“ጅብ የማያውቁት አገር ሔዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ“
(የምክር ቤት አባል ተስፋየ ዳባ)
“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ዥግራ ናት ይሏታል“
(የምክር ቤት አባል ገብረእግዚአብሔር አርአያ)
በአገር አቀፍ ደረጃ በየአምስት ዓመቱ እንዲካሔድ በሕገ መንግሥቱ የተቀመተው አገራዊ ምርጫ በዚህ ዓመት ነሐሴ /2012 እንዲካሔድ ቀን ተቆርጦለት እንደነበር የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች እየተከናወኑ በነበረበት ወቅት በዓለም አቀፍ ብሎም በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት አስቸኳይ ጊዜ መታወጁ እና አገር አቀፍ ምርጫን ብቻ ሳይሆን ከምርጫ በፊት የሚከወኑ ቅድመ ምርጫ ዝግጅቶችንም ማካሔድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል በሚል አራት አማራጮችን ከመንግስት ወገን በማቅረብ እንዲተላለፍ መወሰኑ ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ምርጫው ከኮቪድ 19 ጋር በተገናኘ ማካሔድ የማይቻልበት ሁኔታ ላይ መደረሱን በማውሳት አራት አማራጮችን አስቀምጠዋል።
ምክር ቤቱን መበተን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ እና የሕገ መንግሥት ትርጉም መጠየቅ የሚሉ አማራጮች ቀርበዋል። በዚህም መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛውን እና የሕገ መንግሥት ትርጓሜ በሚለው በመስማማት ለሕግ ፍትሕና ዲሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ በመምራት ማጠናቀቁ ይታወቃል። ይህንም ተከትሎ በሚያዚያ 27/2012 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዲሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 7/2012 የሆነውን ለምክር ቤቱ እንዲጸድቅ አቅርቧል።
የውሳኔ ሃሳብ
በኢትዮጵያ የተከሰተውን ኮቪድ 19 ወረርሽኝን በአገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ መቆጣጠር እስኪቻል ድረስ አገራዊ ምርጫው መካሔድ እንደሌለበት ይገልጻል። ይህንም በመመርኮዝ የምርቻው መተላለፍ ሕገ መንግስታዊ በሆነ አካሔድና እንዲሁም የአገርን እና የሕዝብን ሕልውና ብሎም ሉዐላዊነትን ከተለያዩ ስጋቶች መከላከል በሚያስችል መልኩ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አጽኖት ይሰጣል።
የኮቪድ 19 ስጋትን መቆጣጠር ከተቻለ በኋላ ነጻ፣ ሁሉን አቀፍ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ተዐማኒነት ያለው ምርጫ ለማድረግ አስቻይ በሆነ አውድ ምርጫው መካሔድ እንዳለበት በጽኑ ታምኗል።
