በሴቶች ጉዳይ› ሥም አይነገድ!

0
667

ኢትዮጵያ ለዓመታት በሴቶች ጉዳይ ላይ ሲገነቡ ከከረሙ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ናት። ይህንንም ለማሳካት የተለያዩ መዋቅራዊ ለውጦች የተካሄዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል የሴቶች ጉዳይን ብቻ የሚመከለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መመሠረትን ያጠቃለለ ነበር። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያልተገደበው የመዋቅራዊ ድጋፍ፣ በየክልሉ የተመሠረቱ የሴቶች ጉዳይ ቢሮዎች፣ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የተቋቋሙ የሴቶች ጉዳይ ክፍሎች እንዲሁም እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የሴቶች ቢሮዎችን እስከመከፈት የዘለቀ ነበር።

ታዲያ የሴቶችን ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ አድርገው በመንግሥት የእለት ተእለት ተግባራ ውስጥ የሴቶች ጉዳይ የማይዘነጋበትን አገር ይገነባሉ የተባለት እኚህ መዋቅሮች፣ አንዳንዴ ለኮታ ማሟያነት ሌላ ጊዜም ለፖለቲካ መሣሪያነት ሲውሉ መመለከት አዲስ አይደለም። መንግሥት ከፍተኛ በጀት ከሚመድብባቸው የተለያዩ ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው የሴቶች እኩልነት ጉዳይ፣ በየዓመቱ የሚፈስበትን ጉልበትና ገንዘብ ያህል ለምን ለውጥ ማምጣት ሳይቸል ቀር ብለን ለመጠየቅም ጊዜው ደርሷል።

እነዚህ ተቋማት ሴቶች በሥራ ቦታ ላይ ስለሚያጋጥማቸው የተለያዩ ጥቃቶች ሲናገሩም ሆነ የሥራ ቦታዎችን ለሴት ሠራተኞች ምቹ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉም አይታዩም። ከዚህ ባሻገርም መሠረታዊ የሚባሉ የተቋማቱን ሥራ በአግባቡ መምራትም ሆነ ማስተዳደር በማይችሉ ብቁ ባልሆኑ እና በአብዛኛው የፖለቲካ ሹመኞች የሚተዳደሩ መሆናቸው፣ ሌላው የሴቶችን የመብት ጥያቄዎች መመለስ እንዳይችሉ ያደረጋቸው ምክንያት ነው።

በሕግ አውጪው ላይ ሕጎች በሚወጡበት ወቅት ሴቶች ያማከለ እንዲሆን እና እንዲያበረታታ የሚያስችል እንዲሆን ሲታገሉ የሚታዩትም ጥቂት አገር በቀል የሲቪል ማኅበራት እና በግል የተሰባሰቡ ወጣት ሴቶች ናቸው። ለዚህ ማሳያም በቅርቡ ማሻሻያ የተደረገባቸው የተለያዩ ሕጎች፣ ሴቶችን የሚያበረታቱ እንዲሆኑ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦችን እና መንግሥታዊ ያልሁኑ ተቋማትን ማንሳት ይታያል።

የሴቶች እና ሕፃናት ሚኒስቴር ከዚህ በላይ እድሜው መርዘም ያለበት፣ የሴቶችን የመብት ጥያቄ ተረድተው ማስተናገድ የሚችሉ እና ሞያዊ ብቃት ባላቸው ሰዎች መመራት ሲችል እና በገጠር እና በከተማ ያሉ ሴቶች ባለንበት ዘመን የሚያጋጠሟቸውን እንቅፋት መለየት ሲችል ብቻ ነው። ኢዲስ ማለዳ ጠቅላይ ሚኒሰቴር ዐቢይ አሕመድ አዲስ የሚሾሟቸው ሚኒስትር፣ ይህንን የማያሟሉ እና ተቋሙን ብሎም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ሕዝባቸውን የእኩልነት ጥያቄ የሚመጥን ለውጥ የማያመጡ ከሆነ፣ በሴቶች ሥም ተዋቅሮ መቶ ሚሊዮኖችን የሚያባክን እንዲህ ያለው ተቋም ይፍረስ ስትል ትጠይቃለች።

የሴቶች ጉዳይ እንዲህ ባለ ተቋማዊ መልክ ብቻ አይደለም ችግሮችን እያስተናገደ ያለው። በተለይ በከተሞች አሁን አሁን እንደ ጥሩ የንግድ ስትራቴጂ ተደርጎ ለሴቶች እኩልነት ቅድሚያ የሚሰጡ የንግድ ተቋማትን መገንባት እየተስተዋለ ነው። ተቋማት በእርግጥም ያላቸውን ተሰሚነት ያክል በሴቶች እኩልነት ላይ እንደ አገር ከፍተኛ ሚና መጫወት ይችላሉ። ነገር ግን የውስጥ አሠራራቸው የጾታዊ ትንኮሳም ሆነ ሴት ሠራተኞች ከወንድ ሠራተኞች እኩል ሮጠው የሚንቀሳቀሱበት አይደለም። ይልቁብም በአደባባይ ሴት፣ ሴቶች! የሚል ገፅታ በማላበስ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ማደረጉ ሌላ አደገኛ አካሄድ ነው።

ለሴቶች ብቻ ብሎ አንድ ቅርጫፍ የከፈተ ባንክ፣ ለጀማሪ ሴት ነጋዴዎች ግን ሕይወታቸወን ሊለውጥ የሚችል የፋይናንስ ድጋፍ ካላቀረበ፣ ቅርንጫፉ ከሴቶች ይልቅ በቆነጃጅት መስተናገድ ለሚፈልግ ወንድ ደንበኛቸው ይበልጥ መች መሆኑ አይቀርም።

