አዳዲስ ወደ ገበያ እየገቡ ያሉ የውሃ አምራች ድርጅቶች ከዋጋ በታች በመሸጥ ነባር ድርጅቶችን ከገበያ እንዲወጡ እና ፋብሪካዎቻቸውን እንዲዘጉ እያስገደዱ እንደሆነ ቅሬታ ቀረበ።
ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡት የአርኪ የመጠጥ ውሃ አምራች ድርጅት አዳዲስ የውሃ አምራቾች ስርአትን ተከትለው እና የንግድ ሕጉ ሳይገባቸው እየሠሩ በመሆኑ እኛ ከገበያ እንድንወጣ እያደረጉን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ያለአግባብ የገበያ ውድድር ለማድረግ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ገበያውን ለመቆጣጠር በማሰብ ከደረጃ በታች ምርት አምርቶ ከዋጋ በታች መሸጥ እየተለመደ ነው ሲሉ ጌታነህ አስፋው፣ የአርኪ የመአድን ውሃ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ይሄ ነገር በፍጥነት ቁጥጥር ካልተደረገበት እና ትኩረት ካልተሰጠው የሚመለከታቸው አካላትም ሥራቸውን በአግባብ ካልሠሩ፣ አርኪ የታሸገ የመጠጥ ውሃ አቅራቢም ከገበያ መውጣቱ የማይቀር ነው ብለው እንደሚሰጉም ገልጸዋል።
መንግሽት በድርሻው የሚጠበቅበትን ማድረግ እና ከዛም በተጨማሪ ውሃ አምራች ድርጅቶች ማኅበር በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ውይይት ላይ መሆናቸውን ገልፀው፤ የሸማቾች ማኅበርም የተወሰኑ ተገቢ ያልሆነ ሽራ የሚሸሩ የውሃ አምራቾችን እያነጋገረ ነው። በዚህም የተወሰነ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ብለው እንደሚገምቱም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይህ ካልሆነ ለምጣኔ ሀብቱ መድቀቅ እና ለአንዳንድ ድርጅቶች ከገበያ መውጣት ምክንያት መሆኑ የሚቀር አይደለምም ብለዋል።
ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ጋር በመሆን ተደጋጋሚ ቅሬታ ለተለያዩ አካላት መቅረቡንና በዋነኛነትም ለውሃ አምራቾች ማኅበር አቅርበው እንደነበር አውስተዋል። ‹‹በጥያቄያችንም ከአንድ ወር እስከ ኹለት ወር የሚቆይ የገበያ ዋጋ እንዲወጣልን ብለን ብንጠይቅም አንዳንዶች ከዚህ በማፈንገጣቸው ተገቢውን ውጤት ማግኘት አልቻለንም።›› ጌታነህ የተናገሩት ነው።
ጌታነህ በገለፃቸው አሁን ከመንግሥት የሚጠበቀው ጤናማ የሆነ የገበያ ውድድር እንዲኖር ማድረግ እና ገበያ ላይ እንዲወጡ የሚደረጉት የታሸጉ ውሃ መጠጦች ሁሉንም የጥራት ደረጃ ያለፉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ላይ መሥራት ይኖርበታል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ይሄ ነገር ሲደጋገም እና እንደዚህ አይነት ድርጅቶች ሲበዙ ሁሉንም ደረጃ አልፈው በትክክለኛ መንገድ የሚሠሩ ድርጅቶችን ከገበያ ውጪ የሚያደርግ እና በስሩ ቀጥሮ ያሠራቸው የነበሩትን ሠራተኞች እስከመበተን የሚያደርስ ትክክል ያልሆነ ሥራ ነው ሲሉም ኮንነዋል።
ከዋጋ መቀነስ ጋር የተያያዘ ሂደት ተጠቃሚውን ይሄ ብቻ ያስደስታል ብለው መውሰድ የለባቸውም። ከዛ ውጪ ግን ፍትሃዊ የሆነ የንግድ ውድድር ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ይፈጥራል ብለዋል። ትክክለኛ ደረጃውን እና ከፍተኛ ወጪ አውጥተው የሚሠሩትን፣ ብዙ ሂደትን የሚከተሉ ድርጅቶችን ያለአግባብ የሆነ ትልቅ ጫና ይፈጥራል ሲሉ ጌታነህ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
‹‹ገበያ ላይ በማንኛውም ጊዜ ያለአግባብ ውድድር የሚፈጥሩ ነገሮች ሲመጡ ተፅዕኖው ማሳደራቸው አይቀርም። አዲስ የሚመጡ ውሃ አምራቾችም አዲስ ነገረ ይዞ መምጣት ተመራጭ ለመሆን ዋና ምክንያት መሆን አለበት እንጂ በርካሽ በመሸጥ መሆን የለበትም።›› ሲሉ አክለዋል።
ነገር ግን አሁን ሁሌም አዲስ ውሃ ወደ ገበያው ሲገባ የተወሰነ ገቢ ድርሻ ለማግኘት እየተጠቀሙበት ያለው ቴክኖሎጂ ዋጋን የመቀነስ ስትራቴጂ ብቻ ነው። አርኪ ውሃ ከተመሠረት እና ገበያ ላይ ከቆየ አምስተኛ ዓመቱን የያዘ የታሸገ ውሃ አምራች እና አቅራቢ ድርጅት ነው። ከኹለት መቶ ሃምሳ በላይ ሠራተኞችንም ያስተዳድራል። ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ የውሃ አምራቾች ማኅበርን ለማናገር ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012



