ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል!

0
856

የጤና ዘርፋቸው ያልጎለበተ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች በበለፀጉት አገሮች በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን ኮቪድ-19 ቫይረስን ለመቋቋም ያላቸው ዝግጁነት እጅጉን አናሳ ነው። በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ከፍተኛ ክትትል በሚያስፈልጋቸው ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ ሊያገኟቸው የሚገቡት እንደ ቬንቲሌተር ዓይነት የሕክምና ማገዣዎች ቁጥር አናሳ በመሆኑ፣ እነዚህን ዓይነት ሰዎችን ለማዳን ያለው አቅም በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ዓለም የደረሰበትን የሕክምና ቴክኖሎጂ ታጥቀው ምንም የማይበግራቸው የሚመስሉት የበለፀጉ አገራት እንኳ ከፍተኛ የሕክምና መሣሪያዎች እጥረት አጋጥሟቸው ዜጎቻቸው በሺሕዎች ሲሞቱ ለማየት ተገደዋል። በመሆኑም የሕክምና ዝግጁነት ቫይረሱን ለመቋቋም አለን የምንለው ጠንካራ ጎናችን እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

ባለንበት ሁኔታ ውስጥ ቫይረሱ በሰፊው ወደ ኅብረተሰቡ ዘልቆ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ የሚቻለንን ያህል መሥራት፣ ጉዳት የሚደርስበትን ወገናችንን ቁጥር ለመቀነስ የተሻለው አማራጭ ሊሆን ይችላል። ይህንን ለማሳካት ደግሞ ከግለሰቦች ጀምሮ እስከ መንግሥት አካላት ድረስ ያሉ የተለያዩ ባለድርሻዎች የራሳቸውን ሚና በተገቢው መንገድ ሊወጡ ይገባል። ነገር ግን እነዚህ አካላት ሚናቸውን እየተወጡ ነው ብሎ ደፍሮ ለመናገር የሚያስችል ሁኔታ መኖሩ አጠራጣሪ ነው።

ጉዳዩን ከበላይ ወዳሉ አካላት ስንጀምር፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ የሆኑት ንጉሡ ጥላሁን በዚህ ሳምንት ነበር ከተለያዩ መገናኛ ብዙኀን የመጡ ጋዜጠኞችን የቫይረሱን ስርጭት በመቆጣጠር ዙሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያወያዩት። በዚህ ውይይት ላይም ከመንግሥት በኩል በየቀኑ ጠዋት ከ4 እስከ 5 ሰዓት ባለው ጊዜ የየቀኑ መረጃ እንደሚሰጥ፣ ጉዳዩ አስቸኳይ መሆኑን እንደሚገነዘብ እና መረጃ እንደማይደብቅ አፅንኦት ሰጥተው ገልፀው ነበር።

ይህንን ካሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን የየቀኑ መረጃ እንኳን ተዘሏል። ጉዳዩ አስቸኳይ መሆኑን መገንዘባቸውን ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ ሁኔታም በአዳማ ከተማ ቫይረሱ እንዳለባቸው የታወቁት ሰው ጉዳይ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ ከቆየ በኋላ በነጋታው ነው መግለጫ የተሰጠበት። ይህንን ዓይነቱ መረጃን አዘግይቶ የመስጠት አዝማሚያ ሰዎች መረጃ ሰምተው ራሳቸውን ለመጠበቅ ወይም ለሌሎች ላለማስተላለፍ ሊያደርጉ የሚችሉትን እርምጃ የሚገድብ በመሆኑ የብዙዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነው።

በመሆኑም መረጃ ማዘግየት እንደመደበቅ ሊቆጠር የሚገባበት ጊዜ ነው። መረጃዎችም በሚሰጡበት ጊዜ ሊያናግሯቸው ከጠሯቸው መገናኛ ብዙኋን አብዛኞቹን ገለል ባደረገ መልኩ ለመንግሥት እና ለፓርቲ ቅርብ የሚባሉትን ብቻ ተጠቅሞ መስጠቱ ፍትሃዊ አካሔድ አይደለም።

