማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታሰው ዓለም ገልጸዋል።

አክሲዮን ማኅበሩ በዋናነት የሚሰጣቸዉ የዱቤ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አገልግሎቶች፣ በአምራች ዘርፍ ሲሆን ኮንስትራክሽን፣ የማዕድን ውጤቶች፣ የኬሚካል ውጤቶች፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ እንጨትና ብረታ ብረት፣ የጎማና ጎማ ውጤቶች፣ የኤሌክትሪክና ስልክ ገመዶች፣ የአልኮል ምርቶች እና ሌሎችም ማምረቻዎች ማኅበሩ ከሚያቀርባቸዉ የማምረቻ ማሽኖች መካከል ናቸው።

ማኅበሩ አገልግሎቱን የሚሰጠው በአማራ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞችና አምራች ድርጅቶች መሆኑን ጌታሰው ገልጸዋል። እንደሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገለፃ፣ አክሲዮን ማኅበሩ አገልግሎቱን በአዲስ አበባ ለመስጠት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንደከፈተ ተናግረዋል። ማኅበሩ በሌሎች ክልሎች አገልግሎቱን የማይሰጠዉ በየአካባቢዉ አገልግሎቱን የሚሰጡ መሰል ማኅበራት ስላሉ መሆኑንም የሕዝብ ግንኙነቱ አክለዉ ገልፀዋል።

የዋልያ መሥራቾችና ባለድርሻዎች የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ)፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት፣ የአማራ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት (አዉስኮድ)፣ የውሃ ጉድጓድ ድርጅት እና የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት (አመስድ) መሆናቸዉን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል።
የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም የማኅበሩን 50 በመቶ ድርሻ እንደሚሸፍንና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት 25 በመቶ፣ የአማራ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት 12 በመቶ እና የውሃ ጉድጓድ ድርጅት፣ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት 10 በመቶ እንዲሁም የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ኹለት ነጥብ አምስት በመቶ መሆኑን ጌታሰው ጠቅሰዋል። የማኅበሩ ባለድርሻዎች ድርሻ በጥቅሉ 400 ሚሊዮን ብር ነው።

ዋልያ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክስዮን ማኅበር በመጀመሪያ በካፒታል ዕቃ ኪራይ ንግድ ሥራ አዋጅ ቁጥር 103/1990 መሰረት እንደገና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 807/2005 መሰረት የተቋቋመ የፋይናንስ ተቋም ሲሆን፣ የንግድ ፈቃድ ያገኘው በ2006 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው። ሥራ የጀመረውም ፈቃዱን ባገኘ በዓመቱ በ2007 ነው።

ማኅበሩ ከ2006 እስከ 2011 ድርስ ለ9 ሺሕ 669 ሰዎች የሥራ እድል እንደፈጠረ እንዲሁም አንድ ሺሕ 998 ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ ማድረጉንና 5 ሺሕ 100 ማሽኖችን እንደገዛ ከድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። አክስዮን ማኅበሩ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ከሰጣቸዉ አምስት የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ ማኅበራት አንዱ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here