ጋንዲ ሆስፒታል ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ወላዶች መጨናነቁ ተገለፀ

0
940

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆስፒታሎች ለኮቪድ 19 ለይቶ ማቆያ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለመውለድ የተቃረቡ ነብሰ ጡሮችን ወደ ሆስፒታሉ መላክ በመጀመራቸው ማስተናገድ ከሚችለው በላይ በወላዶች መጨናነቁ ተገልጿል።

ዘውዲቱ ሆስፒታል፣ ጥቁር አንበሳ እና ጳውሎስ ሆስፒታል ለኮቪድ 19 ማእከል እየሆኑ ስለሆነ ዘውዲቱ ጥቁር እንበሳ ሆስፒታል ክትትል የነበራቸው እና ወደ መውለድ የተቃረቡት ወደ ጋንዲ እንዲዘዋወሩ መደረጉን፣ ይህም ትልቅ መጨናነቅ እና ታካሚዎች ተገቢውን ግልጋሎት እንዳያገኙ እንዳደረገ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በጋንዲ ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል፡፡

ከኹለቱ የመንግስት ሆስፒታሎች በተጨማሪ 11 የሚሆኑ የጤና ጣቢያ ክትትል የነበራቸው ወላዶች ወደ በጋንዲ ሆስፒታል መገልገል በመጀመራቸው በተገቢው መንገድ ማስተናገድ እንዳልተቻለ ምንጫችን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በጋንዲ ሆስፒታል ያለው መታከሚያ አልጋ ከ 100 እስከ 130 አይበልጥም የሚሉት ምንጫችን ይህ መሆኑ ደግሞ ቀጠሮ ያላቸው ወላዶች አልጋ አጥተው እንዲጉላሉ ከማድረጉም ባሻገር የቀጠሮ ቀናቸውን ጠብቆ ለመንከባከብ እና አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት ከባድ እንዳደረገባቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለፃ ከሆነ ‹‹እንድን ወላድ አንድ ጊዜ መርምሮ ሁለተኛ ዙር ለማየት›› እንዳይቻል ያደረገው ሁኔታ እንዳለና ከሌላ ቦታ ወላዶች በሚመጡበት ጊዜ የተገልጋይ መጨናነቅ ስለሚኖር ከ 3-4 ቀን አልጋ ሳያገኙ እየቆዩ እንደሆነና ይሄ ከዚህ ቀደም ወላዶች ሲበዙ የሚያጋጥም ነገር ቢሆንም አሁን ላይ ያለው ሀኔታ ግን ከባድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እነጂ ከዚህ ቀደም ይሰሩበት ከነበረው አቅም በላይ እየሰሩ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከሆስፒታሉ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዠ ዶክተር አብረሃም ታሪኩ በጤና ሚኒስቴር የህፃናት እና ጨቅላ ህፃናት ጤና አስተባባሪ የሆኑት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት እንደ መንግስት በኹለት አቅጣጫ ነው እየሄድን ያለነው ብለዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ አንደኛው አቅጣጫ ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስን ኃላፊነት ወስዶ ሚንቀሳቀስ አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእናቶች እና ህፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት ሙሉ ስራውን እንደነበር እንዲቀጥል ነው የተደረገው ብለዋል፡፡

የእናቶች እና ሀፃናት ጤና አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ መመርያ ተላልፏል የሚሉት ዶክተር አብረሃም ነገር ግን አሁን የሚታየው ነገር የአገልግሎቱ መቋረጥ ሳይሆን አጠቃላይ እንደ አገር በተወሰነው ውሳኔ ትራንስፖርት እንቅስቃሴው እንደሁልጊዜው ባለመሆኑ ‹‹ እናቶች ወደ ወሊድ ተቋም (የህክምና) ስፍራ በሰአቱ እየደረሱ አደለም›› ብለዋል፡፡ ‹‹በዛም ምክንያት በግዜው ያለመድረስ እና እስከ ሞት የመድረስ ሁኔታ እነዳለ ›› ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ጥቆማ እደረሰን ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ነገር ግን ለውን ሁኔታ ለማየት እና ምን መደረግ ኖርበታል የሚለውን ለመወሰን ያለውን ሁኔታ መገምገም አስፈላጊም ነው ብለዋል፡፡ ከዛም በተጨማሪ እንደ ዶክተር አብረሃም ገለፃ ‹‹ ህብረተሰቡም ጋር የቫይረሱን መከሰት ከሰማ በኋላ በጤና ተቋማት ሄዶ መገልገል መፍራት ጀምሯል›› ብሏል ይህም ግንዛቤ ላይ መሰራት ኖርበታል ብለዋል፡፡ በህክምና ቦታዎች ከዚህ ቀደም ከነበረው ጥንቃቄ በበለጠ በትኩረት ‹‹የማዋለዱንም ሌላ አገልግሎት የማግኘቱም›› ሁኔታ የተጠበቀ መሆኑን ህብረተሰቡ ማወቅ ይኞርበታል በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

እነደ አስተባባሪው ገለጻ ‹‹ኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ከሚገላቸው ሰዎች የበለጠ ብዙ እናቶች እና ህፃናትን እንዳናጣ ነው የሰጋነው ብለዋል›› ይህ እንዳይሆን ህብረተሰቡ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል በማለት ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here