የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት 340 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተሰበሰበ

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመግታት ከለጋሽ ድርጅቶች እና ግለሰቦች 340 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሬታሪ ንጉሡ ጥላሁን ረቡዕ ሚያዚያ 7/2012 በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በክልሎች እና በአዲስ አበባ የተሰበሰበውን የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ሳይጨምር በማእከል ብቻ 340 ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቧል።
ንጉሡ ጨምረው ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ከተከሰተ አንድ ወር ያለፈው መሆኑን እና እስከ አሁንም ድረስ መንግሥት እና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ኅብረተሰቡ ወረርሽኙን ለመግታት ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። በዚህም ረገድ በማእከል ከተገኘው የ340 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በተጨማሪ በዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መሰብሰቡንም ይፋ አድርገዋል። ትረስት ፈንዱ በቅርቡ ገቢ ያደረገው የገንዘብ መጠን ጅማሬ መሆኑንና ድጋፍ የማሰባሰብ እንቅስቃሴውንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስታወቁን ንጉሡ ገልጸዋል።
ፕሬስ ሴክሬታሪው አያይዘውም ከተለያዩ ለጋሾች የተሰበሰበውን ገንዘብ መንግሥት በአገር ደረጃ የተከሰተው ወረርሽኝ ከመግታት ጋር ተያይዞ ለሚያስፈልጉ የጤና፣ የምግብ እና መሰል ፍላጎቶችን ለማሟላት እንደሚጠቀምበት አስታውቀዋል። መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ወደ አገር ውስጥ ገብተው መክፈል የማይችሉ እና መንግሥት ባዘጋጀው ለይቶ ማቆያ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር 6 ሺሕ እንደሚደርስ እና ለእነሱም አልባሳት እና ምግብ በማቅረብም ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
ከለይቶ ማቆያ ጋር በተያያዘ በሰባት ዪኒቨርስቲዎች ማለትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ ዋቻሞ እና ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲዎች እንደተዘጋጁ እና ግልጋሎት ላይ እንደዋሉ ተጠቁሟል። ለለይቶ ማቆያ የተዘጋጁ ዩኒቨርስቲዎች በውስጣቸው ለሚያስጠልሏቸው ሰዎች አስፈላጊውን ምግብ እና ቁሳቁስ በማቅረቡ ረገድ እጥረት እንዳይፈጠር የተቻላቸውን እያደረጉ እንደሚገኙ እና መንግሥትም ለሚደረገው ያላሰለሰ ርብርብ ለዩኒቨርሰቲዎች ፕሬዘዳንቶች ምስጋናውን አቅርቧል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በአገር መከላከያ ሠራዊት ባለበት በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል 38 ለይቶ ማቆያዎች እንደተዘጋጁ ለማወቅ ተችሏል። በሠራዊቱ ዘንድ ያለውን በሽታውን የመከላከል ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ተደጋጋሚ እና ጠንካራ ፍተሻዎች ተደርገው በቂ ዝግጅት መደረጉ እንደታመነበት ፕሬስ ሴክረታሪው አስታውቀዋል።
እንደ ንጉሡ ገለጻ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ምንም ካለመኖር ወደ ስምንት ያደገው ቫይረሱን የመመርመሪያ ማእከል በቅርቡ በመቀሌ፣ ባህር ዳር፣ ሐሮማያ እና ሐዋሳ የተጀመሩት የመመርመሪያ ማእከላት ሦስት የነበሩት ወደ ስምንት እንዳሳደጉት እና በቀጣይም ተጨማሪ መመርመሪያ ማእከላት እንደሚዘጋጁ ለማወቅ ተችሏል።
ጽሕፈት ቤቱ እንደገለጸው ወረርሽኙን ለመግታት በመንግሥት ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች እና ሕግጋት ጋር ተያይዞ ኅብረተሰቡ አሁንም ያለማክበር አዝማሚያ እየታየበት እንዳለ ተናግረዋል። በተለይ በሃይማኖት ተቋማት፣ ሰው በሚበዛቸው የሕዝብ መጓጓዣዎች እና በገበያ ስፍራዎች አሁንም ጥንቃቄ እየተደረገ እንዳልሆነ አስታውቋል። ከዚህ በመነሳት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባወጣው ሕግ መሰረት የፀጥታ መዋቅሩ አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ በመንግሥት አቅጣጫ እንደተቀመጠለት ፕሬስ ሴክሬታሪው ግልጽ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ አዲስ ማለዳ ወደ ማተሚያ ቤት እስከ ገባችበት ጊዜ ድረስ በተደረጉ ምርመራዎች 92 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው እና በሕክምና ተቋማት ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። በዚሁ በጤና ሚኒስቴር ሪፖርት መሰረት 14 ሰዎች ከበሽታው አገግመው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውም ተጠቁሟል።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here