የምርቻ ወቅት እና አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አብረው በሚከሰሱበት ወቅት፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታውን ምላሽ ሰጥቶ አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው ካበቃ በኋላ ምርጫ ሊካሔድ የሚችልበትን መንገድ በሕገ መንግስቱ አለመደንገጉ ተስተውሏል። ሕገ መንግሥቱ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ስለተለያዩ የመንግሥት አካላት የሥልጣን ዘመን እና የምርጫ ጊዜ የደነገጋቸው ድንጋጌዎች እንዲሁም ሕገ መንግስታዊው የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ተጣጥመው እና ተናበው ተግባራዊ የሚደረጉበትን ሁኔታ በሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ ማግኘት እንደሚገባ በመረዳት የውሳኔ ሃሳቡ እንዲሰናዳ መደረጉን ያስረዳል።
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 84 (1) እና በአዋጅ ቁጥር 798/2005 ሕገ መንግስቱን ስለመተርጎም በተደነገገው አንቀጽ 3(2) (ሐ) መሰረት “ በፍርድ ሊወሰን በማይችል በማንኛው ጉዳይ ላይ የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ሲሶው ወይም ከዛ በላይ በሆኑ በፌደራል ወይም በክልል ምክር ቤት አባላት ወይም በፌደራልም ሆነ በክልል አስፈጻሚ አካላት ለአጣሪ ጉባኤ ይቀርባል“ ሲል ይደነግጋል። አጣሪው ጉባኤም በአንቀጽ 84 (1) መሰረት ጉዳችን የማጣራት ስልጣን ያለው ሲሆን ሕገ መንግስቱን የመተርጎም አስፈላጊነት ሆኖ ሲያገኘው ለፌደሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የውሳ ሃሳብ የማቅረብ ኃላፊነት አለበት ሲል ያስቀምጣል። ይህንም ተከትሎ በሕገ መንግስታዊ ትርጉም ጥያቄ ለአጣሪ ጉባኤ እና ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲቀርብ የተደረገው ሒደት በ23 ድጋፍ እና በ3 ተቃውሞ ቀርቦ ነበር።
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 54 (1) የሕዝብ ተወካች ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ በማለት ሲደነግግ፤ አንቀጽ 58 (3) የምክር ቤቱ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሒዶ ይጠናቀቃል ሲል ይደነግጋል። ይህ የሆነው ታዲያ መደበኛ እና ምርጫ ለማካሔድ ምቹ ኔታዎች በሚያጋጥሙበት መልካም ጊዜ ታሳቢ ተደርጎ እንደወጣ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ከቋሚ ኮሚቴው ተብራርቷል።
ይሁን እንጂ የቅድመ ምርቻ ዝግጅቶችና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ሲከሰት እና በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ በማይቻልበት ሁኔታ የስራ ዘመኑ ያለቀው የምክር ቤት ዕጣ ፋንታ ምን መሆን እንደሚኖርት በግልጽ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ እና የሕገ መንግስት ክፍተት በመታየቱ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 54(1)፣ 58 (3) እና አንቀጽ 93 ከሕገ መንግስቱ አላማና ግቦች እንዲሁም መሰረታዊ መርሆች ጋር በማስተባበር እና በማስተሳሰር ትርጉም እንዲሰጣቸው የቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳን ለምክር ቤቱ አቅርቦ ነበር።
