በኢትዮጵያ የታየውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ ሆቴሎች በስራቸው ያሏቸውን ሠራተኞች መቀነስ መጀመራቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
በአዲስ አበባ በሚገኙ ባለኮኮብ ሆቴሎች ውስጥ በተለያዩ የሥራ ድርሻዎች ላይ ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች ከሰሞኑ በሥራ ቦታቸው ላይ ከሥራ የመቀነስ እና በግዴታ ያለ ክፍያ እረፍት እንዲወጡ የሚያስደርጉ ማስታወቂያዎች በመለጠፋቸው ከሥራቸው መቀነሳቸውን ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ጥቆማ ሰጪዎች ጨምረው እንደገለፁት ምንም ዓይነት ቅድመ ዝግጅት ሳያደርጉ ከሥራቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ለሠራተኞቹ ከተላከው ደብዳቤ እንደተረዳችው ስዊዝ ኢን የተሰኘ ሆቴል ለሠራተኞቹ ባስተላለፈው የደብዳቤ መልእክት ከሆቴል ሥራ ዘርፎች ውስጥ የተወሰኑትን በመምረጥ ‹‹ሆቴሉ ችግሩ እስኪያልፍ በሥራ ላይ የሚቆያቸው ሠራተኞች›› በሚል እና ከእነሱም መካከል በሥራው ላይ እንዲቆዩ ለተደረጉት ሠራተኞች ደግሞ ከደሞዛቸው ‹‹ከ10 በመቶ እስከ 40 በመቶ›› ተቀናሽ ሆኖ እንዲከፈላቸው ተወስኗል።
ከዛም በተጨማሪ በስዊዝ ኢን ሆቴል በማኔጅመንት ዘርፍ ይሠሩ የነበሩ የአዲስ ማለዳ ምንጭ ለአዲስ ማለዳ ለሠራተኞቻቸው ማስጠንቀቂያ ጊዜ መስጠት እያለባቸው ነገር ግን ያን ሳያደርጉ አስቸኳይ ጊዜ በታወጀበት ጊዜ የሠራተኛ ቅነሳ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ጉዳዩን በሚመለከት የስዎዝ ኢን የሥራ ኃላፊዎችን ለማናገር አዲስ ማለዳ ያደረገችው ሙከራ አንድ ጊዜ ባለቤቱ ከአገር ውጭ ናቸው በሚል ምክንያት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለማናገር ፈቃደኛ ባለመሆን ሳይሳካ ቀርቷል።
ስዊዝ ኢን እንደ አብነት ተጠቀሰ እንጂ በርካታ በአዲስ አበባ የሚገኙ ባለኮኮብ ሆቴሎች ሠራተኞቻቸውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚጻረር ሁኔታ እየቀነሱ እንደሆነ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ካቀረቡ ሰዎች ማወቅ ተችሏል።
የተፈጠረውን ጉዳይ በሚመለከት ለአዲስ ማለዳ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር ኮንፌደሬሽን የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ሠራተኞችን ለመቀነስ በሚያስቡ መሥርያ ቤቶች ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እያደረግን ነው ብሏል።
ኮንፌዴሬሽኑ ያለውን ቅሬታ እና ከዚህ ቀደም በዚህ መንገድ እየተጓዙ የነበሩት የግል ድርጅቶች ላይ ክትትል በማድረግ የኮሮና ቫይረስ ኮቨድ 19 ምክንያት በማድረግ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተመርኩዞ በትኩረት እየሠራ እንደሆነም ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም የመጣ ስጋት እንደመሆኑ ከሱ ጋር ተያይዥ ሆነው ለሚመጡት ችግሮች ምላሽ ለመስጠት ደንብ ወቶለታል በደምቡ መሰረትም እየሠራን እንገኛለን ብለዋል። ወረርሽኙን አስመልክቶ የሚመጡትን ሠራተኞችን መቀነስ (ማባረር) እንዳይኖር መመሪያ በመውጣቱ ተፈፃሚ የመሆን ግዴታ አለበት። ለዚህም ሠራተኞችን ቀጥረው የሚገኙ ድርጅቶች ይህን ማክበር አለባቸው በማለት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር ኮንፌዴራሽን የውጭ እና የሕዝብ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ መአሾ በሪሁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ ከሆነ አዋጁ ላይ የሠራተኛ ቅነሳ እንዳይኖር፣ ሠራተኞች ከመደብና ደሞዛቸው ተቀናሽ እንዳሆን በወጣው መመርያ መሠረት፣ አሠሪዎች መተዳደር እንዳለባቸው በመግለፅ የወጣውን አዋጅ ተግባራዊ በማያደርጉት ላይ ክትትል እየተደረገ እንደሆነ አውስተዋል።
መአሾ እንደተናገሩት የተወሰኑ እንቅስቃሴዎች የተስተዋሉ ሲሆን፣ እነዚህን የሠራተኛ ቅነሳ እንቅስቃሴዎች ከኢፌዴሪ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በተጨማሪም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተግባራዊ እንዳይሆን አድርገናል በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ከዚህ በኋላም ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥም አስፈላጊውን ያህል ክትትል በማድረግ ከሚመለከተው አካላት ጋር በመሆን ችግሮች እንዲፈቱ እናደርጋለን ብለዋል። ከዛም በተጨማሪ የተወሰኑ ቅሬታዎች እና ጥቆማዎች ነበሩ። ነገር ግን የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርስና ሠራተኞችም ከሥራቸው ሳይፈናቀሉ እንዲስተካከል አድርገናል ሲሉ መአሾ በሪሁ አስታውቀዋል።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣ በኋላ አዋጁን ተላልፈው ሠራተኞቻቸውን የሚቀንሱ እና የደሞዝ ቅነሳ የሚያደርጉ ተቋማት እንዳሉ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012



