የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር በኅብረተሰቡ ዘንድ ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ላይ መዘናጋት መታየቱ ጉዳቱን እጥፍ ያደርገዋል ሲል ስጋቱን አስታወቀ።
የጤና ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ የኮሮና ቫይረስ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ የተገለፀ ጊዜ የነበረው ጥንቃቄ እና ትኩረት መስጠት አሁን አብዛኛውን በሚባል ደረጃ የለም። ይህም ከዚህ ቀደም ይደርስ ከነበረው እና ከደረሰው በላይ ጉዳቱ ከፍተኛ ምናልባትም በእጥፍ ሊያሳድገው እንደሚችል እና ሕዝብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር የጤና ባለሙያ የሆኑ የአዲስ ማለዳ ምንጭ አስታውቀዋል።
ምንጫችን እንደሚሉት ከሆነ የኮሮና ቫይረስ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተሰራጨበት ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹ ሲሆን፣ በተዘናጋን እና ትኩረት በነሳነው ቁጥር አደጋው የከፋ እንደሚሆንም አልሸሸጉም። ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ኮሮና መግባቱን ተከትሎ በመጀመሪያዎቹ ሰሞናት ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከማድረጉ ባሻገር ሕግ አስከባሪ አካላት ጠበቅ ያለ ክትትል እና ጥበቃ ሲያደርጉ ይስተዋል ነበር።
እነዚህ በሕግ አስከባሪ አካላት በኩል ይደረጉ የነበሩ ክትትል እና ቁጥጥሮች የበዛ ቁጥር ያለው የማኅበረሰብ ከፍል በሚንቀሳቀስበት ስፍራ፤ መጠጥ ቤቶችን ጨምሮ በሌሎች የመዝናኛ ስፍራዎች ላይ ይደረግ ነበር።
አሁን ላይ ግን እነዚህ በሕግ አስከባሪ አካላት አማካይነት የሚደረጉ ክትትሎች እና የቁጥጥር ሥራዎች ትኩረት ተነስቷቸዋል የሚሉ ቅሬታዎችን ከአንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች ይነሳል። እንዲሁም አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በተመለከተቻቸው የአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የምሽት ቤቶች እና ሕዝብ የሚበዛባቸው ስፍራዎች ወደ ቀደመው ሥራቸው መመለሳቸውን ለመታዘብ ችላለች።
ይህንንም በሚመለከት ምላሻቸውን የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢኒስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ ክትትሉ አሁንም እንዳለ እና እርምጃ የመውሰዱ ሂደትም ተጠናክሮ መቀጠሉን አፅንኦት ሰጥተው አንስተውታል።
እንደ ኢንስፔክትር ማርቆስ ገለፃ የኅብረተሰቡ መዘናጋት እና ችላ ማለት የፖሊስን ቁጥጥር መጠበቅ አስፈላጊ አይደለም በማለትም ለአዲስ ማላዳ ተናግረዋል። ከዛም በተጨማሪ በአንዳንድ የመዝናኛ ቦታዎች እና በጎዳናዎች ላይ ኅብረተሰቡ ወረርሽኙን እና የሚያስከትለውን የከፋ ጉዳት የመዘንጋት አልፍ ሲል ጠፍቷል ብሎ የማሰብ ስሜት እንደተስተዋለ ታዝበናል ሲሉ ኢንስፔክተር ማርቆስ አስታውቀዋል።
የሚታዩት መዘናጋቶች ከግለሰብ ጤና አልፎ አገር ላይ ሊያደርስ የሚችለው የከፋ ጉዳት ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ መሆኑን ታሳቢ በማድረጋችን በኮማንድ ፖስት ስር አሁንም እንዳለን እና ሕጉ ተፈፃሚነት እንደሚኖረውም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በሕጉ መሰረት ማስክ ወይም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሳያደርጉ የሚንቀሳቀሱ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና በየቦታው ከአራት ሰው በላይ ተሰብስቦ የሚገኝ ከዛም በተጨማሪ መጠጥ ቤቶች ተከፍተው ሕዝብ ተሰባስቦባቸው ቢገኙ አሁንም ተጠያቂ እንደሚሆኑ እና ፍርድ ቤት ቀርበው ከአምስት ሺሕ ብር ገንዘብ ቅጣት እስከ ዐስር ሺሕ ብር ድረስ የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል በማለት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በየቀኑ የሚመዘገበው የሟቾች እና በወረርሽኙ የሚያዘው ሰው ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን በየቀኑ ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የሚያወጣው ሪፖርት አመላካች ነው። ከዚህም በመነሳት እስከ አሁን ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ ይህም እንደ ጤና ሚኒስቴር ገለጻ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችልም ተጠቁሟል።
በኅብረተሰቡ ዘንድ በተለይም ደግሞ ከቀናት ወዲህ የታየውን አለመረጋጋት ተከትሎ ቁጥራቸው እጅግ የላቁ ሰዎች በአንድ ላይ እና ርቀትን ባልጠበቀ መልኩ ተጠጋግተው ተስተውለዋል። ይህም ለወረርሽኙ በፍጥነት መሰራጨት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012