በውሳኔ ሃሳቡም በርካታ እሰጥ አገባዎች እና ዝልልፎች ተስተውለውበታል። ይህንም ተከትሎ ከግራ እና ከቀኝ ይሰነዘር የነበረውን የቃላት ልውውጥ ለምክር ቤቱ ክብር እና ደረጃ የማይመጥኑ ቃላት ናቸው እየተባሉ በአባላት እስኪተቹ ድረስ ነገሮች ከረር ወዳለ አቅጣጫ መሄዳቸውን አዲስ ማለዳ ታዝባለች።
ፍጥጫው በሕገ መንግሥቱ መሰረት ምርጫው መካሔድ ይኖርበታል ካልሆነ ግን ሕገ መንግስቱን መጣስ ነው የሚሉ እና አሁን ያለንበት አገራዊ ሁኔታ አገራዊ ምርጫውን ማካሔድ የሚያስችልበት ቁመና ላይ አይደለንም በሚል የኹለት ተቃራኒ ሀሳቦች ፍትጊያ ነበር።
“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ዥግራ ናት ይሏታል“ (የምክር ቤት አባል ገብረእግዚአብሔር አርአያ)
በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 7/2012 ላይ የመጀመሪያውን ጠንከር ያለ ትችት ያቀረቡት ገብረእግዚአብሔር አርአያ፤ በቋሚ ኮሚቴው የቀረበው ውሳኔ ሃሳብ ከተለመደው አሰራር ወጣ ያለ ነው ሲሉ ይጀምራሉ። “ ባለ ድርሻ አካላት መድረክ ለምን አልተካሔደም? ምክንያቱም በርከት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አልተደረገም። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት አልተካተቱም ወይም እንዲወያዩ አልተደረገም። ውሳኔ ሃሳቡ ላይ የአስረጅነት እና የሌሎች ተሳታፊዎች በአግባቡ የተከናወነ ባለመሆኑ በወቅቱ የደረሰን ዝርዝር ሃሳብ የለም“ ሲሉ ይናገራሉ።
ገበረ እግዚአብሔር አያይዘውም የተሔደበበት አካሔድ ከምክር ቤቱ የአሰራር ደንብ 628 ወጣ ያለ እና የሚጣረስ እንደሆነ ያስረዳሉ። ‹‹ጊዜውም ራሱ ረጋ ያለ እና በአግባቡ የታየበት አግባብ አይደለም የሚል መነሻ ሃሳብ አለኝ። አንደኛ ተሰጠው የውሳኔ ሃሳብ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ስለ ምርጫ ያሚያሻማ ነገር ፍጹም በሌለው፣ የሚቃረን ሃሳ በሌለው፤ ለምንድነው ወደ ሌላ አካል የተመራው? በደምብ መታየት አለበት። ለመሆኑ ቋሚ ኮሚቴው ከሕገ መንግሥት አንጻር ምን ያህል በነጻነት አይቶታል? አንደኛ በጣም በጥድፊያ ነው የሔደበት ፤ በነጻነት ተረጋግቶ ለምንድነው ያላየው የሚለው ጉዳይ በደንብ ቢታይ የሚል ሃሳብ አለኝ›› ሲሉ ይናገራሉ።
ገብረእግዚአብሔር ቀጥለውም ፤ ‹‹በሌላ ደግሞ እኛ ስነመራው፣ እኛ ድጋፍ ስነሰጥ፣ አሁን የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ሳይመራ ምክር ቤቱ ጊዜ ወስዶ ወደ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚመለከተው ኅብረተሰብ ክፍል ጋር እንዲመክርበት፣ መፍትሔ እንዲሰጥበት እንጂ ወደ ሌላ አካል ተላልፎ እንዲሰጥ ሰጠነው ድምጽ አልነበረም።
ፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫ ይራዘም አይራዘም ብሎ የመተርጎም ስልጣን የለውም። ቀድሞውኑም ምርጫ የሚካሔደው በአምስት ዓመት እንደሆነ በሕገ መንግስቱ ቁልጭ ተደርጎ ተቀምጧል። ስለዚህ በምን አግባብ ወደ ፌደሬሽን መተላለፉ ከሕገ መንግሥት ጥሰት አንጻር የሚታይ ነው። ስለዚህ የውሳኔ ሃሳቡ ተቀባይነት የለውም የሚል መነሻ ሃሳብ አለኝ›› ሲሉ ሃሳባቸውን በግልጽ አስተጋብተዋል። ለዚህም ደግሞ እንደማብራሪያ ከላይ የጠቀሷቸው ሕገ መንግስታዊ አይደሉም ካሏቸው ባለፈ ተጨማሪ ምክንያቶችንም ሲያብራሩ፤ ‹‹በአገራችን ያለው እና የደረሰብን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ላችን ተባብረን በጋራ እንዲወገድ መስራት አለብን፣ ጊዜ መስጠት የለብንም፣ተረባርበን እየሰራን ነው ኹሉም አካል እየተሳተፈ ነው።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር፣ ሃሳብ፣ ተሰጥቶበት ከሕዝብ ጋር ውይይት በማካሔድ መርሃ ግብር ወጥቶለት አሁንም በሚገባ መታየት አለበት የሚል ሃሳብ አለኝ። ከዚህ ውጭ ከሆነ እና እኔ ያልኩት የሚል ከሆነ ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ዥግራ ዥግራ ይሏትላ እንደሚባለው አሁን የቀረቡት አማራጮች ከሕገ መንግስቱ ውጭ ናቸው። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የስልጣን ዕድሜን ለማራዘም የሚደረግ ሽርጉድ ካልሆነ በስተቀር ትክክለኛ መፍትሔ አይደለም›› ብለው ሲያበቁ ይህን መሰረት አድርጎ ከሕገ መንግስቱ ውጭ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሊቆም ይባል ሲሉ ሃሳበቸውን ሰንዝረዋል።
በኢትዮጵያ በብሔር ብሔረሰቦች ባልተመረጠ መንግስት እንዲመራ የሚፈቅድለት የለም የሚሉት የምክር ቤት አባሉ፤ ከመስከረም 25/2013 ጀምሮ በሕገ መንግስቱ መሰረት አገርን የሚመራ ፓርቲ በሕዝብ ካልተመረጠ አገርን የሚመራ እንደማይኖርና ምክር ቤቱም ሆነ የፌደሬሽን ምክር ቤት በአምስት ዓመት ውስጥ የስራ ዘመናቸው ያልቃል እንጂ የስራ ዘመናቸውን ማራዘም እንደማይችሉም ጨምረው ገልጸዋል። ሕገ መንግስቱ እየተናደ እንዴት ሆኖ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሔድ የሚቻልበት መንገድም እንደማይታያቸው አስምረውበታል።
የገብረእግዚአብሔርን ሃሳብ የሚጋሩት የሕወሓት ስራ አስፈጻሚ እና የምክር ቤት አባል የሆኑት አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) በበኩላቸው ጉዳዩ ከባድ እንደሆነና በትኩርት ሊጤን የሚገባ እንደሆነ ሳይግጹ አላለፉም። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ዘጠኝን በመጥቀስ ስልጣን መያዝ የሚቻለው በሕገ መንግስቱ በተቀመጠው መንገድ ብቻ እንደሆነም ያናገራሉ። አዲስዓለም ቀጥለውም እንዲህ አይት የሕገ መንግስት ክፍተት ሲፈጠር የፖለቲካ ውሳኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነም ይጠቅሳሉ። ‹‹ሕገ መንግስቱ የትርጉም ክፍተት የለውም መድረኩ ተዘጋጅቶ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው እንዴት መካሔድ አለበት በሚል መወያየትና የጋራ ውሳኔ ሃሳብ ያስፈልገዋል።
ወደ ሌላ አካል መሻገሩ የማይመስል አካሄድ ነው። አንድ ፓርቲ ይህን ለማድረግ አቅሙም አቋምም የለውም፤ ነገር ግን ይሆነኛል፣ ይቻለኛል በሚል የሚደረግ ነገር ጦሰኛ ነው ፤ ይህ ጦስ ደግሞ ሕዝብና አገርን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይከታል፤ አገረ መንግስቱንም ችግር ውስጥ ይከታል›› ሲሉም ሃሳበቸውን ሰንዝረዋል። ‹‹ድንጋይ መወራወሩ አይጠቅምም። ይህቺ አገር ችግር ውስጥ ነው ያለችው መፍትሔ መፈለግ አለብን፤ ከዚህ ችግርም መውጣት አለብን። ስለሆነም ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበው ሃሳብ ተገቢ አይደለም፤ ሕገ መንግስቱን የሚጋፋ ነው ›› ሲሉም ደምድመዋል።
