ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት እና አመታዊ የውሀ አለቃቀቅ በተመለከተ የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ላይ ያላትን አቋም ግልፅ አደረገች

0
689
የኢትዮጵያ ፣ የግብፅ እና የሱዳን የውሀ ሚኒስትሮች የታላቁን የህዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት እና አመታዊ የውሀ አለቃቀቅን በተመለከተ የሚያደርጉት የሶስትዮሽ ድርድር በትናንትናው እለትም ቀጥሎ ተካሂዷል፡፡
 
በዚህም የሁለተኛው ቀን ውይይት ላይ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሶስትዮሽ ትብብር ውይይቱን በተመለከተ ያላትን አቋም ለሁለቱ የተፋሰስ ሀገራት ግልፅ አድርጋለች፡፡
 
የኢፌድሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ ያወጣውን ጋዜጣዊ መግለጫ በቀጥታ ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ወደ አማርኛ በመተርጎም አዲስ ማለዳ እንደሚከተለው አቅርባዋለች፡፡
 
በዚህም መሰረት
1. ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውሀ ሙሌት እና ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ህግ እና መመሪያዎች ላይ ቀና ትብብር እና ድርድር ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ በመግለፅ፤ በሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ ውይይቱን እንደገና በመጀመሩ ደስተኛነቷን ገልፃለች፡፡
 
2. ኢትዮጵያ በሶስቱ ሀገራት መካከል የተደረጉ ስምምነቶች ሙሉ በሙሉ መከበር እንደሚገባቸውም አስገንዝባለች፡፡
 
3. የሦስቱ ሀገራት ስምምነት ላይ ደርሰው ልምድ እና ተሞክሮዎችን እንዲያካፍሏቸው ካልጠየቁ በስተቀር የታዛቢዎች ሚና ድርድር ከመመልከት እና ከመታዘብ የዘለለ መሆን እንደሌለበትም ኢትዮጵያ አሳስባለች፡፡
 
4. ከየካቲት 5-6 ቀን 2012 በተካሄደው ስብሰባ የሦስቱ አገሮች የሕግና የቴክኒክ ቡድኖች ያቀረቡት የሥራ ሰነድ የድርድሩ መሠረት መሆን እንደሚገባው አስታውቃ፤ በዚህም አውድ ፣. ኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሀ ሙሌት እና ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም መመሪያዎች እና ህጎችን በተመለከተ የራሷን አማራጭ ሃሳብ አካፍላለች፤ ሱዳንም እንዲሁ አቋሟን የሚያሳይ ሰነድ አስገብታለች፡፡
 
5. በሶስትዮሽ ውይይቱ የመጀመሪያ ቀን ማለትም ሰኔ 2/2012 እንደተስማሙት የህዳሴው ግድብ ድርድር እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከማክሰኞ ፣ አርብ እና እሑድ በስተቀር ባሉት ሁሉም ቀናት በኢንተርኔት የሚደረገው የቪድዮ ውይይት የሚቀጥል መሆኑም ተገልጿል፡፡
 
ኢትዮጵያ በሶስትዮሽ ውይይቱ ጊዜ በተወያይ ወገኖች መካከል ጠንካራ እምነት መገንባት እጅግ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ያሳሰበች ሲሆን፣ ሆኖም ግን የግብፅ ቀጣይነት ባለው የሶስትዮሽ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ፈቅዳ በተመሳሳይ ሰአት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም / ቤት የውጭ ዲፕሎማሲ ጫና እንዲያሳድር የምታደርገው ጥረት በድርድሩ ላይ ግልፅነት እና መተማመን እንዲኖር የሚያደርግ አይደለም ስትል ኢትዮጵያ አስታውቃለች፡፡
 
ስለሆነም ኢትዮጵያ በድርድሩ ላይ የሚሳተፉ አካላት እውነተኛ የሆነ የውይይት እና የድርድር አቋምን ይዘው እንዲሳተፉ ጥሪን በማቅረብ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰቡም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በድርድሩ እንዲሳተፉ እንዲያበረታታ በጥብቅ ያሳስባል የሚል ጠንካራ እምነት እንዳላትም አስታውቃለች፡፡
 
በመጨረሻም ኢትዮጵያ የሶስትዮሽ ድርድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት ሙሉ በሙሉ ትሰራለች፡፡
 
የኢፌድሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here