በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገ 4,120 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 142 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው እንዲሁም ተጨማሪ 3 ሰዎች በቫረሱ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
በዚህም እስካሁን በሀገሪቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 1,486 ደርሷል።
ሚኒስትሯ እንደገለፁት ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 84 ወንድና 57 ሴቶች ሲሆኑ እድሜያቸውም ከ 7 ዓመት እስከ 78 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከእነሱም ውስጥ 140 በዜግነት ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ 2ቱ ደግሞ የፖርቹጋል እና የጅቡቲ ዜጎች ናቸው፡፡
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች
126 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፣
2 ሰዎች ከአፋር ክልል፣
7 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣
6 ሰዎች ከአማራ ክልልና 1 ሰው ከሶማሌ ክልል መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በቫይረሱ ምክንያት የተጨማሪ 3 ሰዎች (የ70 ዓመት የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ የ46 ዓመት የኦርሚያ ክልል ነዋሪ እንዲሁም የ40 ዓመት የደቡብ ክልል ነዋሪ) ሕይወት ያለፈ ሲሆን በዚህም በአጠቃላይ በሀገራችን በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 17 ደርሷል፡፡
በሌላ በኩል ተጨማሪ 15 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ 246 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
ቫይረሱ በሀገራችን እንደተገኘ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በተደረጉት የላብራቶሪ ምርመራዎች ከተገኙ እለታዊ ቁጥሮች ጋር ሲነፃፀርም በእነዚህ ሁለት ሳምንታት የተመዘገቡት የታማሚዎች ቁጥር ከ300 መቶኛ በላይ ጭማሪን ማሳየቱን የጤና ሚንስትር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያስታወቁ ሲሆን ህብረተሰቡም ከምን ጊዜውም በላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የወረርሽኙን መዛመት ይገታ ዘንድ አሳስበዋል፡፡





