የገቢዎች ሚኒስቴር ከግንቦት 1 እስከ 30 2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተደረገው ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ በድምሩ 135.9 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና የተለያዩ ዓይነት ህገወጥ የጦር መሣሪያዎችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
እንደ ባለ ስልጣን መስርያ ቤቱ ገለፃ ከሆነ የኮንትሮባንድ እቃዎቹ በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት በሁሉም የሀገሪቱ ጉምሩክ ኬላ ጣቢያዎች በሞያሌ፣ ጅግጅጋ፣ አዋሽ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ጅማ፣ ሞጆ፣ አዳማ እና በሌሎች የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ላይ በተደረገው ከፍተኛ ቁጥጥርና ፍተሻ ነው፡፡
እነዚህ በቁጥጥር ስር የዋሉ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ማለትም በቱሪስት ስም የገቡ ተሸከርካሪዎች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ አልባሳት፣ ጊዜው ያለፈበት የተለያዩ ዓይነት የምግብ ቁሳቁሶች እና ጎጂ የሆኑ የአደንዛዥ ዕፆች እና ሺሻ ሲሆኑ ከዚህም በተጨማሪ እነዚን ህገወጥ የኮንትሮባንድ እቃዎች ህጋዊ ለማስመሰል የተሳሳቱ ሰነዶችን እና ንግድ በማቅረብ አጭበርብረው ለማሳለፍ በመሞከራቸው ለገቢዎች ሚኒስቴር ተጨማሪ ግብርና ታክስ እንዲከፍሉ ተደርጓል፡፡ እነዚህም የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተይዘው ለመንግስትና ህዝብ ገቢ እንዲሆኑ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል።
የገቢዎች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት ኡሚ አባ ጁማል ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች በተጨማሪ በባህር ዳር ሰርባ የጉምሩክ ኬላ መቆጣጠሪያ ጣቢያ የቱርክ ሲሪት የሆኑ 348 ዘመናዊ ሽጉጦች እና 300 ጥይቶች በጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች፣ ሠራተኞችና በፀጥታ አካላት በተደረገው ከፍተኛ ፍተሻና ትብብር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ በግንቦት ወር 18 ነጥብ 35 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰብስቧል ያሉት ኡሚ አባ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በግንቦት ወር 23 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 18 ነጥብ 35 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 77 ነጥብ 8 በመቶ መሳካት መቻሉንም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡
ይህም የእቅድ አፈፃፀም ከሀገር ውስጥ ታክስ 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን ከውጪ ቀረጥና ታክስ ደግሞ 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መቻሉንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
አፈፃፀሙም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ3 ነጥብ 08 ቢሊዮን ብር ወይም የ20.15 በመቶ ዕድገት አለው፡፡
በሌላ በኩል የተቋሙ የ2012 በጀት ዓመት እቅድ 270 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ያቀደ ሲሆን በ11 ወራት ከታቀደው 242 ነጥብ 94 ቢለዮን ውስጥ 217 ነጥብ 24 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ 89 ነጥብ 42 በመቶ ማድረስ ተችሏል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ይህም አፈፃፀም ከባለፈው በጀት ዓመት 11 ወራት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 38.79 ቢሊዮን ወይም 21.74 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፡፡
እንደሚታወቀው በሀገራችንና በአለም አቀፍ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ እንደ ከዚህ በፊቱ ከዕቅድ በላይ ለመሰብሰብ እንቅፋት ቢሆንበትም፤ ሆኖም ግን ሚኒስቴር መ/ቤቱ ቀደም ብሎ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማካካት ከቫይረሱ በፊት ባሉት ተከታታይ ወራት የላቀ አፈፃፀም ለመሰብሰብ ችሏል፡፡
በተጨማሪም ገቢዎች ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃለፊው ኡሚ አባ ጀማል ይሄ የግንቦት ወር ብቻ ሪፖርት መሆኑን ተናግረዋል፡፡



