በኢትዮጵያ የኦክስጅን ቬንትሌተር መመረት ሊጀምር ነው

0
681

በዓለም ላይ ከኮሮና ወረርሽኝ ተጠቂዎች መብዛት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ እጥረት የታየበት የኦክስጅን ቬንትሌተር በኢትዮጵያ ለማምረት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ። ይህም ኒው ኤራ ሪሰርች ዴቨሎፕመንት (ነርድ) በተባለ አገር በቀል ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ መመረት ሊጀምር መሆኑ ታውቋል።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ናትናኤል ከበደ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ኦክስጅን ቬንትሌተሩን ለማምረት ከተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር ማለፍ ያለበትን ወይንም ደረጃውን ጠብቆ ማሟለት ያለበትን ሂደት እንዲያልፍ ተደርጎ እየተሠራ ነው። አስፈላጊው የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች በአስቸኳይ ተጠናቀውም ወደ ምርት እንደሚገባ ለማወቅ ተችሏል።

ኩባንያው ሊያመርት የተዘጋጀው ማሽን ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው የተጠቀሰ ሲሆን÷ እንደ ናትናኤል ገለፃ እስከ አሁን ይህን ሥራ ለማገዝ ከኩባንያው ጋር አብሮ የሠራ የመንግሥት መሥርያ ቤትም ሆነ የግል ኩባንያ እንደሌለ ተጠቅሷል። ይሁን እንጂ አምራች ኩባንያው ሌሎች አካላትን የሚያሳትፍ አሠራር በመቅረጽ እና በማዘጋጀት ለተለያዩ መሥርያ ቤቶች ማስገባት መጀመሩን አስታውቋል።

የአመራረት ሂደቱን በተመለከተ ናትናኤል ሲያስረዱ፣ አንድ የኦክስጂን ቬንቲሌተር ለማምረት በአማካይ ከ4 እስከ 5 ቀን ይወስዳል። ይህም ከግብዓት እጥረቶች ጋር ተዳምሮ እንጂ፣ የግብዓት አቅርቦቱ ቢስተካከል አምርቶ ማጠናቀቂያ ጊዜው ከዚህ ዝቅ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ኩባንያው አሁን ባለው የማምረት አቅሙ ሁሉም ግብአቶች ተሟልተውለት እና በሙሉ አቅም ቢሠራ በሳምንት ከመቶ እስከ መቶ ሃምሳ የሚጠጋ ኦክሲጅን ቬንትሌተሮችን ለማምረት እንደሚችልም ናትናኤል ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቬንትሌተሩን በአገር ውስጥ በሚገኝ ግብአት እንደሚመረት ተጠቅሷል። ይህ የሆነበትም ምክንያት በአሁኑ ሰዓት ምርቶችን ከአገር ውስጥ ለማስወጣት እና ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ሁኔታዎች ምቹ እንዳልሆኑ በመገንዘብም እንደሆነም ናትናኤል ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ኩባንያው አሁን ለማምረት በእቅድ ላይ ያለውን የኦክሲጅን ቬንትሌተር፣ በኢትዮጵያ ጥራት እና ቁጥጥር ባለሥልጣን ተመዝኖ ውጤት ለማግኘት በሂደት ላይ መሆኑም ተነስቷል።

እንደ ናትናዔል ገለፃ ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ ተገብቷል። ነገር ግን ወደ ሙከራ ሲገባ እና ወደ ማምረት ሲዘለቅ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት እንደሚያስፈልጉ እና የማምረት አቅሙን ከፍ በማድረግ አገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ እንደ ናትናኤል ገለጻ፣ ምርቱን አምርቶ ወደ ገበያ ለማስገባት በሚጀምርበት ወቅት የአንድ ኦክሲጅን ቬንትሌተር ዋጋ ምን ያህል ሊሆን ይችላል የሚለውን የሚያስፈልጉት ግብአቶች ይወስነዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ነርድ የተሰኘው ኩባንያው ይህን ኦክሲጅን ቬንትሌተር ማምረት ለመጀመር ከማሰቡም በፊት አዳዲስ የቴክኖሎጂ እቃዎችን በማምረት ላይ እንደሚገኝ ናትናኤል ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ለኢንዱስትሪዎች እና ታላላቅ ፋብሪካዎች የሰውን ኃይል የሚተካ ሮቦት ያመረቱ ሲሆን፣ የስፖንጅ መቁረጫ ማሽኖችንም በማምረት በመካከለኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የስፓንጅ ፋብሪካዎች እና የወንበር እና አልጋ ማምረቻዎች እንዳቀረቡም ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ የሚመረተው የኦክስጅን ቬንቲሌተር ባደጉት አገራት በተለይም ደግሞ በአሜሪካ ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ለበሽተኞች ከሚሰጠው የጽኑ ሕሙማን እንክብካቤ መዳረስ ባለመቻሉ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ የሚታወስ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም እንደ ጤና ሚኒስቴር ሪፖርት መሰረት ሊከሰት ይችላል ተብሎ ከታሰቡት ችግሮች መካከል በቬንቲሌተር በኩል የሚኖረው እጥረት እጅግ እንደሚከፋ ለማወቅ ተችሏል። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ አንድ ኦክስጂን ቬንቲሌተር ከ30 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ ዶላር ዋጋ እንዳለው ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here