መጠንከር አሁን ነው!

0
508

ገና ከትልሙ ጀምሮ በኋላም ላይ ወደ መሬት ወርዶ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ከዛሬ ዘጠኝ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሳንካ ያላጣው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አሁን ደግሞ ነገሮች እየተካረሩ በተለይም ደግሞ ከግብጽ በኩል እጅግ የበረታ ተቃውሞው እየቀረበ ይገኛል። ይህም ደግሞ ግብጽ ከዘመናት በፊት ጀምሮ ለዘመናት የተጠቀመችውን የናይልን ውሃ ከኢትዮጵያ ጠብታ ውሃ ዘለላ ሳይቀርባት አሁንም ለቀጣይ ዘመናት መተቀም እና የመጠቀም መብቷን ማሻገርም እንደሆነ ይጠቀሳል።

ከአዲስ አበባ እስከ ዋሽግተን፤ ከካርቱም እስከ ካይሮ ያልተገባበት እና ለስምምነት ይልታደሙበት መድረክ ባይኖርም ዕልባት ላይ የመድረሱ ጉዳይ ግን እንደ እምቧይ ካብ ገነባነው ሲሉ እየተናደ ዓመታትን አወዛግቧል። በኢትዮጵያ በኩል የግድቡን መገንባት ተከትሎ ከየትኛውም ኣለም አቀፋዊ ድርጅት ወይም ለጋሽ አገር ብድር እና ድጋፍ ያልተወሰደ እና ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን የዕመበለት መቀነት የተፈለቀቀ ገንዘብ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ‹‹የትኛውም ምድራዊ ኃይል ግድቡን ከመገንባት የሚያስቆመን የለም›› በሚል በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ዘንድ ሲነገር ተሰምቷል። ይህ ፈርጠም ያለ መግለቻ ታዲያ ከዚህ ቀደም በነበሩት ኹለት ጠቅላይ ሚንስትሮች ዘንድ ሲስተጋባ የመጣ እና ግብጽ በተደጋጋሚ ሳሊኒ የግንባታ ድርጅት መገኛ ኢጣል ድረስ በመሔድ በግንባታው ላይ እንዳይሳተፍ እንዳደረገችበት እና ሳይሳካ መቅረቱን የተመረኮዘ እንደሆነ ሊታወስ ይገባል።

በቅርቡ በሦስቱ የዓባይ የላይኛው ተፋሰስ አገራት አሜሪካንን እና የዓለም ባንክን እንደ ታዛቢ፣ አሸማጋይ እና ሌሎች ድርሻዎችን በመስጠት የአራተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የታየበት የሽምግልናና ድርድር መርሃ ግብር በዋሽንግተን፣ አዲስ አበባ፣ ካይሮ እና ካርቱም ቢካሔዱም እልባት ላይ መድረስ እንደተናፈቀ ቀርቷል። አንድ ጊዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሌላ ጊዜ ደግሞ በቴክኒካል ኮሚቴዎች የተለያዩ ጉንጭ አልፋ ድርድሮች በዜሮ የተባዙ ውጤቶችን ከማስከተል ባለፈ ምንም ጠብየሚል ነገር ሳይኖራቸው አልፈዋል። ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ ከግብጽ በኩል የሚሰማው እና የሚደረገው ለድርድር አልመች ባይነት ነው።

በቅርቡ ግብጽ ከድርድሩ አስቀድማ እስከ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ በመግባት ኢትዮጵያ በአባይ ዙሪያ ላይ የያዘችውን አቋም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተለው እና በኢትጵያ ላይ ጫና በማሳደር ከግንባታው እንድትታቀብ የሚወተውት ደጅ መጥናቶችን ስታካሂድ እንደነበር በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሲነገር ሰንብቷል። አንድ እግሯን ድረድር ውስጥ ሌላ እግሯን ደግሞ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘንድ በማድረግ በኢትዮጵያ እና በዓባይ ላይ ዘርፈ ብዙ ዘመቻ የምታደርገው ግብጽ ታዲያ ከኢትዮጵያ ወገን ጠንከር ያለ ምላሽ ሊሰጣት እና የእስከ ዛሬው ትዕግስት እና መለማመጥ ይብቃ ስትል አዲስ ማለዳ ትናገራለች።

