በተገባደደው ዓመት 10ኛ ክልል በመሆን በይፋ የተካለለው እና ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበት የነበረው የሲዳማ ክልል በጀት እንደ አዲስ ለብቻ ተሠርቶ ለምክር ቤት ቀርቦ ጸድቋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 30/2012 የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል መንግሥት የ2013 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና ውሳኔ ሐሳብ መርምሮ የበጀት አዋጁን አጽድቋል። በዚህም ወቅት በፌዴራል መንግሥት ለቀጣዩ ዓመት ማለትም ለ2013 በጀት ዓመት የተበጀተው እና ለምክር ቤቱ የቀረበውን በጀት በሚመለከት በቅርቡ ክልል በመሆን የተካለለው እና ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የተለያየው የሲዳማ ክልል በጀት ለብቻው ተሠርቶ በመቅረቡ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
በጀቱ ለምክር ቤት በቀረበበት ወቅት ከዚህ ቀደም ይሠራ እንደነበረው በዘጠኝ ክልሎች እና በኹለት ከተማ አስተዳደሮች የተከፋፈለ እንደነበር በመታወቁ እና ከምክር ቤት አባላት በተለይም ከሲዳማ ዞን የተወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዘንድ ከባድ ተቃውሞ እና ሰፊት ቅሬታ ቀርቦበት ነበር። በዚህም ወቅት የሲዳማ በዞንነት እንደነበረበት የቀደሙት ዓመታት በመታሰብ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል 36 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተመድቦለት እንደነበር የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ ከምክር ቤቱ ለቀረበው ቅሬታ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር አሕመድ ሽዴ በሰጡት ምላሽ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የበጀት ቀመሩን ከክልሎች የሕዝብ ብዛት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር አስልቶ እንደሚያቀርብላቸው እና ሚኒስቴሩም በጀቱን እንደሚሠራ በመጠቆም በቀጠይ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሠርቶ ካመጣ በጀቱን እንደሚያስተካክሉም ገልጸው ነበር።
በመሆኑም በሰኔ 30/2012 ምክር ቤቱ ባካሔደው ጉባዔ አስረኛው ክልል ሲዳማ 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተሠርቶለት በቋሚ ኮሚቴው ለምክር ቤቱ በመቅረቡ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። ከቀረበው በጀት ውስጥም 6 ነጥብ 904 ቢሊዮን ብር ከመንግሥት ግምጃ ቤት ሲሆን፣ ቀሪው 9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከውጭ አገር እርዳታ እንደሆነም በበጀት ድልድሉ ወቅት ተገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ ለምክር ቤት ቀርቦ ወደ ቋሚ ኮሚቴው ተመርቶ በነበረው የ2013 በጀት ዓመት ከፌዴራል መንግሥት የቀረበው በጀት ለደቡብ ክልል 36 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በድጋሚ የሲዳማ ክልል በጀት ለብቻው በተስተካከለበት ወቅት ወደ 27 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ዝቅ እንዲልም ሆኗል።
ለቀጣዩ ዓመት የተበጀተው በጀት 133 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም በ2012 ከተደለደለው የ16 ነጥብ 7 በመቶ ቅናሽ እንደሚያሳይ ለምክር ቤቱ ቀርቧል። ከበጀቱም ውስጥ 34 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው ለደሞዝ አበል እና ልዩ ልዩ ክፍያዎች እንደሚውል ተገልጿል። የካፒታል በጀት 160 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለክልሎች የሚሰጥ ድጎማ 176 ነጥብ 3 ቢሊዮን እንዲሁም የመጨረሻው ለዘላቂ ልማት የሚውል 6 ቢሊዮን ብር መሆኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
በአሕመድ ሽዴ ለሕዝብ ተወካዮች በቀረበበት ሪፖርት እንደሚያመለክተው በ2013 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጮች እንዲሁም ከውጭ ዕርዳታ በድምሩ 350 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚሰበስብ በዕቅዱ መያዙም ታውቋል። በቀጣዩ ዓመት የበጀት ዕቅድ ውስጥ በፌዴራል መንግሥት ገቢ እና ወጪ በጀት መካከል 126 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት መታየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 3 በመቶ እንደሚይዝ ታውቋል።
የ2013 በጀት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዕድገት ቢኖረውም ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ወጪ ፍላጎት እንደሚጨምር ታሳቢ ተደርጎ እና ከአገሪቱ የልማት ፍላጎት አንጻር በቂ ነው ሊባል እንደማይችልም አሕመድ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል። የቀጣይ ዓመት በጀት ማለትም 2013 ከቀዳሚው ዓመት 2012 በ30 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወይም የሰባት በመቶ እድገት እንዳለውም ተገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012


