‹ኢንተርኔት› የሌለ ጊዜ!

0
874

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል። ይህም ለአገር ሰላምና ደኅንነት በሚል እንደሆነ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ከሚያደርጉ ሰዎች ወገን ቢሰማም፣ በአንጻሩ ‹ምስጢር ለመደበቅ ነው! ሰዎች እንዳይናገሩ ለማፈን ነው!› የሚሉም አሉ። መቅደስ ቹቹ ይህን ሐሳብ አንስተው፣ በተለይ አሁን ላይ ይልቁንም የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ አግልግሎቱ መቋረጡ የሚኖረውን ጉዳትና ጥቅም ለማስረዳት ሞክረዋል።

ሐሰተኛ መረጃ ለዓለም ፈተና መሆን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይልቁንም እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ቴሌግራም ያሉ የማኅበራዊ ሚድያ የተባሉ የብዙኀን መገናኛ አውዶች ከተፈጠሩ በኋላ፣ ጉዳታቸው አመዝኖ ለብዙ ጥፋቶች መንገድ ሆነው ተገኝተዋል። ‹ከፍተኛ ጥቅም አላቸው› ብለው የሚሟገቱ ሰዎች ሳይቀር፣ ጥቅሙ ጉዳቶችን የተከተለ እንደሆነ ያምናሉ። ይህ ምን ማለት ነው?
ለምሳሌ በአንድ ስፍራ የኹለት ሰዎችን አለመስማማት መነሻ አድርጎ፣ አብረው ሲኖሩ የቆዩ ሕዝቦች መካከል ግጭት እንደተፈጠረ አንድጎ በማኅበራዊ መገናኛ አውድ ላይ አንዱ ያወራል። ይህ አድጎ መፈናቀልን ያስከትላል። ይህን የሚቃወም ሌላ የበጎ ሰዎች እንቅስቃሴ ደግሞ ወዲህ ይጀመራል። ድጋፍ ይሰባሰባል፣ እርዳታ ይሰጣል።
ብቻ በድምሩ! ማኅበራዊ መገናኛዎች ዓለም ከጠቀሟት በላይ ጎድተዋታል፣ ወይም ከጎዷት በላይ ጠቅመዋታል የሚለው፣ ጥናት ሳይፈልግ አይቀርም።

የተለያዩና የተጠፋፉ ሰዎች የሚገናኙበት፣ ለአንድ ዓላማ ሰዎች የሚሰባሰቡበት፣ ትዳርና ጓደኝነት የሚጀመርበት፣ ምክርና የተለያየ ሐሳብ የሚገኝበት አውድ እንደሆነም ግልጽ ነው። ጉዳት ሲባል ግን፣ ስለማይመለስ የሰው ልጅ ሕይወት ጭምር ስለምናነሳ፣ ጉዳቱ አመዝኖ የሚያዩት ጥቂት አይደሉም።

አንቺ የሌለሽ ጊዜ! ‹ኢንተርኔት›
የሚካኤል በላይነህ መዚቃ ነው፣ ‹አንቺ የሌለሽ ጊዜ፣ የቆምኩበት ጠፋኝ ተጫነኝ ትካዜ…› እያለ በዜማ ይቀጥላል። ኢንተርኔት የተዘጋ ጊዜ ምን ይፈጠራል?
ከሰሞኑ የኢንተርኔት አገልግሎት ጭራሹን የለም። ይህም የሆነው የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ ሊፈጠር ይችላል የተባለውን ክስተት ለመቆጣጠር እንደሆነ መገመት ቀላል ነው።

በአዲስ አበባ ያለ ኢንተርኔት፣ በስልክ ጥሪ እና በጽሑፍ መልዕክት ብቻ እንኳ ‹አብያተ ክርስትያናት ተቃጠሉ› የሚል ዜና ከተማዋን እንዴት አውኳት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።
ይህን የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ታድያ ብዙዎች የተቃወሙት አይመስሉኝም። በእርግጥ ሁሌም ብጥብጥ በተነሳ ቁጥር ኢንተርኔት ተዘግቶ ይሆናል ወይ የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው። በተጓዳኝ ይህ ኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋት ድምጽን የማፈንና በኢንተርኔት የመጠቀም መብትን የሚጋፋ ነው ብለው የሚሞግቱ አሉ።