በቅርቡ ካለፈው የካቲት ወር ከተቋረጠ በኋላ የሦስቱ አገራት መሪዎች ለየብቻ ከመከሩ በኋላ በቴክኒክ ደረጃ እንዲቀጥል ውሳኔ ላይ በመደረሱ ድርድሩ ቀጥሏል። በዚህ ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበሩ የተለሳለሰ አቋሟን በመግታት ፈርጠም ያለ የዲፕሎማሲም ሆነ ቴክኒካል የበላይነትን ይዛ አገራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ይኖርባታል ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ እንዳሉት ይህ ጉዳይ ቤጅንግ ወይም ዋሽንግተን ተሒዶ ይግባኝ ሚባልበት ሳይሆን ከኢትዮያዊያን ኪስ በሚወጣ ገንዘብ እስከተገነባ ድረስ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ይግባኝ እንደሚባልበት ሁሉ መንግስትም በዚህ ሰዓት ትኛውንም አለም አቀፋዊ ጫና ሳይመለከት በሙሉ ትኩረት ወደ ቀጣዩ ግድቡ የግንባታ ደረጃ መሸጋገር እንደሚኖርበት አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። ይህ በሚሆንበት ወቀትም የአሜሪካው ደኅንነት መስሪያ ቤት በትዊተር ገጹ እንዳሰፈረው ኢትዮጵያ የድርድሩ ፍጻሜ ሳይታይ ግድቡን ውሃ መሙላት እንደማትችል አስታውቋል። ነገር ግን ይህ ኢትዮጵያን የመጫን አካሔድ ሳይገድበን በተባበረ እና በጠነከረ እርምጃ ግድቡን ከዳር ለማድረስ ከመቼውም በበለጠ አሁን መጠንከራችን ግድ እንደሚሆን አዲስ ማለዳ አቋም ነው። ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ግብጽን ውትወታ ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰው ጫና ገና ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚጠብቅ ሲሆን በተለይም ደግሞ የጥቂት ሳምንታት ዕድሜ የሚቀረው የግድቡን ውሃ የመሙላት ሂደት ተከትሎ እጅግ የበረታ ተቃውሞ እና ጫና ስለሞኖር እንደ አገር መንግስት እና ሕዝብ በአንድነት መጠንከር ይኖርብናል ስትል አዲስ ማለዳ መልእክቷን ታስተላልፋለች። በአገር ውስጥ ያለውን ጥቃቅን አለመግባባቶችን እንደ መግቢያ እና እንደመጠቀሚያ በማድረግም አገርን የማተራመስ አካሔድ ሊኖር ስለሚችልም መንግስት ይህነ ከወዲሁ በመገንዘብ ጥብቅ ቁጥጥር እና ቀዳዳዎችን የመድፈን ስራ መስራት እንደሚኖርበትም አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። በዓለም ትልቁን ወንዝ አቅጣጫ የማስቀየር ስራ እንደመስራት ከባዱ ስራ አልነበረም እና በዚህም ኢትዮጵያ እጅግ የበረታ እና የጠነከረ ስራ መስራቷ የሚያኮራ ቢሆንም ግድቡ ተጠናቆ ለታሰበለት ዓላማ እስኪውል ድረስ የጠነከረ የሞት ሽረት ተጋድሎ ኢትዮጵያ ማድረግ እንደሚኖርባት መገንዘብ ይገባል። በዚህም ረገድ ኢትዮጵያ በቀጠናው ላይ ያላትን ተቀባይነት እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም በቅርቡ በኬንያ መንግስት በኩል የተቸረውን የግድቡን ግንባት ድጋፍ ወደ ሌሎች አጎራባች እና ተፋሰስ አገራት ዘንድ በማጋባት ጠንካራ ድጋፍ ማግኘት እና አገራቱም ከግድቡ ሊጠቀሙ የሚችሉበትን አሰራር በማቅረብ ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆሙበትን ዕድል መጨመር ያስፈልጋል።

የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጀስቲን ሙቱሪ በኬንያ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለምን በጽ/ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሄደው ድርድር ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ሊካሄድ የሚገባው ነው ብለዋል። ኢትዮጵያውያን እንደሌሎች የአካባቢው አገሮች የተፈጥሮ ኃብታቸውን በመጠቀም የመልማት ተፈጥሮኣዊ መብት እንዳላቸው እንደሚገነዘቡም አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።

በውይይቱም አምባሳደር መለስ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ መካከል እየተካሄደ ስላለው የሶስትዮሽ ድርድር ገለፃ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ እና ኬንያ ፓርላማዎች መካከል በተለያዩ ክፍለ-አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተደጋግፎ ለመስራት ከመግባባት ደርሰዋል። ይህ ጠንካራ ድጋፍ ታዲያ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስንቅ በመሆን ለበለጠ ስራ የመነሻ እና ከቀደሙት ጊዜያት በላይ መጠንከሪያ ሊሆን እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

በድርድር ብቻ ሳይሆን ግብጽም በሔደችበት ዲፖሎማሲ መንገድም በመሔድ የግድቡን ተጠቃሚነት ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ይኖርባታል። ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ኮንግረስ ቀርቦ ጉዳዩ ኹለት ጎራዎችን ከፍሎ ሲያከራክር መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ጎራም ኢትዮጵያ የራሷን ጠንካራ አባባዮች በማሰማራት የድጋፍ ጎራውን በዲፕሎማሲ በመደገፍ የአለም አቀፍ ጫናውን እና ርብርቡን መታገል ትችላለች። በቀደሙት ኣመታት በግድቡ ዙሪያ ይደረጉ የነበሩትን የጥበቃስራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር የሚገባ ሲሆን በተለይም ደግሞ በቅርቡ በግብጽ በኩል ተደርጓል ስለተባለው እና በግድቡ የግንባታ ስፍራ ብጥብጥ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች መኖራቸው የተሰማ ሲሆን ቀጣይም መንግስት እና ሕዝብ በንቃት አካባቢውን እና አገርን እንደ አጠቃላይ መጠበቅ ይኖርበታል። በኹሉም ዘርፍ የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደሚኖር እና ካለም እየጠነከረ መሔዱ ማይቀር ሲሆን በተለይም ደግሞ ምዕራባዊያንን በጠንካራ የዲፖሎማሲ ግንኙነት ጫናቸውን እንዱያቆሙ ማድረግ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። እንደ አገር በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ትኩረታችንን ሳናሸሽ የሕዝብ አንጡራ ሀብት የፈሰሰበት አገራዊ ሐብት ተጠብቆ እና በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ገብቶ ኢትዮጵያን ከድኅነት ለማውጣት በሚደረገው ርብርብ ትልቁን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ መረባረብ ይኖርብናል ስትል አዲስ ማለዳ ሀሳቧን ትደመድማለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here