መነሻውን በቻይናዋ ዉኀን ግዛት ያደረገው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አራት ወራት እየተጠጋ ባለው የጊዜ ቆይታው ዓለምን በማዳረስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በማጥቃት በአጠቃላይ ከ55 ሺሕ በላይ ሰዎችን በመግደል የአስፈሪነት ግስጋሴውን ቀጥሏል። ትኩረት ባያገኝም ወረርሽኙ ከያዛቸው መካከል ከ220 ሺሕ በላይ ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውም ታውቋል።
አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥም ወረርሽኙ ተከሰተ ከተባለበት ከሦስት ሳምንታት በኋላ በቫይረሱ የተጠቁት ሰዎች ቁጥር አራት ዐሥርት ተቃርቧል። በቫይረሱ ከተያዙት ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በተከታታይ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በቫይረሱ በከፍተኛ ቁጥር ከተጠቁት እና ከፍተኛ የሞት ቁጥር ካስመዘገቡት አሜሪካ፣ ጣሊያን እና ስፔን እንዲሁም ወረርሽኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ካጠቃባቸው ደቡብ አፍሪካ እና ግብጽ በንጽጽር በኢትዮጵያ የቫይረሱ ስርጭት ገና አስደንጋጭ የሚባል ደረጃ እንዳልደረሰ መረዳት ይቻላል። ይሁንና በዓለም ጤና ድርጅት፣ በጤና ሚኒስቴር እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡና መተግበር ያለባቸው ምክሮች በቸልታ ከታለፉና ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ የጉዳቱ መጠን መጨመሩ የማይቀር ነው። ኅብረተሰቡም ተለምዷዊ ከሆኑት የኑሮ ዘየዎቹ መካከል ለወረርሽኙ መስፋፋት ምቹ ናቸው የተባሉትን በመተው የመከላከል ዘመቻው አካል መሆን ይገባዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከሚያደርሰው አካላዊ ስቃይና ሞት ባልተናነሰ የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ከፍተኛ እንደሆነ የአገራት ተመክሮ ያመላክታል። የምስቅልቅሉ ከፍታ በተለይ ወደ ማኅበራዊ ቀውስነት የሚለወጥ ከሆነ በከፍተኛ ደረጃ አገራትን የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን ከቀውሱ ለመውጣት የሚደረጉ ጥረቶችን ሩቅ ሊያደርግ የሚችል ነው፡፡ በመሆኑም አዲስ ማለዳ ወረርሽኙን ከመከላከል ጎን ለጎን ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር በልዩ ትኩረት መሰራት ይገባል ስትል ታሳስባለች። ወደቀውስ ሊያመሩ የሚችሉ አብነቶችንም ከአገራት ልምድ እና ዝንባሌ በመጥቀስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራ ስትል ድምጿን ታሰማለች።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ቀላል በማይባል የሰው ልጆች ላይ የሥነ ልቡና ጫና በመፍጠር ለጭንቀት እና ድባቴ ተጋላጭ አድርጓል። ይህም በመሆኑ ሰዎች ከድባቴና ጭንቀት የተነሳ ራሳቸውን የማጥፋት ዝንባሌ ውስጥ እንዲገቡ ይገፋፋቸዋል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ በወረርሽኙ ጭንቀታቸው በመጨመሩ ምክንያት ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር ተበራክቷል የሚሉ ዘገባዎች እየተሰሙ ይገኛሉ።
ወረርሽኙን ለመከላከል አንዳንድ አገሮች በወሰዷቸው የቤት ውስጥ መቆየት (ከቤት ያለመውጣት) እርምጃዎች ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸው እየታየ ነው፡፡ ይህም ወረርሽኙ በማኅበራዊ ሕይወት ላይ የሚያሳድረውን ከፍተኛ ጫና የሚያመላክት ነው፡፡
በዚህ ረገድ የሕንድ መንግሥት ዜጎቹ ከቤት እንዳይወጡ የወሰደው ድንገታዊ እርምጃ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ድሃ ዜጎቹን ለረሃብ እና ከፍተኛ እንግልት መዳረጉን ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙሃን ብቻ ሳይሆኑ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ትኩረትም የሳበ ጉዳይ ሆኗል። ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኋኑ ያናገሯቸው እኚህ ሕንዳውያን ከኮሮና ቫይረስ ይልቅ ረሀብ ቀድሞ ሊገድላቸው እንደሚችል መግለጻቸው መንግሥት የማህበረሰቡን ጤና አስቀድማለሁ ሲል በሌላ መንገድ የማህበረሰቡን ሕይወት አደጋ ላይ እንደጣለ የሚጠቁም ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ‘ሂውማን ራይትስ ዎች’ ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ የሕንድ መንግሥት በዜጎቹ ላይ ያስተላለፈው በቤት ውስጥ የመቀመጥ እርምጃ ድሆችን የበለጠ ችግር ላይ ጥሏቸዋል ሲል ይወቅሳል። ከዐስር ቀን በፊት ለሦስት ሳምንታት ተግባራዊ እንዲደረግ ታስቦ የተወሰደው እርምጃ ድሃ እና ተጋላጭ ሕንዳውያንን ለከፋ የምግብ አቅርቦት እጥረት፣ የመጠለያ እና የጤና አገልግሎት