“ጅብ የማያውቁት አገር ሔዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ“ (ተስፋየ ዳባ)
አገራዊ መርጫውን ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን እና ትኩርት መሰጠት የሚገባው በአሁኑ ሰዓት ለወረርሽኙ እና እንዴት መመከት እንደሚገባ የሚለውን ሃሳብ የሚያቀነቅኑት የምክር ቤት አባል እንዲሁም ውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው ተስፋየ ዳባ ናቸው። በኣለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ወረርሽኝ ተከትሎ የተለያዩ አገራት የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን በተለይም ደግሞ ከምርጫ ጋር የተያያዘ ኹነቶቻቸውን በተለይም 47 የሚሆኑ አገራት ምርጫቸውን ማራዘማቸውን ጠቅሰዋል።
ተስፋየ አስቀድሞ በተነሳው እና በምክር ቤት አባሉ ገብረእግዚአብሔር ለተተረተው ተረት ግብረ መለስ የሆነ ተረት በመተረት ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት። ‹‹ጅብ የማያውቁት አገር ሔዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ ። ይህን የምልበት ምክንያት በዚህ የምክር ቤት ታሪክ ውስጥ ምን ስንሰራ እንደቆየን ወደ ኋላ መለስ ብለን ማየቱ ጥሩ ይመስለኛል። በመጀመሪያ ደረጃ ሕጎችን እንዴት ነበር ስናወጣ የነበረው? ያን ጊዜ ሕገ መንግስቶችን እንዴት ነበር ስናሻሽል የነበረው? የሚለውን ነገር እኔ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው የምፈልጋቸው ኹለት ሕገ መንግስት ድንጋጌዎች ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ እንዴት እንደተሻሻሉ ማሳየትም እፈልጋለሁ›› ሲሉ ይነገራሉ። በመጀመሪያ ደረጃ የሕግ አወጣጥ ሂደትን በተመለከተ የሚናገሩት ተስፋየ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በምክር ቤቱ የአባላትና ስነ ምግባር ደንብ መሰረት አማራጭ ስልቶችን አስቀምጧል በተለይም የባለ ድርሻ አካላትን ውይይት፤ ነገር ግን አስቸኳይ ሆኖ ካገኘው በመጀመሪያ ንባብ ወደ ኹለተኛ ንባብ ታላልፎ ውሳኔ የሚያሳልፍበት አግባብ መኖሩን ጠቅሰዋል። ተስፋየ ቀጥለውም ‹‹ኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው የሚያስፈልገው ስንት አዋጆች በተለይም ትልቅ ትኩረት የሚሹ እንደ ሊዝ አዋጅ አይነት ስንት አርሶ አደሮችን ከጥቅም ውጪ ያደረገ እና ስንት አርሶ አደሮችን ያስለቀሰ የሊዝ አዋጅ በዚህ ምክር ቤት ውስጥ እንዴት እንደወጣ ይህን የመንግስት ተጠሪ ሲመሩት የነበሩት የሕወሓት ጓድ እንዴት አድርገው ሲመሩት እንደነበር እናውቃለን›› ሲሉ ተናግረዋል።