የራስን ኃላፊነት ከመወጣት አንጻር ሌላ በዚህ ሳምንት የታየው ችግር ደግሞ በገዢው የብልጽግና ፓርቲ በኩል ነው። ምንም እንኳን የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ራሳቸው ስብሰባዎችን ማድረግ የተከለከለ መሆኑን ለሕዝብ ያሳወቁ ቢሆንም፣ በዚህ ሳምንት የተለያዩ ቦታዎች የራሳቸው ፓርቲ ሰዎች ትላልቅ ስብሰባዎችን ሲያካሂድ ከርሟል።

የቫይረሱ ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች ተፈጻሚነት በከፊል ከሆነ የሚኖራቸው ውጤትም አጥጋቢ እንደማይሆን ግልጽ ነው። በመሆኑም ይቆማሉ ተብለው ቢጠበቁም እስከ አሁን ሲቆሙ ያልታዩት የብልጽግና ፓርቲ ስብሰባዎች በአስቸኳይ ሊቆሙ ይገባል።

ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ሌላ ከፍተኛ ክፍተት ያሳዩት ደግሞ ነጋዴዎች ናቸው። ያለአግባብ ትርፍን ለማጋበስ ሲባል በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ቫይረሱን ከመከላከል ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ምርቶችን እንዲሁም የፍጆታ እቃዎችን እጥረት በመፍጠር እና ዋጋ እጅግ በማናር ሕዝብን እያማረሩ ያሉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች ታይተዋል።

ሌሎች ደግሞ ባዕድ የሆኑ ነገሮችን ከምግብ ነክ እና የጽዳት ዕቃዎች ጋር በማቀላቀል ለሕዝብ ቅንጣትም ያህል ርህራሄ እንደሌላቸው በሚያሳይ መንገድ ለመክበር እየጣሩ ነው። እንዲህ ዓይነት የችግር ጊዜያት የሚታለፉት ሰዎች ለሌሎች ሰዎች ሕይወት በሚኖራቸው ተቆርቋሪነት እና የኃላፊነት ስሜት እንጂ በሀብት ክምችት እንዳልሆነ ወደ ተቀረው ዓለም ዞር ብሎ በማየት መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም የአገራችን ነጋዴዎች ከሕግ ጋር የለመዱትን ድብብቆሽ አቁመው አገራችን ያሉባት ብዙ ችግሮች ላይ ሌላ ችግር ከመከመር ሊቆጠቡ ይገባል።

ግለሰቦችም ያለባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ካልሆኑ አካላት መካከል በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። ከመንግሥት የሚሰጡን ራስን ከቫይረሱ የመጠበቂያ እርምጃዎች ካለመከታተል፣ ቢከታተሉም ቸል ከማለት ወይም ጉዳዩን እንደ ሃይማኖት ዓይነት ሌላ ጉዳይ ጋር በማገናኘት የራስንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት አደጋ ላይ መጣል በሰፊው የሚታይ የኃላፊነት ማጉደል ተግባር ነው።

በታክሲ ሰልፎች ላይ ርቀትን ሳይጠብቁ መቆም፣ እጅን በንጽህና መጠበቂያዎች ያለማጽዳት፣ በሃይማኖት ተቋማት የሚደረጉ የሃይማኖት ሥነ ስርዓቶች ላይ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ መንቀሳቀስ እና በሽያጭ ቦታዎች ላይ ተፋፍጎ መንቀሳቀስ በዚህ ሳምንት ሲሰጥ ከቆየው ማስጠንቀቂያ በተቃራኒ ግለሰቦች ሲያደርጓቸው የቆዩ ለቫይረሱ መተላለፍ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ አጋጣሚዎች ናቸው።

