አዳዲስ ችግሮች በአዳዲስ እርምጃዎች መፈታት አለባቸው!

0
795

መቼም ይኼ ኮሮና የማይገባበት ጉዳይ የለም፤ ይኸው በዚህ ሳምንት ደግሞ የምርጫውን መራዘም አስከትሎ የተፈጠረውን ሕገ መንግሥታዊ ችግር እንዴት እንፍታው በሚል ፖለቲከኞቻችንን እያጨቃጨቀ ይገኛል። የእነሱ ጭቅጭቅ የተለመደ ቢሆንም አሁን ያነሱት ጉዳይ ግን ከዚህ በፊት ካጋጠማቸው ለየት ያለ ነው።

በነሐሴ ሊካሔድ የነበረው አገራዊ ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መተላለፉ በመስከረም 2013 የሥልጣን ዘመኑ የሚያልቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዲስ ተመራጮች ሳይተካ እንዲበተን በር ይከፍታል። ሕገ መንግሥቱ ደግሞ እንዲህ ያለ አጣብቂኝ በሚያጋጥምበት ጊዜ መውጫ ይሆናል ብሎ ያስቀመጠው አማራጭ የለም። በዚህም የተነሳ ከመስከረም መጨረሻ ጀምሮ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ቅቡልነቱን እንዲያጣ እና ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ እንዲፈጠር የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል።

ይህ ደግሞ በመጠላለፍ እና ባለመተማመን ለሚታወቀው የኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሔድ አዲስ መድረክ ፈጥሯል። ከሰሞኑ እንዳየነውም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በየፊናቸው የተለያዩ ጽንፎች ላይ ቆመው እርስ በእርስ እየተጓተቱ ነው። የዛሬ ኹለት ዓመት የሽግግር መንግሥት መመሥረት አለበት ያሉት ሌሎችን ጨምረው አሁንም ያንን አጀንዳ አንስተዋል፤ የፖለቲካ ልሒቃን ድርድር ያስፈልጋል የሚሉትም ይህንኑ ሀሳብ አሁንም መድኃኒት ነው ይላሉ፤ የማሻገር ኃላፊነቱን የተቀበለው የለውጥ ኃይልም ሳትሻገሩ ፍንክች የለም እያለ ነው።

በእነዚህ አቋሞች ውስጥ የሚታዩ ለውጦች እምብዛም ናቸው። እንዲያውም ደፈር ብሎ ማን ምን ሊል እንደሚችል በሚተነብይ መልኩ አቋማቸውን ቀደሞ ብሎ መናገር ይቻላል። ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ፖለቲከኞች የችግሮች ዓይነት፣ ስፋት እና አሳሳቢነት ሳይወስናቸው ለሁሉም ተግዳሮቶች ተመሳሳይ መድኃኒታቸውን ይዘው መከሰታቸው የሚያስተዛዝብ ነው።

በመሆኑም ችግሩ ተከስቶ አገሪቱ ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው መንግሥት የማያስተዳድራት ሁኔታ ውስጥ ከመግባቷ በፊት ሁኔታዎች የሚስተካከሉበት መንገድ ሊገኝ ይገባል። ይህንን ከባድ ውሳኔ ለመወሰን ደግሞ ብልፅግና ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እና ሲቪክ ማህበረሰቡን ማወያየቱ ተገቢ እርምጃ ነው። የአገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ውሳኔ እስኪገኝ ድረስም እንዲህ ዓይነቱን ውይይት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ ከዚህ በፊት አጋጥሞን የማያውቅ ችግር ሲከሰት ደግሞ የሁኔታውን አሳሳቢነት ተረድቶ በጋራ ለመፍታት እና አገርን ከሚከተለው ችግር ለማዳን መረባረብ እንጂ ሌሎች ከጉዳዩ ውጪ ያሉ ልዩነቶችን እያነሱ ከፍ ዝቅ መደራረግ ከአቅመ አዳም በብርሃን ዓመታት ከራቁ ሰዎች የማይጠበቅ ነው። በተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ሆነ በገዢው ፓርቲ መሪዎች የተሰነዘሩት ዝልፊያዎች ይመሩናል ብለው የበሰለ ውይይት እና ውሳኔ የሚጠብቁ ዜጎችን ያሳዘኑ ናቸው።