ውይይት ሊደረግበት ይገባል በተባለበት ወቅት የምክር ቤት አባላት የውይይት ዕድል ሳይፈቀድ የመሬትን ጉዳይ የሚያስተዳድር የሊዝ አዋጅ ሕገ መንግሥቱን በተጻረረ ሁኔታ ጸድቋል ሲሉ አውስተዋል። በኹለተኛ ደረጃ የቀድሞውን የኢፌዲሪ ፕሬዘዳንት ነጋሲ ጉዳዳ (ዶ/ር) ጉዳይ ያነሱት ተስፋየ ‹‹ የዶክተር ነጋሲ ጊዳዳን ጥቅማ ጥቅም ለመከልከል ሲባል ምክር ቤቱ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ከማድረጉ በፊት አባላትን ሰብስቦ የውሳ ሃሳብ እንዲዘጋጅ ተደርጎ ተወሰነውንም ማስታወስ ያስፈልጋል›› ሲሉ ኢ ሕገ መንግስታዊ ስራዎች ባለፉት ዓመታት ተሰርተዋል በማለት ሃሳበቸውን ሰንዝረዋል። ይህንም ተመርኩዘው አሁን ደርሶ ስነ ስርዓትና የሕገ መንግስት ተቆርቋሪ መሆን የማይታረቅ ሃሳብ መሆኑንም አውስተዋል።
ምርጫን በተመለከተ በሕገ መንግስቱ በግልጽ መቀመጡን የሚናገሩት ተስፋየ ነገር ግን ይህ ነገር ይከሰታል ተብሎ እንዳልተገለፀ እና ‹‹በፊት ያሻሻልነው የሕዝብና ቤት ቆጠራን የሚመለከት አንቀጽ 103 እንዴት ነው ያሻሻልነው? ቁልች ድርጎ ሕገ መንግስቱ በ10 ዓመት ቆጠራ ይካሔዳል የሚለውን በአንድ ነጭ ወረቀት ነው ሕገ መንግስቱ የተሸሻለው።
አንቀጽ 104 ሕገ መንግስት ማሻሻያ የሕዝብ ውይይት ተደርጎ ሕዝብ ውሳኔ እና አስተያየት እንዲሰጥበት ያስገድዳል፤ እሱን አልፎ ምከር ቤቶች ሲሶው የሚሆነው በክልል ምክር ቤታቸው እንዲወያዩበትና እንዲያጸድቁት ይጠይቃል፤ ከዚህም በተጨማሪ ኹለቱ ምክር ቤቶች በኹለት ሦስተኛ እንዲያጸድቁት ይፈለጋል። ነገር ግን ይህ ኹሉ ሕገ መንግስታዊ አካሔድ ተጥሶ ነው የሕዝብና ቤት ቆጠራ አንቀጽ 103 የተሸሻለው›› የሚሉት ተስፋየ የኹሉም ክልል ብሔር ብሔረሰቦች ሳይስማሙበት የክልሎችን አፈ ጉባኤዎችና ርዕሳነ ብሔራት በመሰብሰብ በቀጥታ ትዕዛዝ አንቀጹ እንዲሻሻል ተደርጓል ሲሉ አውስተዋል።
በጋራ ግብር የመጣልን በሚመለከት በሕ መንግስቱ አንቀጽ 98 በሚመለከት የተደረገውን ማሻሻያ ተስፋየ ሲናገሩ ሕዝቡ ሳይወያይበትና ክልሎች ይሁንታቸውን ሳይሰጡ በተለይም ደግሞ ኹለት ክልሎች መልስ ባልሰጡበት ሁኔታ ተሸሽሏል። ከዚህ ቀደም በሕወሓት በኩል ሲደረግ የነበረውን የሕገ መንግስት ማሻሻያ አሁን ቢደረግ ተለዋዋጭ ያለመሆንን ጉዳይ ያሳይ ነበር ሲሉም ተስፋየ ይናገራሉ።
ሕግ የሚተረጎምበትን አጋጣሚዎች ተስፋየ ሲያስቀምጡ፤ ‹‹ሕጉ ዝም ሲል፣ ሕጉ ሲጋጭ፣ ሕጉ ክፍተት ሲኖረው›› በሚል ይከፍሉታል። የዚህን ጉዳይ እና ኃላፊነት ለፌደሬሽን ምክር ቤት የተሰጠበትን አጋጣሚም ተስፋየ ሲገልጹ ‹‹ያን ጊዜ የሽግግር መንግሥት (ፓርላማው) በወቅቱ ይመራ የነበረው በኢህአዲግ ሊቀመንበር ነበር። ፕሬዘዳንትም አፈ ጉባኤም አቶ መለስ ነበሩ። እኛ ያልመጣልን ሃሳብ ካለ ከወቅቱ ከአገር ከኢኮኖሚ አኳያ የሚገኙ ክፍተቶች ካሉ ትርጉም ሊሰጥባቸው እንደሚያስፈልግ እና እንዲሻሻሉ እንደሚያስገድድ የሚጠቁም ነው።›› የሚሉት ተስፋየ የፌደሬሽን ምክር ቤትን በተመለከተ ተነሳውን የስልጣን ጉዳይ አሁን የመጣ ሳይሆን ቀድሞም ነበረ እንደሆነ አውስተዋል።
‹‹ዛሬ ተነስተን በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 ያቋቋምነውን ዛሬ ልንተቸው አይገባም›› ሲሉም ይናገራሉ። ከቀረቡት አራቱ አማራጮች ውጪ የፖለቲካ አማራጭ የሚለው ሀሳብ ሌላ ፍላጎት ያለው እና እርስ በራሱ የሚጋች ሃሳብ ነው የሚሉት ተስፋየ በአንቀጽ 9 ያለ ሕገ መንግስት አካሔድ ስልጣን መያዝ እንደማይቻል በተነገረበት ሁኔታ የፖለቲካ አማራጭ ማለት የማይታረቅ ሃሳብ እንደሆነ አስረግጠዋል።