ያም ሆነ ይህ፣ በአሁኑ ሰዓት (ይህ ጽሑፍ ተጽፎ ለሕትመት እስከበቃበት ጊዜ ድረስ) የኢንተርኔት አግልግሎቶች መቋረጣቸው አዲስ አበባን እና ኢትዮጵያን በአንጻራዊነት ጠቅሟቸዋል።
የንግድ እንቅስቃሴያቸውን በኢንተርኔት ላይ መሠረት አድርገው የሚሠሩ ሰዎች ተጎድተዋል። በዛም ላይ ብቻ የሚንቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙኀን ድካም ይተርፋቸዋል፣ ቤተሰብ ከሩቅ አይገናኝም፣ አሁን በኮቪድ 19 የኮሮና ወረርሽ ወቅት ተማሪዎች በቋፍ የያዙት በኢንተርኔት አግልግሎት ላይ መሠረት ያደረገ ትምህርት የባሰ ይታጎልባቸዋል፣ መገናኛ ብዙኀን መረጃዎችን ለመቀባበልና ዜናዎችን ለማድረስ ተቸግረዋል። ሌላም ብዙ የማላውቀው ጉዳት እንደሚኖር አልጠራጠርም።

የሆነው የሚመስለኝ እንዲህ ነው። ‹ቤት የእግዚአብሔር ነው› የሚል ቤተሰብ ሁሌም በሩን ክፍት ያደርጋል፣ ሁሉንም ይቀበላል። አገሩ ሌባ የገባ ቀን ግን፣ እስኪያልፍ በሩን ይዘጋል። ዘው የለም፣ ሰው ከመጣም አንኳክቶ ማነህ ተብሎ ነው የሚገባው። ታድያ ለሁሉም ክፍት የነበረ ማኅበራዊ መገናኛ አውድም ለወትሮ ክፍት ሆኖ ይቆያል።

አገር በክፉ አሳቢዎቿ በተከበበች ጊዜ ታድያ ይህን ሐሰተኛ ዜና መግቢያ በር ብትዘጋ ተሳሳትሽ አትባልም። በዛም አለ በዚህ፣ የቀደሙ እንደ ቲቪና ጋዜጣ ያሉ በሮች አሉ። መረጃው በዛ አንኳክቶ ይገባል። አሁን እንደ ቀደመው ጊዜ ሰዎች መነጋገር፣ መደዋወል፣ ቴሌቭዥን መመልከትና ዜና መጠበቅ ጀምረዋል።

ምን ጠቀመ በሉኝ፣ በተለይም ጎልቶ የተሰማኝ አንድ ነገር አለ፣ ሰው በነጻነት ማሰብ ይችላል። እውነት ነው! ማኅበራዊ ገጾች አግልግሎት እየሰጡ ባይሆንም በስልክ ጥሪ እና በጽሑፍ መልእክት ብቻ ብዙ ሐሰተኛ ዜናዎች ተሰራጭተዋል። እነዚህን ግን መዋጋት ቀላል ነው። መደበኛ በሆኑ መገናኛ ብዙኀን ሐሰተኛ መሆናቸውን መግለጽ።

ለምሳሌ ኢንተርኔት በተዘጋበት ጊዜ ‹የአዲስ አበባ የቧንቧ ውሃ ተበከለ› የሚል መረጃ ተሰራጭቶ ነበር። ምንጩ ከየት እንደሆነ ባይታወቅም፣ በመደበኛ አውዶች ባይነገርም፣ በየስልካችን ግን ተደውሎ፣ የሚያስብልን ወዳጃችን ‹የቧንቧ ውሃ እንዳትጠጡ› የሚል መልእክት አድርሶናል። ‹መጀመሪያ ውሃዋም በኖረች!› ያለ አይጠፋም።

