‹‹የጊዮን ሆቴሉ ሳባ አዳራሽ በድንገት አልፈረሰም››

0
540

በግዮን ሆቴል ስር ይገኝ የነበረው ሳባ አዳራሽ ህዳር 23/2012 በድንገት ፈርሷል መባሉ ሐሰት እንደሆነ ማንነታቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉ የሆቴሉ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

ከ7 ወር በፊት በድንገት ፈርሷል ተብሎ በመገናኛ ብዙኋን የተዘገበው ሳባ አዳራሽ አፈራረስ ድንገተኛ እንዳልነበረ፣ ነገር ግን እንደዛ እንዲታወቅ እንደተፈለገ ሠራተኞቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አሁን ድርጅቱን እያስተዳደሩ ካሉት ሰው በፊት የነበሩት ሥራ አስኪያጅ ሰፊ አዳራሽ እንዲፈጠር ሳባ አዳራሽን ከሌላ አዳራሽ ጋር ለመቀላቀል ሲያደርጉ በነበረው ጥረት ችግር ተፈጥሮ አዳራሹ መፍረሱን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

ሠራተኞቹ ሳባ አዳራሽ 73 ዓመት የቆየ እና ከዚህ በኋላም ረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል ቅርስ ነበር፤ ነገር ግን እውቀትን መሰረት ያደረገ ሥራ ባለመሰራቱ የመደርመስ አደጋ ሊደርስበት ችሏል ሲሉ አስረድተዋል።

በጊዜውም ባለሙያ አይቶት የሳባ አዳራሽ ዋናው ምሰሶ ከተነካካ እንደሚፈርስ እና የቆመውም በእርሱ ድጋፍ እንደሆነ እንደተነገራቸው ሠራተኞቹ ያነሳሉ። ነገር ግን በጊዜው የነበሩት ሥራ አስኪያጅ የባለሙያውን ሀሳብ ወደ ጎን በመተው አንድ ላይ ለማድረግ ሲጥሩ እንደነበር እና በዚህ ሒደት ዋና ቋሚው (ምሰሶ) በመነካቱ ምክንያት አዳራሹ አቅም አጥቶ እንደተደረመሰ ምንጮቹ ተናግረዋል።

ሠራተኞቹ ‹‹ይህ ህንጻ እንዴት ፈረሰ ተብላችሁ ብትጠየቁ፣ በእራሱ ሳይነካ በድንገት ተደረመሰ በማለት እንድትመልሱ›› ብለው የሆቴሉ አስተዳዳሪዎች እንዳስገደዷቸው ተናግረዋል። በተጨማሪም ስለ አዳራሹ መፍረስ መንግሥት ምርመራ አላደረገም፣ ምንም ዓይነት የመቆርቆር ስሜትም አላሳየም ሲሉም ወቅሰዋል።
በዚህም ምክንያት ይላሉ ሠራተኞቹ በመደርመስ አደጋ ሳባ አዳራሽ ሙሉ ለሙሉ እንደወደመ ተደርጎ ህብረተሰቡ እንዲረዳ ተደርጓል።

በተጨማሪ የሳባ አዳራሽ በተደረመሰ ጊዜ የጊዮን ሆቴል ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ገበረፃድቃን አባይ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ አዲስ ማለዳ በስልክ አግኝታቸው የነበረ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ለተደረመሰው አዳራሽ የመድህን ክፍያ ሆቴሉ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት መደርመስ በስምምነቱ እንዳልተካተተ ጠቅሶ ውድቅ ማድረጉን አዲስ ማለዳ በ72ኛ እትሟ ጠቅሳ ነበር። ይህንን አስመልክቶ አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት መንግሥቱ መሃሩን ለውጥ እንዳለ አናግራ ተጨማሪ መረጃ በቅርቡ ከቅርንጫፍ እንዳልመጣ ምላሽ አግኝታለች።

ነገር ግን አዲስ ማለዳ በ72ተኛ እትሟ የመድህን ካሳ ሆቴሉ መከልከሉን አስመልክታ ባስነበበችው ዜና የመድን ድርጅቱ የጠቅላላ መድህን ጽ/ፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፍክሪ አብዱልመጅድ ሆቴሉ የረጅም ዘመን ደንበኛ በመሆኑ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የወደመውን ንብረት እያጠና መሆኑን ገልፀው ነበር። በዚህም መሠረት በጥናት የተገኘው 4.5 ሚሊዮን ብር ውድመት በእርዳታ መልክ ለሆቴሉ እንዲሰጥ በከፍተኛ አመራሮች መወሰኑን ገልፀው ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here