በኹለት ወራት ውስጥ እስከ 80 በመቶ የዘይት ፍጆታ በአገር ውስጥ ምርት ይሸፈናል

0
678

በአሁኑ ሰዓት ዘጠኝ በመቶ ብቻ ነው በአገር ውስጥ ምርት የሚሸፈነው

በመጪዎቹ ኹለት ወራት በአገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት ፍጆታ እስከ 80 በመቶ የሚደርሰውን በአገር ውስጥ ምርት እንደሚሸፈን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው በቅርቡ በሚጀምሩ ሦስት ዘይት ፋብሪካዎች ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት ዘጠኝ በመቶ ብቻ በአገር ውስጥ ምርት የሚሸፈነውን የምግብ ዘይት ፍጆታ እስከ 70 ከፍ ሲልም 80 በመቶ ድረስ መሸፈን እንደሚቻል ንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር መላኩ አለበል አስታውቀዋል።

እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ 1ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነውን የአገር አቀፍ ምግብ ዘይት ፍጆታ በአገር ውስጥ ምርት ይሸፈን እንደነበር ያወሱት መላኩ በአሁኑ ሰኣት ግን 9 በመቶ መድረሱን አብራርተዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በቀጣይ ባሉ ኹለት ወራት ውስጥ ወደ ስራ በሚገቡ ሦስት ዘይት ፋብሪካዎች ምክንያት በአገር ውስጥ የሚሸፈነው የዘይት ፍጆታ ወደ 80 በመቶ ከፍ እንደሚል ተገልጿል። መላኩ አያይዘው በቀጣዩ አመት 2013 ኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ፍላጎቷን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርት እንደምትሸፍን ዕቅድ ከወዲሁ ይፋ ተደርጓል።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከአራት መቶ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ ዘይት ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ይምታስገባ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በ2012 መጋቢት ወር ላይ 40 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚሆን ምግብ ዘይት ወደ አገር ያስገባች መሆኑን ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል። በአገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዘይት ፍጆታን በተመለከተ ኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ ከተማ እና አማራ ክልል ከአንድ እስከ ሦስት ከፍተኛ ፍጆታ ያለባቸው ሆነው መመዝገባቸውን በ2011 የተሰራ ጥናት ያመላክታል።

በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካው ግብርና ቢሮ የውጭ አገራት ግብርና አገልግሎት ጥር 2012 ባወጣው ሪፖርት እንዳስታወቀው ለምግብ ዘይት ማምረቻ ግብዓትነት የሚውሉ የቅባት እህሎች በኢትዮጵያ ያለውን ምርታማነት ይፋ አድርጓል። በዚህም ረገድ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ40 ሽ ሜትሪክ ቶን ከፍ ያለው ሰሊጥ ሲሆን በዚህም በ2011 በጀት ዓመት 340ሽሕ ሜትሪክ ቶን ምርት መመዝገቡን ያስታወቀ ሲሆን ኑግና አኩሪ አተርም በ305 ሽሕ እና በ200 ሽህ ሜትሪክ ቶን በኹለተኛ እና በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በሪፖርቱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው በቀዳሚው ዓመት ላይ ነበረው 790 000 ሜትሪክ ቶን የቅባት እህሎች ድምር ምርት መጠን በ2011 በጀት ዓት ላይ 845 ሽሕ ሜትሪክ ቶን መድረሱን አመላክቷል።

ይሁን እንጂ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ መንግሥት በእርግጥም የአገርን ምግብ ዘይት ፍጆታን በአገር ውስጥ ለመተካት ያደረገው ጥረት ሚደነቅ እና ሚበረታታ ቢሆንም ተፈጻሚነቱ ግን ትልቅ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው ሲሉ አስታውቀዋል። አስተያየት ሰጪው አያይዘው እንደገለፁት ምቱ ስለጨመረ ብቻ የአገርን ዘይት ፍጆታ ማሟላት ይቻላል ማለት አስቸጋሪ እንደሚሆን ይጠቁማሉ። ምክንያታቸውንም ሲያስቀምጡ የቅባት እህሎች ለአገር ውስጥ ገበያ ከሚቀርቡት እና በመንግሥት ተመዝግበው ወደ ውጭ ከሚላኩት የበለጠ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት አገራት ወይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚጓዙት ይበልጣሉ ይላሉ። በመሆኑም አሁን ዘይት ወደ ማምረቱ ይገባሉ የተባሉ ድርጅቶች ለምርታቸው የሚሆን ግብዓት ራሳቸው ማምረት ይኖርባቸዋል ካልሆነ ግን ከፍተኛ የግብዓት ዕጥረት ይገጥማቸዋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here