አንዳንድ ሰዎች ግን ‹መጠንቀቁ ቢበጅም፣ ሐሰተኛ ነው የሚሆነው› ማለታቸው አልቀረም። ምክንያቱም በራሳቸው እንዲያስቡና እንዲያሰላስሉ እድል አግኝተዋል። አስር ዓይነት በተለይም ከሐሰተኛ መረጃ ጋር የተገናኘ ሐሳብ ገብቶ አይረብሻቸውም።

የቅርብ ወዳጅና ቤተሰብ ጋር ደውለው፣ ‹ይህ ነገር እውነት ነውን?› ብለው ይጠይቃሉ። እገሌና እገሊት ባሉት ሳይሆን ከተጽእኖ ወጥተው ሐሳቦችን በፈቃዳቸው መዝነው፣ የተሻለ ሐሳብ ይሰጠኛል ያሉትን አማክረው ሊወስኑ ይችላሉ።

የማሰብ ነጻነት
የማሰብ ነጻነት ማለት የተለያየ ሐሳብን አለማስተናገድ ማለት አይደለም። ብዙውን ጊዜ በማኅበራዊ ሚድያዎች የሚነሱ ሐሳቦች ግን የሐሳብ ብዝኀነት ሳይሆን የስድብ ዓይነት የሚስተናገድባቸው ናቸው።

አንዳንድ ጥሩ ሐሳብ የሚሰጡ ሰዎች ሳይቀሩ የሚበሳጩበት ጊዜ አለ። የሚፈልጉትን የሐሳብ ሙግት ሳይሆን የስድብና ጽንፍ የያዘ የጥላቻ ንግግር በአስተያየት መስጫ ሳጥኖች ውስጥ ያገኛሉ።
እንዳልኩት ገንቢ ሐሳብ የሚሰጡም አሉ። ይህም ሐሳብን ለማዳበር፣ እይታን ለማስፋት ይረዳል። ማኅበራዊ ገጾች እንደ ዓለም ወይም እንደ አገር ወይም እንደ ሰፈር ናቸው። በዓለም፣ በአገር ወይም በሰፈር ላይና ውስጥ አንድ ሰው በሁሉም ሊወደድ አይችልም። አንድን ሐሳብም ሁሉም ሰው በእኩል መንገድና በተመሳሳይ ሊቀበለው አይችልም። ተቃራኒና አዲስ እይታ ያላቸው ሐሳቦች አሉ። እነዚህን በስርዓት ለማስተናገድ የበቃ ተጠቃሚ ግን አለ ብሎ በድፍረት መናገር አይቻልም።

‹ማኅበራዊ ሚድያ አረፍ ማለቱ፣ በነጻነትና በራሳችን ይረዳል ወይም ረድቷል› ሲባል፣ ተቃራኒ ሐሳብን ከመፍራት አልያም የአንድ ወገን ሐሳብ ብቻ ጸንቶ ሌላው እንዳይታይ ከማድረግ ፍላጎት የመነጨ አይምሰላችሁ።

ብዙዎች ግን አእምሯቸው በእነዚህ ማኅበራዊ ገጾች ቁጥጥር ስር ነው። የትኛውንም ሐሳብ በራስ ከማመዛዘን ይልቅ ‹እገሌና እገሊት ምን አሉ?› የሚለውን መሠረት አድርገው ማሰብ ይቀናቸዋል።
‹አይመስለኝም! ብዬ አላምንም! እንደዛ መሆን አለበት! ሳይሆን አይቀርም!› የሚሉ የራስን ሐሳብ መሠረት አድርገው ሊሰጡ የሚችሉ ግምቶች በተጽእኖ ስር አይገኙም። ‹ለካ እንዲህ ማለቱ ነው! ለካ እገሌ እንዲህ ብሎ ነው!› ወዘተ የሚሉትን በአንጻሩ እናገኛለን።

