ያሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያን በተለይም ደግሞ መዲናችን አዲስ አበባ ከተማን እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ስር የሚተዳደሩ የክልል ከተሞችን ሲያስጨንቅ እና መግቢያ ቀዳዳ ሲያስጠፋ የሰነበተ ጉዳይ ነበር። ውልደቱን ከአዲስ አበባ በ125 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የምዕራብ ሸዋዋ አምቦ ከተማ ያደረገው እና የኦሮሞኛ ሙዚቃን ደረጃ አርቆ ሰቅሎታል የሚባልለት የጥበብ ሰው ከያኒው ሀጫሉ ሁንዴሳ በአዲስ አበባ ከተማ ገላን ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሰኞ ሰኔ 22/2012 ምሽት 3 ከ30 ላይ መገደሉ ነበር የግርግሩ መንስኤ።
ሀጫሉ መገደሉ ከተሰማበት እና ከተረጋገጠበት ሰዓት አንስቶ ነገሮች መልካቸውን ቀየሩ ሌሊቱን ሁሉ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሐዘናቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጹ እና ሲያስተጋቡ ማደር አይበለው ሰኞ ዕኩለ ሌሊትን አልፎ ማክሰኞ ማለዳ ሆነ።
በዚህ ወቅት ግን ነገሮች መልካቸውን ቀየሩ፤ ማክሰኞ ማለዳ ከፓውሎስ ሚሊኒየም ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወደ ትውልድ አገሩ መሸኘት የጀመረው ሀጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን ግን ሰላማዊነቱ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ችሎ ማለፍ አልቻለም ነበር።
ሀጫሉ አምቦ ከተማ አይቀበርም በሚል ከመንግስት እና ከሟች ቤተሰብ ጋር የተደረገውን ውይይት ወደ ጎን በመተው የተደራጁ ተባሉ ቡድኖች የሀጫሉን አስከሬን ከወዳጅ ዘመድ እና ከአጀቡት የመንግስት አካላት ዕጅ በመንጠቅ የመልስ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ያደርጋሉ። በዚህ ወቀት ታዲያ በተፈጠረ ግርግር እና መካረር የሟች ሀጫሉ ሁንዴሳ አጎት ከአስከሬን ነጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት የወንድማቸውን ልጅ ተከትሎው አሸለቡ ሌላ ተጨማሪ አስከሬንም በስፍራው ተገኘ።
ከዚሁ ግድያ በተመሳሳይም ከዚህ ቀደም በተከብቢሊሁ በሚል ከፍተኛ የኦሮሞ ወጣቶችን ማሰለፍ ችሎ የነበረው ጃዋር መሀመድም እንደ ፖሊስ መግለጫ ከሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው የኦረሚያ ባህል ማዕከል ተሰብስበው ሲመክሩ በነበሩ የኦሮሞ ባለስልጣናት ላይ አደጋ ለመጣል እና የዛሬ ዓመት የተፈጠረውን አሳዛኝ ሰኔ 15/2011 ክስተትን ለመድገም አሲረዋል በመባል እስከ ትግል ጓዳቸው እና አንዲት ሴትን ሲጨምር 35 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በበርቶች ዘንድ ምነው በዚህ ሰው ላይ የመንግስት ሆደ ሰፊነት ልክ አጣ ሲባልበት የነበረው ጃዋር መሐመድ ‹‹አይነኬ›› ሲሉትም ብዙዎች የሚጠሩት ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋል በብዙዎች ዘንድ ግርምትን እና መንግስትም በሕግ ማስከበር ላይ ከፍተኛ የሆነ ተነሳሽት እንደያዘ ማሳያ ተደርጎም እንደተወሰደ ማየት ተችሏል።
ኢትዮጵያ በተለይም መዲናችን ሸገር ክራሞቷን ከሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና ጀዋር ምን ሲባል ይታሰራል ባሉ የተቆጡ እና የተደራጁ ቡድኖችም ስትሸበር ሰንብታለች። ይሁን እንጂ ከአዲስ አበቤውም እንደከዚህ ቀደሙ የዝምታ እና ፍራቻ ምላሽ ሳይሆን በተደራጀ እና ሰፈሬን ፣ ከተማየን አላስነካም ባለ ጨዋነት እና ወኔ ነበር ግብረ መልስ የተሰጠው። መሰንበቻው ይህ ነበር።
ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012


