በጋምቤላ ክልል በ66 ሚሊዮን ብር የመከላከያ ካምፕ ሊገነባ ነው

0
792

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር በጋምቤላ ክልል በ66 ሚሊዮን ብር ወጪ የመከላከያ ካምፕ ለማስገንባት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጡን አስታወቀ። ግንባታው በአንድ ዓመት ወስጥ ለመገንባት እቅድ ተይዞለታል ተብሏል።
የግንባታ መሰረተ ድንጋዩን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ እና በመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል መሰለ መሰረት አስቀምጠዋል። ሚኒስቴሩ የሚያስገነባው ካምፕ የግንባታ መሰረተ ድንጋዩ ሚያዚያ 29/2012 በኢታንግ ልዩ ወረዳ መቀመጡ ተገልጿል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሉት የካምፑ መገንባት በክልሉ ያለውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል። በመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል መሰለ መሰረት በበኩላቸው የሻለቃ መኖሪያ ካምፑ መገንባት ለአካባቢው ልማት፣ ኢኮኖሚና ሰላም መስፈን ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉ አክለዋል።
በ78 ሔክታር መሬት ላይ የሚካሄደው የካምፑ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አስታውቀዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው፣ የካምፑ ግንባታ የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ በተጨማሪ የሥራ እድልን ከመፍጠር አንፃር አስተዋጽኦው የጎላ እንደሚሆን አብራርተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት በክልሉ በጎግ ወረዳ፣ በጋምቤላ ወረዳና በኢታንግ ልዩ ወረዳ የሠራዊት መኖሪያ ቤቶች፣ ካምፖችና ሜካናይዝድ የከባድ ጦር መሣሪያ ማእከላት ለመገንባት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የክልሉን ሰላም ይበልጥ የሚያጎለብት እንደሆነ አመልክተዋል።
በተለይም ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር በሰፊው የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ በተለያዩ ጊዜያት በሙርሌ ታጣቂዎች የሚደርሰውን ጥቃት በመከላከል ረገድ ላሳዩት ወገናዊነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here