እጦት እንደዳረጋቸው የድርጅቱ መግለጫ ያትታል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በድንገት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሆኑት የባቡር እና የአውቶብስ አገልግሎት መቋረጡ ዝቅተኛ ኑሮ ገፊ ሕንዳውያን እና ስደተኛ ሠራተኞች ላይ ብርቱ ክንዱን ማሳረፉን ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል። የረሃቡ ሳያንስ በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኛ ሠራተኞች ብዙ ኪሎሜትሮችን በእግር እንዲሔዱ አስገድዷል። ወረርሽኙ እና ወረርሽኙን ተከትሎ የተወሰደው መንግሥታዊ እርምጃ የጎዳና ነዋሪዎችንም አልማረም። የእንቅስቃሴ መገደብ የመሰረታዊ አቅርቦቶች እጥረት ይከሰታል የሚል ፍርሃት በሕዝቡ ዘንድ ያሳደረ ከመሆኑም ባሻገር በአጠቃላይ የኑሮ ውድነትን አስከትሏል።
በርግጥ የሕንድ መንግሥት በተለይ ድሃና ተጋላጭ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመታደግ 22.5 ቢሊዮን ዶላር መድቦ ነፃ የምግብ እደላ እንዲደረግላቸው ከማድረግም ባሻገር የገንዘብ እገዛም በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል። በተጨማሪም ለጤና ባለሙያዎች የጤና ዋስትና በመግባት ችግሩ ወደ ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይለወጥ በመታተር ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከሕንድ ጋር የሚያመሳስሏት ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች በመኖራቸው መንግሥት እየወሰደ ካለው የቅድመ ወረርሽኝ መከላከል እርምጃዎች ጎን ለጎን ወረርሽኙ ሊኖረው የሚችለውን ማኅበራዊ ተጽዕኖዎች መገደብ ላይ ሊዘጋጅ ይገባል፡፡ አዲስ ማለዳ ወረርሽኙ በጤና ላይ ከሚያስከትለው ችግር ባልተናነሰ ማኅበራዊ ቀውስ የመፍጠር አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥትም ሆነ ዜጎች ይህን ተገንዝበው በልዩ ትኩረት መሥራት አለባቸው ስትል ትመክራለች።
በርግጥ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የክልል መንግሥታት በተለይ የአዲስ አበባ አስተዳደር ወረርሽኙን ለመከላከል እንዲሁም ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉትን የምግብ አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት እና የጤና መጠበቂያዎችን ለማሟለት በጀት መድበው ከመንቀሳቀሳቸውም ባሻገር በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ከተለያዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ። እስካሁንም የፌዴራል መንግሥት በዓይነት ከሰበሰባቸው መሠራታዊ የምግብ እና የጤና መጠበቂያዎች ባሻገር በጥሬ ገንዘብ ከ190 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም የአዲስ አበባ አስተዳደር ደግሞ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻላቸው ትልቅ ተግባር ነው፡፡ ችግሩ ሊያስከትል ከሚችለው ጉዳት እና ሥፋት አንጻር እርዳታ ማሰባሰቡን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም እሙን ነው፡፡
እርዳታን በጥሬ ገንዘብም ሆነ በዓይነት ከማሰባሰቡ ጎን ለጎን ድሃ እና ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንዴት እና መቼ እርዳታው ይድርስ የሚለው በትኩረት ሊሠራበት ይገባል። ወረርሽኙ ማኅበራዊ ቀውስ ከማስከተሉ በፊት እርዳታው በተጠናና ውጤታማ በሆነ መልኩ ድሃ እና ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ ተደራሽ ማድረግ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንኦት ትሰጣለች።
ችግሩ ጠቅለል ተደርጎ ሲቀመጥ የቫይረሱን ስርጭት እንቅስቃሴን በመገደብ መከላከል የሚቻል ሲሆን ይህ ደግሞ የዕለት ጉርሳቸውን ተሯሩጠው የሚያሳኩ ድሆችን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ በእጅጉ የሚፈታትን ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥትም ሆነ ማህበረሰቡ እነዚህ ወገኖቻችን እንቅስቃሴያቸውን ገድበው ሊቀመጡበት የሚችሉበት ቦታ ማዘጋጀት፣ በአንድ ቦታ በመቀመጣቸው የሚበሉት እንዳያጡ የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡
እነዚህ ነገሮች በተሟሉበት ሁኔታ ከቤት ያለመውጣት እርምጃ ቢወሰድ አገራችን ቫይረሱን ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት የተሳካ ይሆናል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ የሚወሰድ ከቤት ያለመውጣት እርምጃ ግን ወደ ማህበራዊ ቀውስ የሚከት እንደሆነ ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012


