አንድ ወር ተኩል መብራት የጠፋባቸው ነዋሪዎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ገለጹ

0
828

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ሲኤምሲ በተለምዶ ፊጋ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሐኮማል ሪል እስቴት በተገነባ የጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች መብራት አንድ ወር ከ15 ቀን በላይ በመጥፋቱ ችግር ውስጥ መሆናቸውን እና ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኗሪዎቹ በሚኖሩበት ሕንጻ መብራት ከተቋረጠ አንድ ወር ከግማሽ ቢሆነውም እስካሁን መፍትሔ እንዳላገኙና ለተጨማሪ ወጭ እየተዳረጉ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የሐኮማል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተከራይተው፣ ገዝተውና ቅድሚያ ክፍያ ከፍለው በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚኖሩ ሰዎች ይገኙበታል። እነዚህ ኗሪዎች በትራንስፎርመር መቃጠል ምክንያት መብራት ባለማግኘታቸው ለተለያዩ ችግሮች እንደተጋለጡ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከ 100 በላይ የሚሆኑ አባውራዎች በመብራት ዕጦት እየተንገላቱ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፤ ችግሩ እንዲፈታላቸው በተደጋጋሚ ወደ ሚመለከተው አካል በመቅረብ ቢጠይቁም እስካሁን ድረስ መፍትሔ አጥተን እየተቸገርን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ነዋሪዎቹ መልስ በማጣታቸው እንደ አማራጭ ሐኮማል አፓርትመንት ባቀረበው አማራጭ በቀን ለሰባት ስዓት ብቻ በጀነሬተር መብራት ለማግኘት ለ10 ቀን 500 ብር እንድከፍሉ ተጠይቀው፣ በድርድር ለ10 ቀን 300 ብር እየከፈሉ በቀን ሰባት ስዓት መብራት ለማግኘት ተስማምተው በወር ለ900 ብር ያልተፈለገ ወጭ እየተዳረጉ መሆኑን በምሬት ይናገራሉ።

አዲስ ማለዳ በመኖሪያ ቤቶች ላይ ሐኮማል አፓርትመንትን ወክለው ይሰራሉ የተባሉ አንድ የኮሚቴ አባል ለማናገር ሞክራ እኔ ሀኮማልን አልወክልም በማለት አስተባብለዋል። አዲስ ማለዳ ያናገረቻቸው ተወካይ ሀኮማልን አለመወከላቸውን ቢገልጹም፣ ያጋጠመው የትራንፎርመር ብልሽት ጥገናው እስከሚደረግ ድረስ ሀኮማል በጊዜያዊነት ለኗሪዎቹ የጀነሬተር ኪራይ ችሎ መብራት እንዲያገኙ እያደረገ ነው ብለዋል።

ለነዋሪዎቹ የሚቀርበው በቀን የሰባት ስዓት መብራት የኃይል ውስንነት ስለሚያጋጥመው በመብራት አማካኝነት የሚከወኑ ሥራዎችን ለመከወን እንደተቸገሩ ገልጸዋል።
በጋራ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ያለ መብራት መኖር በብዙ መልኩ አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት ኗሪዎቹ፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ አንዲሰጣቸው ጥሪ አቅረበዋል።

የቀረበውን ቅሬታ በሚመለከት የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው በተለያዩ አካባቢዎች ተደጋጋሚ የሆኑ የኃይል መቆራረጦች ቢኖሩም በመሐል አዲስ አበባ ይህን ያህል ቀናት የተራዘመ የኃይል መቋረጥ ሊፈጠር እንደማይችል እና በአስቸኳይ ጉዳዩን እንደሚያጣራው አስታውቋል።

በትራንስፎርመር መበላሸት በተመለከተ ለማስተካከል ከሦስት እስከ አራት ቀን የሚፈጅ መሆኑን የገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቀለ የመሬት ውስጥ መስመሮች መፈንዳት የሚያጋጥምበት ጊዜያቶች በርካታ በመሆናቸው በተለያዩ አካባቢዎች ከአንድ ቀን እስከ አንድ ቀን ተኩል የሚፈጅ የማስተካከያ ስራ የሚያሰራ ሲሆን የተባለውን ጉዳይ ግን በግልጽ እንደማያውቁ እና መረጃውም እንደሌላቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በሐኮማል የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲገነባላቸው ውል ገብተው በዚሁ የጋራ መኖሪያዎች ላይ ቅድሚያ ክፍያ ክፍለው ያሰሩ ሰዎች ሐኮማል አጠናቅቄቀ አስረክባለሁ ባለበት ጊዜ ሳያጠናቅቅ በመቅረቱ ተቸግረው እንደነበርም በመኖሪያ ቤቶች ላይ ድርሻ ያላቸው ነዋሪዎች አስታውሰዋል። የመኖሪያ ቤቶች ግንባት ዘጠኝ ዓመት እንደፈጀም ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ከሐኮማል የመኖሪያ ቤቶች ላይ ቅድሚያ ክፍያ ከፍለው አሰርተው እና ገዝተው የገቡ ነዋሪዎች ሀኮማል ሪል እስቴት አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን እንዳላሟላላቸው ተናግረዋል።

የግበንባታ ጊዜው በዘገየበት ጊዜም ቅድመ ክፍያ የከፈሉ ሰዎች የግንባታው የፊኒሽንግ ሥራ በመዘግየቱ በራሳቸው ወጭ የፊኒሽንግ ሥራ ሰርተው እንደገቡም አስተውሰዋል። በተጨማሪም የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ሰዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታና ፕላን እንደሌላቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እነዚህን እና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ለተጨማሪ ማብራሪያ ወደ ሐኮማል ኮንስትራክሽን ድርጅት ያደረግናቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች ከሓኮማል ኮንስትራክሽን በኩል ጥሪውን ለመመለስ እና ማብራሪያ ለመስተት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here