የገቢዎች ሚኒስቴር ቢሜት የተባለ የኤሌክትሪክ ገመድ አምራች ድርጅት በኹለት መሥራቾቹ መካከል አድርጌዋለሁ ባለው የ900 ሺሕ ብር የድርሻ ስጦታ ላይ የጣለው 570 ሚሊዮን ብር ግብር፣ ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ እና በጋራ ውሳኔ እንዲሰጥበት ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር ወሰነ።
በኹለት ቱርካውያን ወንድማማቾች መካከል በተደረገ የባለቤትነት ድርሻ ዝውውር ድርጅቱ 900 ሺሕ ብር ነው ይበል እንጂ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ግን ድርጅቱ ያስመዘገበው ካፒታል ኹለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ስለሆነ እና ግለሰቦቹም የዚህን አንድ አራተኛ በመሻሻጣቸው ምክንያት የስድስት መቶ ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ ነው ሲል ሞግቷል። በዚህም መሠረት 30 በመቶ ወይም 190 ሚሊዮን ብር ግብር እና 190 ሚሊዮን ብር ቅጣትን ጨምሮ፣ 570 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ሊከፍሉ ይገባል ሲል ወስኗል።
የቢሜት ኢነርጂ ቴሌኮም አምራች እና ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ሞገስ ፈየራ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ቢሜት ያደረገዉ ሽያጭ እንዳልሆነና የባለቤትነት ዝውውር ነው። ድርጅታቸውም ይህ ተገቢ አይደለም በሚል ለገቢዎች ሚኒስቴር ቅሬታ ሰሚ ቦርድ ቅሬታ አቅርበው መታየቱንም ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴርም በጉዳዩ ላይ የሕግ ማብራሪያ ለመስጠት በቀረበለት ጥያቄ መሰረት፣ በሚኒስቴር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በተፈረመ ደብዳቤ ለጊዜው የግብር ውሳኔው አፈፃፀም ታግዶ ይቆይ ሲል ወስኗል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ ክፍል ኃላፊ ቦቹ ስንታየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ቢሜት በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ያለው የቱርክ ድርጅት መሆኑን ገልጸዉ፣ በኢትዮጵያ ያለው ቅርንጫፍ ዋና ድርጅት ስላልሆነ አክስዮን መሸጥ ወይም ማስተላለፍ አይችልም ሲሉ አስረድተዋል። ድርጅቱ ያቀረበው ጥያቄም ገና ያለመመርመሩን ገልጸው፣ ከላይ ሲታይ ግን ምክንያታዊ ስለሚመስል ለጊዜው ውሳኔው እንዲታገድ መወሰኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ቱርክ በዜጎቻቸው ላይ ተደራራቢ ግብር እንዳይጣል ውል ያላቸው ሲሆን፣ ይህንንም ኢትዮጵያን ወክሎ የሚያከናውነው የገንዘብ ሚኒስቴር ነው።
የአክስዮን ድርሻ ሻጩም ገዥውም ቱርካዊ ናቸው ያሉት ቦቹ፣ በኹለቱ አገራት ስምምነት መሰረት አክሲዮን ገዥዉ የአንዱ አገር ኗሪ መሆን እንዳለበት ገልጸው፣ ስምምነቱን መሰረት አድርጎ ኗሪነቱ ተረጋግጦ እንደሚወሰን ጠቅሰዋል። በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችሉ መረጃዎች በተገቢዉ ሁኔታ እንደተሟሉም ውሳኔ እንደሚሰጥ ቦቹ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
በኹለቱ አገራት መካከል ያለው የተደራራቢ ግብር ማስቀሪያ ውል ላይ ተመስርቶ የገንዘብ ሚኒስቴር የኹለቱ ወንድማማቾች የመኖሪያ ቦታ የት ነው የሚለው ላይ ከወሰነ በኋላ፣ ግብሩን የመሰብሰብ ሥልጣን ያለው የትኛው አገር ነው የሚለው ላይ እንደሚወሰንም ቦቹ አስረድተዋል።
ቢሜት በ2011 አዲስ አበባ የተመሠረተ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ትልቁ የኤሌክትሪክ ገመድ (ኬብል) አምራች ድርጅት መሆን ችሏል። ቢሜት የቴሌኮም ገመዶችን እና የፋይበር ገመዶችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት የኤሌክትሪክ ገመዶችን እንዲሁም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ማምረት ይችላል።
ድርጅቱ በኢትዮጵያ ሥራ መሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እ.አ.አ በ2012 ተፈራርሞ፣ በ2013 ምርት ማምረት የጀመረ፣ በሰበታ ሐዋሳ ወረዳ ዲማ ጎራነዳ ቀበሌ የሚገኝ፣ ኬብል አምራች የግል ድርጅት ነው። ቢኤምኢቲ ያለዉ ሀብት በግምት ሦስት ቢሊዮን ብር መሆኑን ከድርጅቱ ድረ ገፅ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።
ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012



