በተጭበረበሩ ቼኮች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ተመዘበረ

0
557

ከ2011 የመጨረሻ ወራት ጀምሮ በተደረገ ክትትል በቼክ ማጭበርበር ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ መመዝበሩን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። በተደረገው ክትትልም በቁጥጥር ስር ውለው ክስ የተመሰረተባቸው 30 የክስ መዝገቦች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል።

ከቼክ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታዩ ካሉ ክሶች ውስጥ በተደረገባቸው ምርመራ በንግድ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ዳሽን ባንክ እና ሌሎች በርካታ ባንኮች የማጭበርበር ድርጊቱ እንደተፈጸመባቸው ዐቃቤ ሕግ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ድርጊቱ የባንኮቹን ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ተሳታፊ በሚያደርግ መልኩ የሚከናወን ሲሆን፣ የድርጊቶቹ ፈጻሚዎች ከባንኮቹ ደንበኞች ቼኮቹን በመስረቅ ወይም በማጭበርበር ካገኙ በኋላ ሐሰተኛ መታወቂያዎችን እና ሌሎች ሰነዶችን በማዘጋጀት ወደ ባንክ ቅርንጫፎች በመሄድ ገንዘብ ወጪ ለማድረግ በሚሞክሩበት ጊዜ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

ባንኮች ገንዘብ ለመክፈል ወደ ቼኩ ባለቤት በሚደውሉበት ወቅት ተጠርጣዎቹ ከኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች ጋር በመመሳጠር ስልኮችን የሚያዘጉ ሲሆን፣ የቼኮቹ ባለቤቶችን ስልክ ቁጥር ራሳቸው በመውሰድ ባንኮቹ ክፍያ እንዲፈፅሙ ራሳቸው ተጠርጣሪዎቹ እንደሚያዙም ከዐቃቤ ሕግ የተገኘው ምርመራ ያስረዳል።
በሌላ በኩል ደግሞ ተጠርጣሪዎቹ ሐሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት የደንበኞችን ሂሳብ ለማንቀሳቀስ ውክልና የተሰጣቸው በማስመሰል ሂሳብ የማዛወር ሥራ እንደሚሠራም ተገልጿል።

ከእነዚህ 30 የክስ መዝገቦች ላይም በእያንዳንዳቸው መዝገቦች ከአንድ እስከ 19 ብዛት ያላቸው ተጠርጣሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ80 በላይ የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

20 የሚሆኑ መዝገቦች ክስ ተመስረቶባቸው፣ አብዛኛዎቹ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው። ወደ ውጪ አገራት የሸሹ ተጠርጣዎችን ለመያዝም ፌዴራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በተገኙበት ይዞ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ መሰጠቱ ተገልጿል። ተመዘበሩ ከተባለው ገንዘብ ውስጥ ከ100 ሚሊዮን በላይ ቼክ የተመዘበረ ሲሆን ከነዙም ውስጥ ከባንክ ሳያወጡ ከአንዱ ወደ ሌላው አካውንት በማዘዋወር 40 ሚሊየን ተደርሶበት በፍርድ ቤት መታገዱን ገለጸዋል፡፡
ሃሰተኛ ቼክ እና መታወቂያ በመያዝ ብሩን ሊያወጡ ሲል በጥ 10 ሚሊዮን ብር በሙከራ ደረጃ መቅረቱንም ለማወቅ ተችሏል።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀሎች ምክትል ዳይሬክተር ዘላለም ፍቃዱ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ድርጊቶቹ በሐሰተኛ ሰነዶች የሚፈፀሙ በመሆናቸው ወረዳዎች የግለሰቦችን ማንነት እና ነዋሪነት ሳያጣሩ እና ሳያረጋግጡ መታወቂያዎችን መስጠት የለባቸውም። ኢትዮ ቴሌኮምም ግለሰቦች በራሳቸው ሥም ያወጧቸውን ሲም ካርዶች በሚያዘጉበት ወቅት ትክክለኛውን ማጣራት ሊያደርግ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች የወንጅል ድርጊቶች እየታዩ እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለአብነት ያህልም ቢሮዎችን ሰብሮ በመግባት ፊርማዎችን አስመስሎ መፈረም፣ ሐሰተኛ ቼክ በማዘጋጀት እና ውክልና እንደተሰጣቸው አድርጎ መፈረም የወንጀል ድርጊቱ ከተፈጸመባቸው መንገዶች ተጠቃሽ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ተጠርጣሪና ተከሳሾች በአሁን ወቅት ምርመራቸው በሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የምርመራ ሂደቱ እንደተጠናቀቀም ብይን እንደሚሰጥበት ዘላለም ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here