የትግራይ ክልል መንግሥት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በክልል ደረጃ ምርጫ የማካሄድ ሕጋዊ መሰረት እንደሌለው ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ ክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ማስታወቁን በሚመለከት መረጃ እንደሌላቸው ነገር ግን በሕጉ መሰረት የፌዴራልም ሆነ የክልል ምርጫዎች የሚደረጉት ገለልተኛ በሆነ የምርጫ ቦርድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልሌ ውስጥ ምርጫ አካሂዳለሁ ካለ፣ በክልል ደረጃ ምርጫ የማካሄድ ሕጋዊ መሠረት የለውም›› ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ ሕወሓት ምርጫ 2012 ሊካሄድ በታቀደለት ጊዜ የማይካሄድ ከሆነ ፓርቲው የራሱን አማራጭ እንደሚወስድ አስታውቋል። የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል ጌታቸው ረዳ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መንገድ ከተዘጋ የራሳችንን አማራጭ እንወስዳለን›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ጌታቸው አክለውም በፌዴራል መንግሥት በኩል ምርጫ ያለ አግባብ የማራዘም ፍላጎት አለ በማለት ወቅሰዋል። አያይዘውም ‹‹ኮሮናን አስመልክቶ ከአገር በፊት ቀድመን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጅን ሰዎች ምርጫው በግድ ነሐሴ ላይ ይሁን አንልም›› ብለው፣ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ መሰረት ምርጫ መካሔድ እንደሚኖርበት አስቀምጠዋል።
የፌዴራል መንግሥት በምርጫ ጉዳይ ከሕጉ ውጭ የማራዘም ጥረት የሚቀጥል ከሆነ ፓርቲያቸው የራሱን አማራጭ የመውሰዱ ነገር አቋማቸው መሆኑን ጌታቸው ተናግረዋል። ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ያራዘመው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ነው ብለው እንደማያምኑም ጌታቸው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ 2012 ለማካሄድ እንደማይቻል እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫውን ማካሄድ የማይችል መሆኑን ገልጾ፣ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሠረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ መወሰኑ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 24 ቀን 2012 ባወጣው መግለጫ ምርጫውን ቀድሞ ባቀደው ቀን ማለትም ነሐሴ 23 ቀን 2012 ማከናወን እንደማይችል ማሳወቁን ተከትሎ፣ ቦርዱ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ጥናት አካሂጃለሁ ብሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተጠሪነቱ ለተወካዮች ምክር ቤት ስለሆነ ውሳኔውንም ለተወካዮች ምክር ቤት አሳውቋል።
ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት ምርጫውን ማከናወን ካለመቻሉ በስተቀር የተራዘመ ቀን ቆርጦ አለመኖሩን ጠቅሷል። ቦርዱ ማድረግ የሚችለው ምርጫ ማከናወን አለመቻሉን ገልጾ ሪፓርት ለሚያደርግለት ለተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቅ ብቻ መሆኑንም መግለጹ ይታወሳል።
የቦርዱን የምርጫ አፈጻጸም ዝግጁነት የሚጨምሩ፣ ሁኔታው ተቀይሮ ተቋሙ ወደ መደበኛ ተግባሩ ሲመለስ በተገቢው ሁኔታ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስችል ሁኔታን የሚፈጥሩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚቆይም አስታውቋል። ቦርዱ የወረርሽኙ ሥጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን እቅድና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቃሴውን እንደሚያስጀምር አሳውቆ ነበር።
በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት መሠረት አሁን ያለው የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሥራ ዘመን ከመስከረም 30 በኋላ እንደሚጠናቀቅ በሕግ የተቀመጠ ጉዳይ ነው። በዚህ ሕግ አግባብ መሰረት የፌዴራል ፓርላማና የክልል ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ይጠናቀቃል። በፓርላማና ክልል ምክር ቤቶች የተቋቋሙት ሥራ አስፈፃሚዎች የሥራ ዘመንም አብሮ ያበቃል። ይህን ተከትሎ በባለድርሻ አካላት በምርጫ ጉዳይ አዲስ አማራጭ አቅጣጫዎች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሚያዚያ 21/2012 ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት አራት አማራጮችን ማቅረባቸው ይታወሳል። እነዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻል እና የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ ናቸው።
ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012



