የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆነውን የቤት እድሳት መርሀ ግብርን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ በሚኖሩበት አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ቀነኒ ሁንዴ መኖሪያ ቤት በመገኘት የቤት እድሳት መርሀግብሩን ያስጀመሩ ሲሆን በየአካባቢው የሚገኙ ለኑሮ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አቅመደካማዎች መኖሪያ ቤታቸው የሚታደስም ተገልጿል።
በመኖሪያ ቤት እድሳቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶችና የተለያዩ አካላት የሚሳተፉ መሆኑም ታውቋል።
ከቤት እድሳት መርሀግብር በተጨማሪም “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሰው” እርስ በእርስ የመደጋገፍ መርሀግብር በይፋ ይጀመራል።
በመርሀግብሩ እያንዳንዱ ቤተሰብ በአቅራቢያው ላለ ሌላ የኑሮ አቅሙ ደከም ላለ ቤተሰብ ድጋፍ የሚያደርግበትና ያለውን የሚያካፍልበት ነው ተብሏል።
“በአንድ ቤተሰብ ለአንድ ሰው” መርሀግብር የከተማዋ ነዋሪዎች፣በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ታዋቂ ግለሰቦች፣የከተማዋ ባለሀብቶችና የከተማዋ አመራሮች እንደሚሳተፉበትም ከከንቲባው ፅሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።