ይህ ዓለማቀፋዊ ወረርሽኝ በተለያየ መንገድ ደጋግሞ እንዳሳየን ከዚህ በፊት ይዘናቸው የመጣናቸው አሠራሮች ብዙም የሚያዛልቁ አይደሉም። ብዙዎቹ የፖለቲካ ርዕዩት ዓለማት፣ የጤና ስርዓቶች፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ፖሊሲዎችም ቢሆኑ ከፍተኛ ሕፀፅ ያለባቸው እንደሆኑ በወረርሽኙ ተጋልጠዋል። አይነኬ የሚመስሉን የዓለም ኃያላን አገራት በማይታመን ሁኔታ ሲያፍሩ በሳል ፖለቲከኞች ከዚህ በኋላ አስተሳሰቦች እንዴት መቀየር እንዳለባቸው ቀድመው ሊያስቡ ይገባል።

በተለመደው አካሔድ መቀጠል ሊበቃ ይገባዋል። ለዘመናት ሳይቀየር የሔደውን ጉልበተኛ የሚያሸንፍበት የፖለቲካ አሠራር አቁሞ ተማክረው የተሻለው ውሳኔ ላይ የሚደርሱበትን አዲስ መንገድ መቀየስ ያስፈልጋል። ፈረንጆቹ እንደሚሉት ያልተለመዱ ችግሮች ያልተለመዱ እርምጃዎችን ይጠይቃሉ።

የተጋረጠው ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ እውን ቢሆን ሊፈጠር የሚችለው ፖለቲካዊ ችግር በኮሮና ወረርሽኝ ተዳክሞ ከቆየው ኢኮኖሚ እና በአንበጣ መንጋ እና ጎርፍ ከተመታው ግብርና ጋር ሲዳመር አገራችንን እንደሚያሽመደምዳት አጠራጣሪ አይደለም። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ እየተራበ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሕዝብን የሚመራ ሕጋዊ ያልሆነ መንግሥት ያለባት አገር ወደ መሆን ልትሸጋገር ትችላለች። ይህ ደግሞ የዜጎችን ህልውና በከፍተኛ አደጋ ውስጥ የሚጥል ሁኔታ በመሆኑ ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ፖለቲከኞች በአንድነት ሊከላከሉት ይገባል።

የእራስን የፖለቲካ ጥቅም ሊፈጠር ከሚችለው ዘግናኝ ሁኔታ በላይ አድርጎ ማየት ወይም የሚመጣውን ችግር ለማየት ያለመቻል ከታሪክ ተጠያቂነት አያድንም። በመሆኑም ሁሉም ፖለቲከኞች በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት የተጋረጠውን ችግር ለመፍታት በተናጠል እና በጋራ ሊሠሩ ይገባል።

ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ ናቸው ያላቸውን አራት አማራጮች መንግሥት ያቀረበ ሲሆን እነዚህም ሕገ መንግሥታዊነታቸው የተረጋገጠ አካሔዶች ናቸው ተብሏል። ከእነዚህ አማራጮች ውጪ ማምጣት ደግሞ የተከለከለ ነው ምክንያቱም አማራጮቹን ያወጡት አገሪቷ ውስጥ ብቃት አላቸው ተብለው የሚታመኑ የሕግ ባለሙያዎች ናቸው መባሉ ከአራቱ የቱን መንገድ እንምረጥ የሚለው ላይ ብቻ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች እንዲወያዩ የሚያደርግ ነው።

በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግሩን ለመፍታት ይሆናሉ የሚሏቸውን የፖለቲካም ሆኑ የሕግ አማራጮች እንዲያቀርቡ የሚጋብዝ ሳይሆን ከተቀመጠው አራት አማራጭ የቶቹን ትመርጣላችሁ የሚል ነው። ያለውን የፖለቲካ ያለመተማመን እና ሴራ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሌሎቹ የፖለቲካ ኃይሎች ባያምኑ የሚገርም አይደለም። በመሆኑም ቅንነቱ ካለ ሦስቱ አማራጭ አቅራቢ ቡድኖች ሲዋቀሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰዎችን እንዲጠቁሙ በማድረግም ሆነ ሒደቱን እንዲያውቁት በማድረግ ማሳተፍ እና ውጤቱም ላይ የጋራነት ስሜት ተሰምቷቸው በቀላሉ እንዲቀበሉት ማድረግ ይቻል ነበር። ይህ የመንግሥት ግዴታ ባይሆንም ለውጤቱ መሳካት ያለውን ቀናኢነት የሚያሳይ ይሆን ነበር።

የሽግግር መንግሥትም ሆነ ሌላ ዓይነት የሥልጣን መጋሪያ መንገድ በአሁኑ ጊዜ ማንሳት የብጥብጥ መንግሥት ለመፍጠር መጣር ነው ብሎ ነገሮችን መዝጋት ግን ከዚህ በፊት የሰማናቸውን ዓይነት መሪዎቻችንን ምላሾች የሚያስታውስ ነው። በአብሮነት ስሜት እና ነገሮችን ለማስተካከል በሚደረገው ሒደት አሁንም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልፎ አልፎም ቢሆን የሚያነሷቸው ቀናነት፣ ትብብር እና መደመር አላለፈባቸውም። እንዲያውም ወረርሽኙም ሆነ የሕገ መንግሥቱ የሕግ ክፍተት በአንድነት ርብርብ የሚጠይቁ ንግግሮችን በተግባር ማዋያ ጥሩ አጋጣሚዎች ናቸው።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት እድሉን ባገኙ ቁጥር ከአጀንዳ እየወጡም ቢሆን ገዢውን ፓርቲ የሚኮንኑ መሆኑ ተገቢ አይደለም። እንዲያውም የችግሮቹን መደራረብ ከግምት ውስጥ በማስገባት ትኩረትን በችግሮች አፈታት ላይ አድርጎ በጋራ ለመሥራት በሙሉ ጉልበት መንቀሳቀስ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታም ጠ/ሚኒስትሩ የእርሳቸውን እድሜ ያክል በፖለቲካ ትግል ውስጥ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የቆዩትን ለወትሮው የሚያከብሯቸው ፖለቲከኞች ማሸማቀቃቸው እርሳቸውም የተሻለ ባህሪይ እንዳላሳዩ የሚገልፅ ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ እርስ በእርስ የሚያናቁሩን ጉዳዮች አሉባት። የዘር ፖለቲካ፣ የባንዲራ ጉዳይ፣ የፌዴራሊዝም ዓይነት፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ የመገንጠል መብት፣ የእኩልነት ጥያቄ የመሳሰሉት ከባባድ ጉዳዮች ገና በእነዚሁ ሰከን ብለው ለመነጋገር በሚቸገሩ መሪዎቻችን እንዲፈቱ የሚጠበቁ ጉዳዮች ናቸው።

በዚህ ረገድ አሁንም ኮሮና ይህንን የሕገ መንግሥት ክፍተት ችግር በማጋለጥ ፖለቲከኞቹ አስተሳሰባቸውን፣ አሠራራቸውን እና የመግባቢያ መንገዳቸውን እንዲያስተካክሉ እድሉን እንደከፈተ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ወረርሽኙን ለመከላከል ሕብረተሰብ ከማህበራዊ እሴቶቹ ጋር የማይሔዱ እርምጃዎችን እንዲወስድ ሲወተውቱ የምንሰማቸው ፖለቲከኞች እራሳቸውም የለመዱትን የሴራ መንገድ እንዲተዉ ጥሩ አጋጣሚ በወረርሽኙ ቀርቦላቸዋል። ይህንን የተጋረጠውን የሕግ ክፍተት ተባብረው እንዲፈቱት የቀረበላቸውን ፈተና ለማለፍ የሚያድርጉት ጥረት ከላይ ለዘረዘርናቸው በርካታ ችግሮች አፈታት ጥሩ ልምምድ እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here