የኮሮና ቫይረስ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እንዳይከናወን እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ተገለፀ።
በህዳሴ ግድብ የብረታ ብረት ሥራዎች የሚያከናውነው ሲኖ ሀይድሮ የተባለ የቻይና ኮንትራክተር ኮሮና ቫይረስ በተከሰተባት ዉሃን ግዛት ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ፣ ከቦታው ባለሙያዎችን እና የግንባታ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ እንዳልተቻለ ተገልጿል።
የግንባታ እና የባለሙያዎች በታሰበው ጊዜ አለመድረስም በመጪው ክረምት እንደሚጀመር ሲገለፅ የቆየው የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል የተባለ ሲሆን፣ በቻይና በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተግዳሮት ገጥሞታል።
‹‹የሰው ኃይል እና የግብአት እጥረት ቢያጋጥመንም በአገር ውስጥ ማምረት በምንችለው መጠን በማምረት እየተረባረብን ነው›› ሲሉ የህዳሴው ግድብ የሜካኒካል እና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኤፍሬም ወልደኪዳን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። ፕሮጀክቱን በመገንባት ላይ ከሚገኙት ኮንትራክተሮች መካከል ከሦስት በላይ የሚሆኑት ቻይናውያን መሆናቸው፣ በግድቡ ግንባታ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በቫይረሱ ምክንያት የቻይና ፋብሪካዎች የፋብሪካ እና የቢሮ ሥራዎች ማቆማቸውን የጠቆሙ ሲሆን፣ የብረታ ብረት ሥራዎችን የሚሠራው ኮንትራክተር ቫይረሱ በተከሰተባት ግዛት ውስጥ ያለ መሆኑ ዕቃዎችን እና የሰው ኃይል በጊዜው አለማድረሱ የግድቡን የዉሃ ሙሌት ዕቅድ ወደ ቀጣይ ዓመት ሊያዘዋውረው እንደሚችል ጠቁመዋል።
የግድቡ የመጀመሪያ የሙሌት ሥራ በአባይ ወንዝ ላይ ከፍተኛ የፍሰት መጠን በሚኖርበት ከመጪው ሐምሌ 2012 እስከ መስከረም 2013 በክረምት ወራት እንደሚከናወን ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፣ በቻይና በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የዉሃ ሙሌት ስራው ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላልም ብለዋል።
ግድቡ በዚህ ዓመት ውሃ ይሞላል የሚለው ዕቅድ ምርቶቹን አገር ውስጥ በማምረት በሚገኘው ውጤት ላይ የሚመሰረት መሆኑን የገለፁት ኤፍሬም፣ የሜካኒካል እና የብረታ ብረት ሥራዎችን ከግድቡ ውሀ ከመያዝ ሥራዎች ጋር አያይዞ ለመሥራት እየተሞከረ ነው ብለዋል።
የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና የሀይድሮ ሜካኒካል ሥራዎችን ላይ ቮይት ሀይድሮ ሻንጋይ፣ ቻይና ኤክስ ዲ ግሩፕ እና ሲኖ ሀይድሮ የተሰኙ ተቋራጮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ጄነራል ኤሌክትሪክ የተሰኘ የአሜሪካን ኮንትራክተር በኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ላይ እየተሳተፈ ሲገኝ፣ ሳሊኒ የግድቡን የሲቪል ሥራዎች በማከናወን ላይ ነው።
የቫይረሱ መከሰት የብረታ ብረት ሥራዎችን ለማከናወን እና ባለሙያዎችን ከቻይና ለማስመጣት መጠነኛ እክል ፈጥሯል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ኦሮ፣ ከቻይና ዕቃዎችን በመርከብ ለማምጣት እክል ፈጥሯል ብለዋል።
አክለውም የብረታ ብረት ምርቶችና በአገር ውስጥ አምርቶ ለመተካት እየተሞከረ ነው ያሉ ሲሆን፣ ባለሙያዎችን ከቻይና የማስመጣቱ ጉዳይ መጠነኛ ተፅዕኖ መፍጠሩን አሰታውቀዋል። ችግሩንም ለመቅረፍ በተጨማሪ ከህንድ እና ከሌሎች አገራት በማምጣት ላይ ነን ብለዋል።
‹‹እኛ በእቅዱ መሰረት ግድቡ ውሃ መያዝ የሚችልበት ደረጃ ላይ ለማድረስ እየጣርን ነው›› ያሉት ኢንጅነር ክፍሌ፣ ግድቡ በታቀደለት ጊዜ ውሃ የመያዙ ጉዳይ በውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚወሰን እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቀጣዩ ክረምት ከባህር ጠለል በላይ እስከ 560 ሜትር ከፍታ እንደሚደርስና አራት ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሀ እንደሚይዝ ይጠበቅ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ግድቡ በአጠቃላይ ከሚይዘው 74 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ውስጥ 5 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆነውን ብቻ የሚሸፍን ነው።
