ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ የቁም እንስሳትን ለገበያ እንደማያቀርብ አስታወቀ

0
1204

የሜድሮክ ኢትዮጵያ አካል የሆነው ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ በዘንድሮ 2012 ፋሲካ በዓል አሁን ካለው ወቅታዊ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አንፃር የቁም እንስሳት እና ዶሮ ለገበያ እንደማያቀርብ አስታወቀ። ኤልፎራ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረው የቁም እንስሳት ግብይት ከቀጠለ የንክኪ ብዛቱ በርካታ ስለሚሆን ነው የተባለ ሲሆን፣ ለዚህም በፋብሪካ ውስጥ እርድ ተከናውኖ (በሱፐር ማርኬት) እንደተለመደው እንደሚከፋፈል ተገልጿል።
ከዛም በተጨማሪ እርዱ በፋብሪካ ውስጥ እንዲሆን ከመደረጉም በላይ ለኅብረተሰቡ እንደፍላጎቱ መውሰድ እንዲችል (ለወጥ እና ለአሮስቶ) በሚሆን መልኩ ተቆራርጦ እንደሚዘጋጅም ተጠቅሷል።
በቁም እንስሳት ግብይት ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የሰዎች ንክኪ እና ያንንም ተከትሎ የኮቪድ 19 በሽታን ለማሰራጨት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚያደርገው አዲስ ይህ የአሰራር ለውጥ፣ በድርጅቱ የገቢ መጠን ላይ ምንም አይነት ለውጥ እንደማያመጣ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የድርጅቱ የሥራ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
‹‹ይህም በመሆኑ የጎላ ተፅዕኖ አልደረሰብንም›› የሚሉት የድርጅቱ የሥራ ኃላፊ አሁንም ምርቱ በበቂ ሁኔታ እንዳለ እና የአቅርቦትም ሆነ የሽያጭ ችግር ያጋጥማል ብለው እንደማያስቡ አስታውቀዋል። ከዚህ ቀደም በፋብሪካ እርዳቸው ተከናውኖ ተበልተው የሚቀርቡ እና የቁም እንስሳት ሽያጭ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ሙሉ በሙሉ እርዳቸው በፋብሪካ ተከናውኖ ኅብረተሰቡ በሚፈልገው አይነት ተዘጋጅቶ መሰራጨት መጀመሩን ተናግረዋል።
ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ምንም አይነት የዋጋ ለውጥ እንደሌለው ኤልፎራ ያስታወቀ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ከኤልፎራ ይቀርቡ የነበሩት እንቁላሎች ላይ አምስት ብር የነበሩት በደብረዘይት እና በአዲስ አበባ ላሉት ተረካቢዎች በሦስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም እያከፋፈለ መሆኑን እና አራት ብር ከአስር ሳንቲም ደግሞ ለተጠቃሚ እንዲሸጥ መደረጉንም አንስተዋል።
የዶሮ ዋጋም በኪሎ መጠናቸው ከዚህ ቀደም በነበረበት ዋጋ እንደሚሸጥ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቀው ኤልፎራ፣ አንድ ኪሎ የታረደ ዶሮ ዋጋ በ150 ብር ለተጠቃሚ እንደሚቀርብም አስታውቋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ የተለያዩ የገበያ ቦታዎች ላይ ዳሰሳ ባደረገችበት ወቅት፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 02 ‹ቻይና ገበያ› በመባል የሚታወቀው የገበያ ማእከል የሚገኙ ነጋዴዎች እንደነገሯት፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ ከዚህ ቀደም ይገበያዩበት የነበረውን ሂደት በማስቀረት እና ወደተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በመዘዋወር ቅመማ ቅመም፣ እንቁላል እና ዶሮ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ አስበዋል።
ነጋዴዎቹ ጨምረው እንደገለፁት፣ የዘንድሮ የፋሲካ በዓልን እንደተለመደው እንቅስቃሴ ለማድረግ አለመቻሉን በማስታወስ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚል በክልሎች ላይ ተወስዶ የነበረውን እርምጃ በመጥቀስ በበቂ ሁኔታ የቁም እንስሳትን ማስገባት እንዳልቻሉ አስታውቀዋል።
እንደ ነጋዴዎቹ ገለፃ ከሆነ ዶሮዎችን፣ ቂቤ እና አይብ የመሳሰሉት ግብአቶች የሚመጡት ከመቂ እና ወላይታ መሆኑን ገልፀው፣ ነገር ግን አሁን ወደ ኢትዮጵያ የገባውን ኮቪድ 19 ወረርሽኝ አቅርቦቶቹ በጊዜ እንዳይገቡ አድርጓል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here