ይህም ሥራ አስፈፃሚው በዓለም አቀፍ ብሎም በአገር ውስጥ ልሂቃል ዘንድ ሙገሳ ያስቸረውን 50 በመቶ ሴት የካቢኔ አባላት ሹመት እና እነዚህ ሌሎች ኤጀንሲ እና መሰል ተቋማት ላይ ያለውን ሹመት በግርድፉ ማየት ብቻ ያስረዳዋል። የሚታይ የሚዳሰሰው የካቢኔ ጉዳይ ላይ የተወሰደው እርምጃ፣ ቢያንስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ እንኳን ሲደገም አልታየም። የከተማ አስተዳደሩ ካሉት ከዐስር በላይ የካቢኔ ወንበሮች ሦስቱ ላይ ብቻ ነው ሴት መሪዎችን ማግኘት የሚቻለው።
ታዲያ በሴቶች ሥም የሚፈሱት እነዚህ ሁሉ ሃብቶች፣ የት ነው ውለው የሚያደሩት ብልን ብናይ፣ በአብዛኛው ኮፍያ እና ቲሸርት፣ ብሎም የትልልቅ ሆቴሎች የውይይት መድረክ ማዳመቂያ ናቸው።

እነዚህን ነገሮች ጎልተው የሚነሱ በመሆኑ አነሳን እንጂ፣ ከሴቶችም የሚጠበቁ ነገር ግን ሲሆኑ ያልታዩ ተግባራት አሉ። በተለይም በአረአያነት ሊቀመጡ ይችላሉ፣ ምሳሌ ይሆናሉ የተባሉት በዚህ ተወቃሽ ናቸው። እነዚህ ሴቶች በብዙ ጥረት ነጥረው የወጡት ሆነው፣ ከራሳቸው አልፎ ላለው የሌሎች ለውጥ እዚህ ግባ የማይባል ጥረት እያደረጉ አይደለም። ይህም ጉዳዩን ቢያንስ ጎረቤት አገሮቻችን ባደረሱበት ደረጃ እንኳን እንዳናደርሰው የገደበን ነው ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በኃላፊነት ላይ ያሉ ሴቶች ከስራቸው ያሉትን በአግባቡ በመምራት እና በማስተማር ለነገ ማዘጋጀት ግድ ይላቸዋል።

በኢትዮጵያ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች 90 በመቶው ወንዶች ናቸው። ይህ ለምን ሆነ? የተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ሲጠየቁ፣ ‹‹እኛ እድሉን ሰጠተናል። ነገር ግን ሴቶች እሺ አይሉም።›› ሲሉ ይሰማል። የሴቶች ጥያቄ አንዱ የሚፈታው በሕግ አውጪው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በሚያደርጉ እና የመብት ጥያቄዎችን በሰነድ አስደግፈው በሚያቀርቡ፣ ከአንድ ጊዜ ባለፈ ለትውልድ የሚተላለፍ መልስ ተቀብሎ ማኖር ሲቻል ብቻ ነው።

ከዚህም በላይ መዘናጋትም አለ። ከከተማ ራቅ ባሉ ገጠራማ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የሴት ል ግርዛት፣ ጠለፋና የመሳሰሉ ድርጊቶች በሴቶች ላይ አሁንም የሚፈጸሙ ድርጊቶች ናቸው። ነገር ግን የሌሉ ያህል ሲነሱ አይሰሙም። በተመሳሳይ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የሴት ተማሪዎች ቁጥር ብዙ የሚባል ቢሆንም፣ እያገፋ በሄደ ቁጥር እየቀነሰ ሄዶ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲደርስ በእጅግ አንሶ ይገኛል። የዚህን ምክንያት ለመቃኘትና መፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ የተደረገ ጥረት ግን እምብዛም አይታይም።

አሁን አሁን በከተማው ያለው የሴቶች ጥያቄም በገጠር ያለችውን ሴት የማያውቅ እና ያላገናዘበ ነው ብለው የሚሟገቱም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ነገር ግን የከተሜው እንቅስቃሴ በተለይ አጀንዳ አውጪዎች ላይ የሚኖረው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። ይህም ሆኖ ግን አሁንም መሠረታዊ የሰው ልጆች መብቶች ያልተከበሩላቸውን የኢትዮጵያ ሴቶችን ያማከለ እንቅስቃሴ በከተማው እስካልተጀመረ ችግሩ ይቀጥላል።

በአንጻሩ እንዲሆን ግን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጀምሮ፣ እንደ በሬ ኑሮ በየዓመቱ ቁጥር አቅዶ ቁጥርን ከመዘገብ ባለፈ፣ ተጨባጭ ለውጥ ለማጣት መሠራት አለበት። በፖለቲካውና ኢኮኖሚው ላይ ባለሥልጣናትን በመቀያየርና ሥራቸውንም በመከታተል መገናኛ ብዙኀንን ጨምሮ የሚመለከታቸው ሁሉ እንደሚዘምቱት፣ በሴቶች ጉዳይ የሚሠሩ ተቋማትና ቢሮዎች፣ የክልል አስተዳደሮችና አመራሮችን በመከታተል ሥራቸውን መቃኘት ያስፈልጋል።

ከግማሽ በላይ የሆነውን የማኅበረሰብ ክፍል የሚሸፍኑ ሴቶች መብት ሊከበር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች። እይህም እንዲሆን ከአጥፊዎችና መብትን ከሚጥሱ ግለሰቦች ባልተናነሰ፣ መብትና እኩልነትን እንዲያመጡ የተቋቋሙ ተቋማት መሥራት ያለባቸውን ባለመሥራት ጥፋት እያጠፉ ነውና፣ ልብ እንዲሉ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ለሴቶች ጉዳይ ነው በሚል በሴቶች ሥም መነገድም ይቁም ትላለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here