የማኅበረሰብ ትልቅ አካል የሆኑት ግለሰቦች ራሳቸውን ቫይረሱን ለመከላከል በሚያስችል ሁኔታ ሊገሩ ካልቻሉ ችግሩን ወደ ቤተሰባቸው፣ ወዳጆቻቸው እና ወደ ሰፊው ማኅበረሰብ እንደሚወስዱ ሊያቅውቁና ሊረዱ ይገባል። የአንድ ሰው መዘናጋት የብዙዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ሊዳርግ የሚችል በመሆኑ በመከላከያነት የሚገለጹትን እርምጃዎች ለመከወን ግለሰቦች ቀናኢነት ሊኖራቸው ይገባል።

በአንጻሩ ሁሉም ሰው እኩል የኃላፊነት ስሜት ይሰማዋል ብሎ መገመት ስለማይቻል በመንግሥት የተጀመሩ እንቅስቃሴን ሊቀንሱ የሚችሉ እርምጃዎች ሊቀጥሉ ይገባል። በዚህ ረገድ ቀጣዩ እርምጃ መሆን ያለበት ነገር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በኔዘርላንድስ ሔግ የሕገ መንግሥት እና የምርጫ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት አደም ከበደ (ዶ/ር) እንደሚሉት መንግሥት ያለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰዎችን የመንቀሳቀስም ሆነ ሌላ ሰብዓዊ መብት መገደብም ሆነ መንጠቅ አይችልም። በዚህም መሠረት ቫይረሱ አለባቸው ተብለው የተጠረጠሩም ሆኑ ያለባቸውን ሰዎች ለይቶ ማቆየት፣ መዝናኛ ቦታዎች ላይ ሰዎች እንዳይሄዱ ማገድ፣ የሰዓት እላፊ ማስቀመጥ፣ የተማሪዎችን የመማር መብት መገደብ እንዲሁም አጠቃላይ የእንቅስቃሴ እገዳ ማድረግ የሕግ መሠረት ያስፈልጋቸዋል።

ምንም እንኳን ኅብረተሰቡ አስፈላጊነታቸው ቢያስማማውና የመንግሥትን ትዕዛዝ የሚቀበል ሆኖ ቢገኝም፣ ያለ ሕጋዊ መሠረት ይህንን ጥሰው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች በሕግ ፊት ጥፋት እንዳጠፉ ሊታዩ አይችሉም ባይ ናቸው፤ አደም። በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ የሕግ መሠረቱን የሚሰጥ እና መንግሥትም ቢሆን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ እንደሚንቀሳቀስ የሚያረጋግጥ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን መታወጅ ተከትሎ ኮማንድ ፖስት ሊቋቋም ይገባል። ይህም ኮማንድ ፖስት በዚህ ማኅበራዊ መረጋጋት በጎደለበት ጊዜ ደኅንነትን ለማስከበር የሚረዳ ከመሆኑም በተጨማሪ በክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ላይ መዋቅር የሚኖረው ስለሆነ መረጃዎችን እና ትዕዛዞችን በቀላሉ ለማንቀሳቀስ ያስችላል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኮማንድ ፖስቱ በኩል ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ግን የሕግ አስፈጻሚ አካላቱን እና ወታደሮችን ስለ ሰብዓዊ መብቶች እና ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓላማ ማሳወቅ ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት በኃይል የሕዝብን ተቃውሞ ለማስቆም ሲሰማራ የነበረው ይኼው ኃይል አሁንም በተመሳሳይ ስሜት መሰማራት እንደሌለበት ግልጽ ሊደረግለት ይገባል።

ቫይረሱ አገራችን መግባቱ በታወቀበት ኹለት ሳምንት ውስጥ ከመንግሥት አካላት አንስቶ እስከ ግለሰቦች ድረስ ሁላችንም ሰፊ ስርጭት እንዳይኖር ልንወጣ የሚገባንን ሚና በተገቢው መንገድ አልተወጣንም። ነገር ግን ከዚህ ወዲያ ይህ አጠቃላይ መዘናጋት ሊቆም እና ከሌሎች አገሮች ስህተት ተምረን በጋራ ውጤታማ ሥራ እንድንሠራ ስትል አዲስ ማለዳ ጥሪ ታቀርባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here