በሚያዝያ ወር 2012 የተመዘገበው የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ19 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ።
የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የዋጋ ግሽበት ረዘም ያለ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ የሚያሳይ እና ግሽበቱ የተለያዩ ዓይነት ምርቶች ዋጋ የተካተተበት ሲሆን፣ በኹሉም ምርቶች ዋጋ ላይ የታየው የዋጋ ግሽበት በአማካኝ ተሰልቶ ይፋ እንደተደረገ ታውቋል። በዚህም መሰረት በሚያዝያ ወር 2012 አገራዊ የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ የምግብ የዋጋ ግሽበት በ23 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ያሳየ ሲሆን፣ የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ግሽበት ደግሞ በ14 ነጥብ 4 መቶ ጭማሪ ማሳየቱን ለማወቅ ተችሏል።
የሚያዝያ ወር 2012 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ22 ነጥብ 9 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል። ይህንንም ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ በሚል ሲከፋፈሉ፤ የምግብ ዋጋ ግሽበት የሚያዝያ ወር 2012 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ25 ነጥብ 9 በመቶ ጭማሪ እንደታየበት ለማወቅ ተችሏል።
በተገባደደው ወር በኹሉም የእህል ዓይነቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ የተስተዋለ ሲሆን፤ በስጋ እና በአንዳንድ ተፈላጊ የአትክልት ዓይነቶች ላይም ጭማሪ መታየቱን የዋጋ ግሽበቱን በሚመለከት በወጣው ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል።
ከዚህም በመነሳት ተፈላጊ በሆኑ አትክልት ዓይነቶች ላይ በተለይም ነጭ ሽንኩርት፣ ድንችና በርበሬ የዋጋ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን፤ በርበሬ በንጽጽር በምግብ ኢንዴክስ ውስጥ ከፍተኛ መቶኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ የታየው የዋጋ ጭማሪ በዚሁ ከቀጠለ የዋጋ ግሽበቱን ሊያባብስ እንደሚችል ተተንብዮለታል።
ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ዋጋ ከአሁኑ ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በንጽጽር ዝቅተኛ ስለነበር የዋጋ ግሽበቱ በያዝነው ወር ከፍ ብሏል። በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የሚያዝያ ወር 2012 ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጋር ሲነፃፀርም፣ የ19 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት በተከታታይ ጭማሪ እንዳሳየም በሪፖርቱ ተካትቷል።
ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ ትምባሆ፣ አነቃቂዎች (ጫት)፣ ልብስና መጫሚያ፣ የቤት ኪራይ፣ የቤት እንክብካቤና የኃይል ምንጮች (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማስጌጫዎች፣ የቤት መሥሪያ ቁሳቁሶች፣ ትራንስፖርት እና ሕክምና ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ መሆኑ ይፋ ተደርጓል።
ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012