በተደራራቢ ሐሰተኛ ዜናዎች ላይ መሠረት ያደረገ የመረጃና ዜና ፍለጋም፣ ከመሠረቱ ሊናድ ስለሚችል ከመደበኛው መገናኛ ብዙኀን ጋር ተጣጥሞ የመሄድ እድሉ ጠባብ ነው።
እዚህ ላይ የመደበኛ መገናኛ ብዙኀንን ክፍተት አንዘነጋም። በተለይም ከአንድ ወገን ያልሆነና ሚዛናዊ ሥራዎች ቢቀርቡ፣ አስቀድሞ መገናኛ ብዙኀን ተዓማኒነትን ቢያገኙ ኖሮ፣ ይህ አይቀጠርም ነበር።

ምንአልባት ግን አሁንም እነዚህ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን እድል አላቸው። በተለይ ሰዎች እነዚህን አማራጭ አድርገው እየተከታተሉ ባለበት ጊዜ ለገዢው ፓርቲ፣ ሥልጣንና አቅም ላለው ብቻ ሳይሆን በሁሉም ወገን የታሸ እውነተኛ መረጃን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ለጊዜው ግን የማሰብ ነጻነታችንን ልብ ብለን በማስተዋል እናዳምጠው። ልብ በሉ! ያለምንም ተጨማሪ መረጃ አንድን ክስተት በራሳቸው ግምትና ትንታኔ ‹እንዲህ ነው እንዲያ ነው› የሚሉ ሰዎች በማኅበራዊ ሚድያው አሉ።

ምንም አዲስ መረጃ አለመጨመራቸው ያቀረቡት ሐሳብ ውስጣቸው የኖረ ክምር ሐሳቦች ውጤት እንደሆነ ግልጽ ነው። እነዚህ ሰዎች በዚህ የገዛ የግል ትንታኔያቸው፣ በተለይም ስድብና ቁጣ፣ ጥላቻና ጭካኔ የተመላ ከሆነ፣ እኔና እናንተስ በራሳችን እይታ ማሰባችን በምን ሊያንስ ይችላል?

የሥነ ልቦና ባለሞያ ወይም በዘርፉ አንዳች ጥናት ያደረግሁ ሆኜ አይደለም። ግን ነገሩን ለመረዳት ከባድ አይመስለኝም። ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ሱስ የሆነባቸው የሚመስሉ ሰዎች ሱሳቸው ከሰዎች ጋር ማውራት ወይም ‹ቻት ማድረግ› ካልሆነ በቀር፣ የሐሳብ ጥገኝነት እንደሆነ አያጠራጥርም። እንዳልኩት የተለያየ ሐሳብ ማግኘትና እይታን የማስፋት ጉዳይ አይደለም፣ የራሳቸውን ትተው የሌሎችን ሐሳብ ጭነው የሚንቀሳቀሱ ጥቂት አይደሉም ነው።

እንዲህ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ሲዘጋ ግን ሰዉ በራሱ ዳሰሳና ግምት ጉዳዮችን ይበይናል። ያለበትን ደረጃ ያውቃል። ሰዎች ሲያወሩ ይሰማል፣ አስተያየት ይሰጣል፣ ይቀበላል። ‹የኔ ነው!› የሚለው የሚያምንበትና የራሱ የሆነ እይታና ሐሳብ ይኖረዋል።

ይህን ያልኩት ታድያ በዚህ አውድ ፍጽምና አለ፣ ፍጹም ስህተት የለም በሚል እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። በንጽጽር ሲቀመጥ እንጂ፣ በገዛ ሐሳቡ ብቻ በጥላቻ ተነሳስቶ የሚጽፍ፣ ሰው የማያማክር ሰው ነው በማኅበራዊ መገናኛዎች እሳት ለኩሶ ችግር የሚፈጥረው።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here