የትግራይ ክልል ምክር ቤት ክልላዊ ምርጫው ይህ ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት እንዲካሄድ መወሰኑ አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫው መቼ እንደሚካሄድና በማን እንደሚከናወን የጠቀሰው ነገር አለመኖሩ ተገልጿል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ታረቀ ለቢቢሲ እንደገለፁት ምርጫው ከጵጉሜ በፊት እንዲካሄድ መወሰኑን አረጋግጠዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘንድሮ ነሐሴ መጨረሻ ላይ ለማካሄድ ታቅዶ የነበረውን አገራዊ ምርጫ ማከናወን አልችልም ማለቱ የሚታወስ ሲሆን በዚህም ምክንያት የሕገ መንግሥት አጣሪ የመንግሥትን የሥራ ዘመን ባማራዘም ምርጫው የሚራዘምበትን አማራጮች ካቀረበ በኋላ፤ የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ የሚለው አማራጭ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል።
ጉዳዩን የመረመረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ሆኖ እስከቀጠለ ድስረ ሁሉም የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች በሥራ ላይ እንዲቆዩ እና ምርጫው የበሽታው ስጋት መወገዱ ከተረጋገጠ በኋላ ከ9 ወር እስከ 1 ዓመት ባለው ጊዜ እንዲካሄድ ሲል ከቀናት በፊት ወስኗል።
የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ህወሓት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ምርጫው መካሄድ አለበት ሲል አቋሙን ሲያንጸባርቅ የነበረ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ዘመኑን በማራዘም ምርጫ ለማካሄድ ያቀረበውን አማራጭ በመቃውም፤ በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት አደርጋለሁ ማለቱም ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱኳን ሚደቅሳ “ክልላዊ ምርጫውን ለማካሄድ አስበው ከሆነ ትክክለኛ አካሄድ አይሆንም። ሕገ-መንግሥታዊም አይሆንም” በማለት፤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 102 የተቋቋመውና እርሳቸው የሚመሩት ምርጫ ቦርድ በፌደራል፣ በክልል እና በቀበሌ ደረጃ የሚካሄዱ ምርጫዎችን የማስፈጸም ብቸኛ ስልጣን የተሰጠው መሆኑን አስታውቀው ነበር ሲል ከቢቢሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡



