የ1.6 ቢሊዬን ብር የስንዴ ግዢ የውል ስምምነት ተፈረመ

0
1253

በአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር (48 ሚሊዬን ዶላር) 240 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዢ ለመፈጸም የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከአቅራቢ ድርጅቶች ጋር የውል ስምምነት ተፈረመ።

የስንዴ ግዢው ከመደበኛው የኢትዮጵያ ዓታዊ ስንዴ ግዥ በተጨማሪ ለቀጣዩ በጀት ዓመት ያጋጥማል ተብሎ ለሚጠበቀው የምግብ ዕጥረት እንዲቀርፍ ታስቦ ግዢው እንደሚፈጸም ፌደራል ንብረት ግዢ እና ማስወገድ አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በጨረታው የተሳተፉ ስምንት ተጫራቾች ባቀረቡት የቴክኒክ የመጫረቻ ሰነድ ላይ አስፈላጊው የቅድመ እና የቴክኒክ ግምገማ ተደርጎ በግምገማ ውጤቱ መሰረት ሆራይዘን ኢኤስሲ ግሩፕ በቅድመ ግምገማ የወደቀ ሲሆን ቀሪዎቹ ሰባት ተጫራቾች ወደ ቀጣይ የፋይናንስ ግምገማ ማለፋቸውን የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ መልካሙ ደፋሊ ተናግረዋል።

በቅድመ ግምገማ እና በቴክኒክ ግምገማ ውጤቱ ላይ ምንም ዓይነት ቅሬታ ባለመቅረቡ ለፋይናንስ ውድድር ያለፉት ሰባት ተጫራቾች የፋይናንስ ፕሮፖዛል መክፈቻ ቀን ግንቦት 05/2012 ከጠዋቱ 3፡30 ላይ የተጫራቾች ተወካዮች በተገኙበት ተከፍቷል።

በሎት አንድ ላይ አሸናፊ የሆነው ተጫራች ጄምኮርፕ ኮሞዲቲስ ትሬዲንግ አንድ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከዩክሬን ገዝቶ የአገሪቱ ቾርኖሞርስክ ወደብ ድረስ ለማድረስ 204.97 ዶላር የጠየቀ ሲሆን 100 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለመሸጥ 20.4 ሚሊዬን ዶላር አቅርቧል። ይህንን ክፍያ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያጠናቅቅም 180 ቀናት ሰጥቷል።

በሎት ኹለትም ላይ አሸናፊ የሆነው ተጫራች ይሔው ጄምኮርፕ ኮሞዲቲስ ትሬዲንግ ሲሆን አንድ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ከሩስያ ገዝቶ የአገሪቱ ኖቮሮሲይስክ ወደብ ለማድረስ 202.33 ዶላር ያቀረበ ሲሆን 100 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለመሸጥ 20.2 ሚሊዬን ዶላር አቅርቧል። ይህንን ክፍያ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያጠናቅቅም 180 ቀናት ሰጥቷል።

በአጠቃላይ ለብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አገልግሎት የሚውል የ200 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዢ እስከ አቅራቢው ወደብ ድረስ የ180 ቀናት ብድርን ጨምሮ በድምሩ 40.7 ሚሊዬን ዶላር በሚያወጣ ዋጋ አሸናፊ ሆኖ ከተመረጠው

ጄምኮርፕ ኮሞዲቲስ ትሬዲንግ ግዥዉ እንዲፈፀም ተወስኗል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ስንዴውን ከዩክሬን እና ሩሲያ ወደቦች ወደ ጅቡቲ ወደብ እንዲጭን የአሽናፊነት ደብዳቤ መሰጠቱን መልካሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በመንግሥት ግዢ መመሪያ አንቀጽ 16.4.2ረ መሰረት ተጫራቹ ከአሸነፈበት መጠን ላይ 20 በመቶ (የ40 ሺህ ቶን) ስንዴ በመጨመር 8.1 ሚሊዬን ዶላር ጭማሪ በማድረግ በአጠቃላይ የ240 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ በአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዬን ብር (48 ሚሊዮን ዶላር) ውል መፈጸሙን ኤጀንሲው አስታውቋል።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከዚህ በፊት ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ ከአውስትራሊያ መንግሥት ጋር የ120 ሚሊዮን ዶላር የስንዴ ግዢ ስምምነት በዚሁ ወር አድርጋለች። እንዲሁም ኢትዮጵያ ከሩስያ መንግሥት ጋር የስንዴ ግብይት ስምምነት ለማድረግ ሂደት ላይ እንዳለች እና በቅርቡ ስምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አዲስ ማለዳ ዘግባ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።

የ200 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ በዓለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ ለመፈፀም የካቲት 15 ቀን 2012 በኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ የጨረታ ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር። ጨረታው ሚያዚያ 22 ቀን 2012 ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ተዘግቶ በዚሁ ዕለት ከጠዋቱ 4፡15 ላይ የተጫራቾች ተወካይ በተገኙበት ተከፍቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here