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 51 (15) ምርጫን የማካሔድ ጉዳይ የፌደራል መንግስት ጉዳይ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአንቀጽ 50 (8) ለፌደራል ተሰጠውን ስልጣን ክልሎች የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው እንደሚደነግግም በተስፋየ ዳባ ተጠቁሟል። በአንቀጽ 62(9) መሰረት ለፌደሬሽን ምክር ቤት ተሰጠው ስልጣን ‹‹በማንኛውም ክልል ሕገ መንግስትን በመጣስ ሕ መንግስታዊስርዓትን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንደሚገባ ሊታወቅ ይገባል›› ብለዋል።
ተስፋየ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ጥሪም በሕ መንግስቱ መሰረት የተቋቋመው አካል ‹‹በአንድ ቡድን ሲብጠለጠል ዝም ሊባል አይገባም፤ ስለዚህ አሁንም ቢሆን ሕገ መንግስት ይከበር እያልን ስለሆነ ከሕገ መንግስት ማዕቀፍ ውጭ የምንሔዳቸው እንቅስቃሴ አጠንክረን የቋሚ ኮሚቴው በደንብ እና በጥሩ ሁኔታ ያቀረበው አማራጭ ጊዜ ቆጣቢ እና በአጠቃላይ በሕገ መንግስቱ ውስጥ የተሰጠውን የፌደሬሽን ምክር ቤት ስልጣን ከግብ ለማድረስ የተቋቋመ እስከ ሆነ ድረስ እሱን ከግብ ለማድረስ ሕገ መንግስታዊ መፍትሔ ነው። ከሕገ መንግስታዊ አማራጭ ውጪ ያሉትን ማንሳት ኢ ሕ መንግስታዊ ነው አገርንም እንደማፍረስ ነው። ከህደት ነው፣ ከሕገ መንግስቱ ውጪ ሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጠቅላላ በግሌ አስተያየት የባንዳ አካሔዶች ናቸው›› ሲሉ ተስፋየ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
የተስፋየን ሃሳብ በመጋራት በርካቶች ሃሳባቸውን አሰምተዋል። ከቀረቡት አማራጮች ውስጥ ምክር ቤቱን መበተን የሚለው አማራጭከስራ ዘመኑ ማብቂያ ቀደም ብሎ የሚደረግ በመሆኑ እና ጊዜው በማለፉ መደረግ እንደማይችል እና መንግስትንም አቅም የሚዳክም በመሆኑ የተሸለ አማራጭ ባለመሆኑ እንዳልተመረጠ ተጠቅሶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚለውም አሁን ኢትዮያ ያለችበት ሁኔታ በዛው መሆኑ እና ቀድሞ የተተገበረ መሆኑን እንደማሳያ ቀርቧል። እንዲሁም ሕ መንግስትን ማሻሻል የሚለው አማራጭ ደግሞ አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ የማይቻል እንደሆነም ተጠቁሟል። በመሆኑን ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ተገቢ እና ሕገ መንግስታዊ መሆኑን በርካቶች በሰጡት አስተያየት ተደምጧል።
ብሔር ብሔረሰቦችን ከወረርሽኝ ለመዳን እየፈለጉ ባለበት ሁኔታ ምርጫን ለማካሔድ ማሰብ ትክክል ያልሆነ ሃሳብ እደሆነም ከምክር ቤቱ ተነስቷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ቀረበው ውሳኔ ሃሳብ በተመለከተ በርካታ አስተያየቶች እና ክርክሮች የተደመጡበት ሲሆን በተደረገው በመጨረሻም በ25 ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012