የአሜሪካው ሜሪየም ዌብስተር መዝገበ ቃላት ላይ የሚገኘው ዘረኝነት የሚለው ቃል ትርጉም ሊሻሻል መሆኑ ተገለፀ

0
1030

የአሜሪካው ሜሪየም ዌብስተር መዝገበ ቃላት እንደ ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ሁሉ ታዋቂና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መዝገበ ቃላት ነው።

አንዲት ወጣት ጥቁር አሜሪካዊት ታዲያ ለዚህ መዝገበ ቃላት አሳታሚ በጻፈቸው ደብዳቤ ምክንያት መዝገበ ቃላቱ ዘረኝነት ወይም (racism) ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የትርጉም ፍቺ ማሻሻያ ለማድረግ ወስኗል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ለቃሉ ትርጉም ፍቺ መሻሻል ምክንያት የሆነችው ኬኔዲ ሚችሀም የምትባል የ22 ዓመት ወጣት ስትሆን ከአዮዋ ግዛት ደሬክ ዩኒቨርስቲ ገና መመረቋ ነው።

ያደገችው በፈርጉሰን ሚዙሪ ሲሆን፤ ይህ አካባቢ ደግሞ በጸረ ዘረኝነት ትግል ላይ ብዙ ታሪክ ያለው ቦታ ነው። ምናልባት አስተዳደጓና ያደገችበት ሰፈር ስለ ዘረኝነት ብዙ እንድታውጠነጥን ሳያደርጋት እንዳልቀረም ተገልጿል።

ወጣቷ ሚችሀም ለአሳታሚዎቹ በጻፈችው ደብዳቤ ዘረኝነት ለሚለው ቃል የተሰጠው ትርጉም “አንድ የጎደለው ነገር አለ” ስትል አስገንዝባለች። ይህም ‘መዋቅራዊ ዘረኝነት’ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ መግደፉ ነው።

አንድ በድርጅቱ በአርታኢነት በከፍተኛ ኃላፊነት የሚሰሩ ሰው ልጅቱ ያነሳቸው ነጥብ መሠረታዊ በመሆኑ ማሻሻያው ይደረጋል ብለዋል። የመዝገበ ቃላቱ አሰናጆችም ይህንኑ አረጋግጠዋል።
አሳታሚው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በአሜሪካ ሜኔሶታ ግዛት፣ በሚኒያ ፖሊስ ከተማ ባለፈው ወር ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ ጥቁር በአንድ ነጭ ፖሊስ የተፈጸመበት አሰቃቂ ግድያን ተከትሎ ተቃውሞ በመቀጣጠሉ ነው።

ሚችሀም ለዚህ ያነሳሳት ዘረኝነትን በተለየ መንገድ ስትመለከትና ሰዎች ዘረኛ ስለመሆናቸው ስትነግራቸው ወደ መዝገበ ቃላቱ በመሄድ እንዴት ዘረኛ እንዳልሆኑ ሊያስረዷት እየሞከሩ ስላስቸገሯት ነው።

ከእነዚህ አጋጣሚዎች በኋላ ሚችሀም የመዝገበ ቃላቱ አሰናጆች ለዘረኝነት ሰፋ ያለ ትርጉም ሊሰጡት እንደሚገባ በማመኗ ደብዳቤውን ለመጻፍ ተነሳስታለች።

አሁን ለጊዜው ዘረኝነት በሜርየም ዌብስተር መዝገበ ቃላት ሦስት ትርጉሞች ብቻ ተሰጥቶት ይገኛል፤

1ኛ. ዘረኝነት ማለት አንድ ማኅበረሰብ በቆዳ ቀለሙ የበላይ ነው፤ አንዱ ከሌላው ይበልጣል ብሎ ማሰብ

2ኛ. ዘርን መሰረት ባደረገ ሁኔታ የተቋቋመ የፖለቲካ ፕሮግራም ወይም አስተሳሰቡን በዚሁ በዘር ልዩነት ላይ መሰረት አድርጎ ማደራጀት

3ኛ. የዘር ልዩነት እና መድልዎ ናቸው

ሚችሀም ለቢቢሲ እንደተናገረቸው ከላይ የተዘረዘሩት የቃሉ ብያኔዎች ያላካተቷቸው ሕያው የዘረኝነት ልማዶችና ከሃይል አሰላለፍ ጋር ያለውን ቁርኝቶች አሉ።

ወጣቷም በግንቦት 28 ለመዝገበ ቃላቱ አርታኢያን ደብዳቤ የላከች ሲሆን በዚህ ደብዳቤዋ ላይ አጽንኦት የሰጠችው ዘረኝነት ሲባል “ማኅበራዊና ተቋማዊ” ረቂቅ ቅርጽ ሊኖረው እንደሚችልና በቆዳ ቀለም የተነሳ አንዱ ለሌላው የሚሰጠው የአስተሳሰብ ብያኔም ዘረኝነት እንደሆነ አብራርታለች።

“ባልጠበቅኩት ሁኔታ ለዚህ ደብዳቤዬ በቀጣዩ ቀን ምላሽ ተላከልኝ” ትላለች ሚችሀም።

ከተከታታይ የደብዳቤ ልውውጦች በኋላ የመዝገበ ቃላት አሳታሚው ይህ ጉዳይ በአፋጣኝ ሊስተካከል እንደሚገባና የቃላት ብያኔው እርሷ እንዳለችው ሆኖ መታተም እንዳለበት ይፋ አድርጓል።

የሜሪየም ዌብስተርስ መዝገበ ቃላት የአርታኢያን ሥራ አስኪያጅ ፒተር ሶኮሎውስኪ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ማሻሻያው “ረቂቅና ተቋማዊ ዘረኝነቶችን የሚይዝ ትርጓሜ እንዲያካትት ይደረጋል። ይህን የተመለከተ አንድ ሁለት ምሳሌም አብሮ ተካትቶ ይታተማል” ብለዋል።

አዲሱን ማሻሻያ የተደረገበትን ቅጽም በነሐሴ ወር ታትሞ ይወጣል ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።

ምንጊዜም ቢሆን “ሰዎች ዘረኝነትን በተመለከተ ያላቸው ትርጉም ተመሳሳይ ሊሆን ይገባዋል፤ መግባባት ይኖርብናል” ይላሉ ፒተር ሶኮሎዉስኪ።

ዘረኝነት የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ ወይም በገቢር የሚፈጸም ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብ ውስጥ የሚቀበር ረቂቅ መልክ እንዳለው ለዘመናት ቸል ሲባል የቆየ ጉዳይ ነው።

ይህ በመዝገበ ቃላት ደረጃ መቀመጡ ሰዎች ዘረኝነትን በተቀራራቢ ትርጉም እንዲረዱት ያግዛቸዋል ተብሎ ይጠበቃል መባሉን ከቢቢሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here