ይህም የግድቡ የመጀመሪያ ኹለት ኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን ወደ ሥራ በማስገባት 260 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚያስችል ነው። ለዘጠኝ ዩኒቶች ኤሌክትሪክ ማመንጨት የሚያስችሉ ተርባይኖች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 71 በመቶ ላይ ደርሶ ይገኛል።
እንደ ግድቡ ሜካኒካልና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኤፍሬም ገለፃ፣ የወንዙን የ95 ዓመታት ፍሰት በማጥናት በአማካይ 49 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ሲሆን የወንዙ ፍሰትም በደረቃማ ወቅቶች ላይ እስከ 20 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ይደርሳል።
ጥሩ የዝናቡ ሁኔታ በሚኖርበት ወቅት ደግሞ ዓመታዊ ፍሰቱ እስከ 63 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ የሚደርስ ነው። አሁን ወደ ተፋሰሱ አገራት ከሚፈሰው መጠን ስምንት በመቶ በመሆኑ፣ በተፋሰሱ አገራት ላይ የሚያደርሰው የከፋ ተፅዕኖ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም ብለዋል።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ ታዛቢነት በግድቡ ሙሌት፣ አለቃቀቅ እና የግድቡ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ዙሪያ የተለያዩ ሐሳቦችን በማቅረብ መደራደር ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
በተገባደደው ሳምንትም የውጪ ጉዳይ፣ የውሃ መስኖ እና ኢነርጀ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባልደረቦች እና በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ ሲሳተፉ የነበሩ ባለሞያዎች፣ ተሰባስበው በግድቡ ላይ ስለሚደረጉ ድርድሮች ለመገናኛ ብዙኀን አብራርተዋል።
በጠቅላይ ሚኒሰትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው በዚህ መግለጫ ላይ፣ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዳሉት፣ የውሃ ሙሌቱ እንዳይጀምር የሚያደርግ ምንም አይነት ውል ከዚህ በፊት ተደርጎ አያውቅም። አሁንም ድርድር አይደረግበትም።
ስለሺ እንደሚሉትም፣ የውሃ ሙሌት ከኢትዮጵያ የግንባታ ሂደት ጋር ብቻ የሚያያዝ እንጂ የአሜሪካ መንግሥት እንዳለው ከሙሌት በፊት በሚደረጉ ስምምነቶች ላይ የሚመሰረት አይደለም። የውሃ ሙሌት የንግግር መሰረት የሚሆነው በመደበኛው ጊዜ ሳይሆን የድርቅ ጊዜያት እና ግድቡ አንድ ጊዜ የሚያስፈልገውን ያክል ውሃ እስኪይዝ ባለው ጊዜ እንደሆነም ያስረዳሉ።
የድርድሩ ይዘትም በተለይ የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት የሚመለከት እና በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱ ለ10 ዓመት ብቻ የሚቆይ ሆኖ እንዲፈረም አቋም የያዘችበት ነው። ይህ ድርድር የመጀመሪያውን ሙሌት የሚመለከት እና የህዳሴ ግድቡን ብቻ የሚመለከት ብቻ እንዲሆን በግልፅ አስቀምጣበታለች። በተጨማሪም ቀደም ሲል የተደረጉ ስምምነቶችን እውቅና የማይሰጥ ስምምነት እንደሚሆንም በግልጽ በስምምነቱ ላይ ተቀምጧል።
ይህ የስምምነት ሰነድም ሙሉ ለሙሉ ሳይታይ የተወሰነው ብቻ ተነጥሎ ለፊርማ በመቅረቡ፣ ኢትዮጵያ ለመፈረም ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች። ከዚህ ባሻገርም በሦሰተኛ ወገን ስምምነቱ ይዘጋጅ የሚል ጥያቄ መምጣትን ኢትዮጵያ ተቃውማለች።
ቀጣይ የድርድር ጊዜ መቼ እንደሚሆን ባይታወቅም፣ ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ውይይቶችን ሳታጠናቅቅ ወደ ድርድር እንደማትመልስ ያስታወቀችው ኢትዮጵያ፣ የግድቡን ግንባታ በማፋጠና በዘጠነኛው ዓመት የመጀመሪያወን ዙር ውሃ በመያዝ ኃይል እንደምታመነጭ ይጠበቃል።
ቅጽ 2 ቁጥር 70 የካቲት 28 2012



